የ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የ ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመጡ ካህናት እና መዘምራን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ በርካታ ምእመናን እሁድ መስከረም ፲፮ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
በዓሉ እሁድ እለት ከሰዓት በኋላ በካህናት አባቶች ጸሎት የተጀመረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ መዘምራን በዓሉን የተመለከቱ መዝሙራትን አቅርበዋል፣ የወንጌል ትምህርት ደግሞ ሥርዓተ ጸሎቱን በመሩት አባታችን ቀሲስ ተስፋዬ ከተሰጠ በኋላ በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን እንዲሁ በዓሉን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል።በማስከተልም ደመራው ተባርኮ የተለኮሰ ሲሆን መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል፤በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።
በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት ላደረጋችሁት መንፈሳዊ አስትዋጾ ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን ዝግጅት በፎቶ ይመልከቱ!

የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ፤ የ፳፻፰ ዓ.ም ቅዱስ ዮሐንስ በዓልም በድምቀት ተከበረ

በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።

የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።

መዝ ፷፭፥፲፩

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ።

የቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በትሮንዳሔም ከጷግሜ ፮፥፳፻፯ ዓ.ም እስከ መስከረም ፪፥፳፻፰ ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የቆየ መንፈሳዊ ጉባኤና የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ከኢትዮጵያ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተጋብዘው ወደ አውሮፓ በመጡት መምህር (ቀሲስ) ለማ በሱፍቃድ አካሄደ። በአዲስ አመት ዋዜማ በስብከተ ወንጌል የተጀመረው ጉባዔ ቅዳሜ መስከረም ፩፥፳፻፰ ዓ.ም ሲቀጥል መርሐ ግብሩ በኪዳን ተጀምሮ፣ የአመቱ ባሕረ ሃሳብ ወጥቶ ስለቤተክርስቲያናችን ዘመን አቆጣጠር ትምህርት ተሰጥቷል። የእሁድ መርሐ ግብርም እንዲሁ በኪዳን ጸሎት ተጀምሮ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ በተለይም በዓሉን የሚያስታውሱ መዝሙሮች ተዘምረው የጉባዔው ፍጻሜ ሆኗል።

መርሃግብሩን በፎቶ ይመልከቱ

የሊቀ ሰማዕታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ መልኩ ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፣ ፳፻፯ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ ምእመናን ዓርብ ሚያዚያ ፳፫ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፬ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ዓርብ እለት ከሰዓት በኋላ በጸሎት የተጀመረ ሲሆን ስለ ቅዱስ ያሬድ በሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ፣ የወንጌል ትምህርት ደግሞ በዲያቆን ብሩክ አሸናፊ ከተሰጠ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ መዘምራን፣ በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን እንዲሁም በዲያቆን ብሩክ በአሉን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል። በመጨረሻም የማሳረጊያ ትምህርት በመጋቤ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ ተሰጥቶ የዓርብ ከሰአቱ ጉባኤ በጸሎት ተፈጽሟል።

በመቀጠልም ጉባኤው ዓርብ ለቅዳሜ ሌሊቱን በሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ ዲያቆናት፣ የሰ/ት/ ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማሕሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። እንዲሁም የነግህ ኪዳንና የቅዳሴው ስርዓት ሲጠናቀቅ በአጥቢያው መዘምራንና በዲያቆንብሩክ አሸናፊ ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በመልዓከ ጽዮን ቆሞስ አባ ሙሴተሰጥቷል። ከእለቱ ትምህርት በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግስ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል።

በመጨረሻም በአባቶች በቅርቡ ስለእምነታቸው ሰማዕት ለሆኑ ክርስቲያኖች ጸሎት ካደረሱ እና ምዕመኑ ጧፍ በማብራት እንዲታሰቡ ከተደረገ በኋላ ታቦተ ህጉ ወደመንበረ ክብሩ ተመልሷል። ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት ላደረጋችሁት መንፈሳዊ አስትዋጾ ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን ዝግጅት በፎቶ ይመልከቱ!

በትሮንዳሄም የ፳፻፯ ዓ.ም. የስቅለትና የትንሣኤ በዓላት አከባበር

ክርስቶስ ተንስአ እሙታን…….በዐብይ ኃይል ወስልጣን
አሰሮ ለሰይጣን ………….አግአዞ ለአዳም
ሰላም…………እምይእዜሰ
ኮነ …………….ፍስሀ ወሰላም
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለትና ትንሣኤ በትሮንዳሄም ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከበረ። ዕለታቱን በአባ ገብረ ማሪያም ቢምረው እና በቀሲስ ካሳዬ አንተነህ የትሮንዳሄም አጥቢያና አካባቢው ምእመናን በተገኙበት ዓርብ ስቅለትን በስግደት እንዲሁም ቅዳሜ ሌሊት ደግሞ የትንሣኤን በዓል በቅዳሴ፣ በወረብና በዝማሬ በድምቀት ተከብሯል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

በትሮንዳሄም የሆሳዕና በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም የሆሳዕና በዓል መጋቢት ፳፯፥፳፻፯ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ። መርሃ ግብሩ በጸሎት ተጀምሮ በህጻናትና በአጥቢያው መዘምራን በዓሉን የተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌል በቀሲስ ወንድወሰን ተሰጥቷል።በመጨረሻም ቀጣዩ ሳምንት “ሰሙነ ህማማት” በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ስርዓት መሠረት ለምእመናን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎ የዕለቱ መርሃ ግብር በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓልን ከመጋቢት ፭ እስከ ፮፥ ፳፻፯ ዓ.ም. ከተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በመጡ አባቶች ካህናት እና ወንድሞች ዲያቆናት እንዲሁም በአካባቢው ከሚኖሩ ምእመናን ጋር በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌልና በያሬዳዊ ዝማሬ በድምቀት ተከብሯል። በዚህ በዓል ላይ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ የእረፍት ቀንም ታስቦ ውሏል። በበዓሉም ላይ በመልዓከ ጽዮን ቆሞስ አባ ሙሴና በዲያቆን ዓብይ በዓሉን በሚመለከት ትምህርተ ወንጌል በሰፊው ተሰጧል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

የ፳፻፯ ዓ.ም. የልደት በዓል አከባበር

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም አጥቢያ በሚገኙ ምእመናን እና ምእመናት በዓሉ በቅዳሴ፣ በዝማሬና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተከብሮ ዋለ።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

በትሮንዳሔም የ ፩ ቀን ጉባኤ ተካሄደ

ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ተጋብዘው ኖርዌይ በመጡት በዘማሪ ዲያቆን እንግዳወርቅ በቀለ እሁድ ህዳር ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም በትሮንዳሔምና አካባቢው ለሚገኙ ምእመናን ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና ስብከተ ወንጌልን ያካተተ ጉባኤ አካሄደ።

ጉባኤውን በፎቶ ይመልከቱ

የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በትሮንዳሔ በአካባቢው ለሚገኙ ምእመናን ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከጥቅምት ፳፰ እስከ ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሄደ። በጉባኤውም ላይ ቀሲስ ወንድወሰን ሶርሳን በመጋበዝ እምነት እና በዓለ መድኃኒዓለምን በተመለከተ ሰፋ ባለ መልኩ ትምህርተ ወንጌል ተሰጧል። ከምእመናን በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ መርሃ ግብሩ በሥርዓተ ጸሎት ተጠናቋል።

ጉባኤውን በፎቶ ይመልከቱ

የ፳፻፯ ዓ.ም የመስቀል በዓል ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም የመስቀል በዓል ዓርብ መስከረም ፲፮ ፳፻፯ ዓ.ም በስርዓተ ጸሎት፣ ደመራ በማብራት እና በያሬዳዊ ዝማሬ በየአመቱ እንደሚደረገው በመሆልት የተማሪዎች መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ቀሲስ ተስፋዬ ፣ የደብሩ መዘምራንና በአካባቢው የሚኖሩ ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት በዓሉ በድምቀት ተከበረ። ቀሲስ ተስፋዬ በዓሉን የሚመለከት ትምህርተ ወንጌል አስተላልፈዋል እንዲሁም የደብሩ መዘምራን የመዝሙር አገልግሎት አቅርበዋል።

የመስቀል በዓል አከባበርን በፎቶ ይመልከቱ