በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሄም ተከታታይ መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት፤ ህዳር 18-19/2008ዓ.ም (November 28-29, 2015) እና ህዳር 25-26/ 2008ዓ.ም (December 05-06/2015) ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤ በትሮንዳሄምና በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን በተገኙበት ተካሄደ። በጉባኤው መጀመርያ ቀን ቅዳሜ ህዳር 18 በአባታችን መልዓከ ሃይል መምህር አባ ዘድንግል (በጣልያን ባሪ ከተማበሚገኘው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ) እና በዲ/ን ዶ/ር አለማየሁ በጸሎተ ኪዳን ተጀምሯል። በእለቱም በዲ/ን ዶ/ር አለማየሁ እና በአባታችን በአባ ዘድንግል ትምህርተ ወንጌል ሰፋ ባለ መልኩተሰጥቷል። እንዲሁም በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙራት ከቀረቡ በኋላ የእለቱን መርሃ ግብር አባታችን በጸሎት አሳርገው ጉባኤው ተጠናቋል።

 ጉባኤው በመቀጠል እሁድ፣ ህዳር 19 በጠዋቱ የቅዳሴ ስርዓት ከተከናወነ በኋላ በአባታችን አባ ዘድንግል ሰፋ ያለ ትምህርት ተሰጥቶ የዕለቱ ጉባኤ ፍጻሜ ሆኗል።

 በቀጣዩ ሳምንት፤ ቅዳሜ ህዳር 25 ጠዋት ጸሎተ ኪዳን ደርሶ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ያተኮረ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል። የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤው ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክና በመዋቅር ስር መሆናችን ለቤተ ክርስቲያናችን ያለውን አስፈላጊነት እንዲሁም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት እንደሚታይ አጠር ያለ ማብራሪያ ለምዕመናን በመግለጽ ሰፊ ውይይት እንዲካሄድ ተደርጓል። በተነሱ ጥያቄዎችም ላይ በአባታችን መልዓከ ሃይል አባ ዘድንግል እና በወንድማችን ዲ/ን ሰሎሞን ገብረሚካኤል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና ቃለ ዓዋዲን መሰረት አድርጎ ለጠቅላላ ጉባኤው በዝርዝር ግንዛቤ ተሰጥቷል። ከዚህም በመነሳት አንዲት፣ ቅድስትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር ታቅፋ ትተዳደር ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስርእንድትሆን በማለት ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል።

  በጉባኤው መጨረሻም ቀን ዕሁድ ጠዋት ስርዓተ ቅዳሴ ተከናውኖ በአባ ዘድንግል የወንጌል ትምህርት እንዲሁም በዲ/ንሰሎሞን ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ መርሃ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል።

የጉባዔውን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!