የ፳፻፲ የጌታችን ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቤተክርስቲያናችን በደማቁ ተከበረ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

ሞተ ወኬዶ ለሞት

ለእለ ውስተ መቃብር

ወሃበ ሕይወተ ዘለዓለመ ዕረፍተ።

የ፳፻፲ ዓ.ም የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ በድምቀት ተከበረ። በዓላቱ ከስዊድን ተጋብዘው በመጡት አባታችን መልአከ ህይወት ፍስሐ አባ ገብረማርያም ቢምረው እና በርካታ ቁጥር ባለው የትሮንዳሄምና አካባቢው ምእመን ሱታፌ በተለያዩ አገልግሎቶች ተከብሯል።

ዕለተ ዓርብ መጋቢት ፳፰፥፳፻፲ ዓ.ም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታችንን ስቅለት በሚያወሱ ምንባባት፣ ሕማሙን በሚዘክሩ ጸሎቶች እንዲሁም በስግደት ያለፈ ሲሆን፤ በመጨረሻም ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ተሰጥቶ በቡራኬ የዕለቱ መርሃ ግብር ተፈጽሟል።

ቅዳሜ ምሽት ከ20:00 ሰዓት ጀምሮ የጌታችንን ትንሣኤ የሚያወድስ ሥርዓት ከምንባባት ጋር ከተከናወነ በኋላ በሥርዓተ ቅዳሴና ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀምሰው ወደየቤታቸው በሰላም ተመልሰዋል።

 

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ።

የ፳፻፲ ዓ.ም. የዘመን መለወጫና የመስቀል ደመራ በዓላት በደመቀ ሁኔታ ተከበሩ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የ፳፻፲ ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓልን በማስመልከት እሁድ ጷጉሜን ፭፥፳፻፱ ዓ.ም ከዴንማርክ ተጋብዘው በመጡት አባ ዘሚካኤል የቅዳሴ አገልግሎትና የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በዕለቱ ከትሮንዳሄምና አካባቢው የተገኙ ምዕመናንም በክብረ በዓሉ ላይ ታድመዋል። በተጨማሪም ቀኑን የተመለከቱ መዝሙሮችም በኅብረት ተዘምረዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ማክሰኞ መስከረም ፲፮፥፳፻፲ ዓ.ም በትሮንዳሔምና አካባቢው ከተገኙ ምዕመናን እንዲሁም ከቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመጡ ምዕመናንና አገልጋዮች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

በዓሉ ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት በኋላ 17:00 ሰዓት ላይ በጋራ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመጡ አገልጋዮች ወረብና ቀኑን የሚያወሱ ንባቦች ቀርበዋል። በመቀጠልም የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በዓሉን የተመለከተ መዝሙራትን ያቀረቡ ሲሆን ስለመስቀል በዓል የሚያስረዳ ስነ ጽሁፍም ቀርቧል። ቀጥሎም ደመራው በወረብና በመዝሙር ምስጋና በመታጀብ ተለኩሷል። መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል። በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽኦ ላበረከታችሁ ምዕመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓላቱን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሚያዚያ ፳ እና ፳፩ ፥ ፳፻፱ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፱ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ዓርብ ሚያዚያ ፳ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፩ ፥፳፻፱ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ዓርብ እለት ምሽት ላይ በጸሎት ተጀምሮ በዲያቆን ብሩክ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ከቀረቡ በኋላ የወንጌል ትምህርት በመልአከ ምህረት አባ ዘሚካኤል ደሬሳ የተሰጠ ሲሆን በመቀጠልም የቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙሮችን እና ወረብ አቅርበዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ማኅሌት ላይ ከሚቀርቡ በዓሉን ከሚያወድሱ ወረቦች መሃከል አንዱን በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እና በአጥቢያው መዘምራን በጋራ ቀርቧል። በመጨረሻም የዓርቡ ጉባዔ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ማሳረጊያ ትምህርትና በአባ ላዕከ ማርያም ቡራኬ ተፈጽሟል።

ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማኅሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። የማኅሌቱ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ የነግህ ኪዳንና የቅዳሴ ስርዓት ተከናውኗል። በመቀጠልም በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በአባ ላዕከ ማርያም ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግሥ በዝማሬና በምስጋና በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ፤ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በአባቶች የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉ ላይ የተገኙት ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

የበዓሉን የቀጥታ ስርጭት ምስሎች ለማየት የቤተክርስቲያናችንን የፌስቡክ ገጽ ይጎብኙ https://www.facebook.com/StGeorgeEOTCTrondheim/?hc_ref=SEARCH

የበዓሉን አከባበር በፎት ይመልከቱ!

የ፳፻፱ የጌታችን ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቤተክርስቲያናችን በደማቁ ተከበረ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

ሞተ ወኬዶ ለሞት

ለእለ ውስተ መቃብር

ወሃበ ሕይወተ ዘለዓለመ ዕረፍተ።

የ፳፻፱ ዓ.ም የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም በድምቀት ተከበረ። በዓላቱ ከስዊድን ተጋብዘው በመጡት አባታችን መልአከ ህይወት ፍስሐ አባ ገብረማርያም ቢምረው እና በርካታ ቁጥር ባለው የትሮንዳሄምና አካባቢው ምእመን ሱታፌ በተለያዩ አገልግሎቶች ተከብሯል።

ዕለተ ዓርብ ሚያዝያ ፮፥፳፻፱ ዓ.ም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታችንን ስቅለት በሚያወሱ ምንባባት፣ ሕማሙን በሚዘክሩ ጸሎቶች እንዲሁም በስግደት ያለፈ ሲሆን፤ በመጨረሻም ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ተሰጥቶ በቡራኬ የዕለቱ መርሃ ግብር ተፈጽሟል።

ቅዳሜ ምሽት ከ20:00 ሰዓት ጀምሮ የጌታችንን ትንሣኤ የሚያወድስ ሥርዓት ከምንባባትና ወረቦች ጋር ከተከናወነ በኋላ በሥርዓተ ቅዳሴና ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀምሰው ወደየቤታቸው በሰላም ተመልሰዋል።

የበዓሉን አከባበር በፎት ይመልከቱ!

የደብረ ዘይት በዓል በድምቀት ተከበረ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓል መጋቢት 9፥ 2009 ዓ.ም ከስዊድን በመጡት አባት አባ ገብረ ጊዮርጊስ እና በትሮንዳሄምና አካባቢው በሚገኙ ምእመናን በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌልና በንሰሃ ዝማሬዎች በድምቀት ተከበረ። በበዓሉም ላይ በአባ ጊዮርጊስ ዕለቱን የተመለከተ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል።

የበዓሉን አከባበር በፎት ይመልከቱ!

የጥምቀት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በትሮንዳሔም በድምቀት ተከበረ

ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በተካሄደው የጥምቀት በዓል ላይ ከበርገን የመንበረ ልዑል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከስታቫንገር የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ከክርስቲያንሳንድ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ በተጨማሪም ከትሮንዳሔም ቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምእመናን ተገኝተው በዓሉን በጋራ አክብረዋል። በዓሉን ለማክበር ከኦስሎ፣ ከላቫንጋርና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች፤ ከኖርዌይ ውጭ ደግሞ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከስዊድን፣ ከዴንማርክና ከስዊዘርላንድ ጥሪ የተደረገላቸው አባቶች ካህናት፣ ዲያቆናት እንዲሁም ምዕመናን በበዓሉ ላይ ተካፍለዋል።

Read more

ለ፪ ቀናት የቆየ ልዩ መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሃገረ ስብከት የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮጳ በመጡት በኩረ መዘምራን ኪነጥበብ ወ/ቂርቆስ እና መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ ለ፪ ቀናት የቆየ የዝማሬና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተካሄደ። ጉባዔው ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ ምዕመናን ቅዳሜ መስከረም ፳፰ በ 9:00 ሰዓት እንዲሁም መስከረም ፳፱ በ 10:30 ሰዓት ስለሃገራችን ሰላምና መረጋጋት የዘወትርና የምኅላ ጸሎት በማድረስ ተጀምሯል። በመቀጠልም ያሬዳዊ መዝሙሮች በበኩረ መዘምራን ኪነጥበብ ከስብከተ ወንጌል አገልግሎት በፊትና በኋላ ተዘምረዋል። የሁለቱም ቀናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተሰጠው በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ነበር። በተጨማሪም ስለ ኦርቶዶክሳዊ መዝሙር ከምዕመናን የቀረቡ የተለያዩ ጥያቄዎች በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ከመርሃግብራቱ ፍጻሜም በኋላ ምዕመናን የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

ጉባዔውን በምስል ይመልከቱ!

የ ፳፻፱ ዓ.ም መስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ፤ የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባዔም ተካሄደ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሃገረ ስብከት የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮጳ በመጡትና ወደ አጥቢያችን የመስቀልን በዓል ለማክበር በተጋበዙት መምህር ፍቃዱ ሳህሌ የ፫ ቀናት ጉባዔ ተካሄደ። ቅዳሜ፣ እሁድ እንዲሁም ማክሰኞ (ከመስከረም ፲፬ – ፲፯) በተካሄደው ጉባዔ ላይ በተለያዩ ርዕሶች መንፈሳዊ ትምህርት ለትሮንዳሔምና አካባቢው ምዕመናን የተሰጠ ሲሆን ከምዕመናን በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ምክረ አበው በማክሰኞው ጉባዔ ተሰጥቷል።

በተያያዥነትም ሰኞ፣ መስከረም ፲፮፥፳፻፱ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል መምህር ፍቃዱ ሳህሌ፣ የአጥቢያው የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ምዕመናን እንዲሁም ከኤርትራ ቅዱስ ሚካኤል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመጡ ካህናትና ዲያቆናት፣ መዘምራንና ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ ሰኞ እለት ከሰዓት በኋላ 17:30 ላይ በካህናት አባቶች ጸሎት እንዲሁም ወረብ የተጀመረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በዓሉን የተመለከቱ መዝሙራትን አቅርበዋል። በመቀጠልም በዓሉን የተመለከተ የወንጌል ትምህርት በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ ከተሰጠ በኋላ ደመራው በቀሲስ ተስፋዬ ተባርኮ ተለኩሷል። መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል። በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽኦ ላበረከታችሁ ምዕመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን ዝግጅት በፎቶ ይመልከቱ!

የ፳፻፰ ዓ.ም የፍልሰታ ለማርያም ጾም አጋማሽ ቅዳሴና የአንድ ቀን ጉባኤ ተካሄደ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀ/ስብከት የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ነሐሴ ፯፥፳፻፰ ዓ.ም ከኢትዮጵያ በመጡት ቀሲስ ምንዳዬ ብርሃኑ (ሊቀ መዘምር) የፍልሰታን ጾም በማስመልከት የቅዳሴ መርሐ ግብር የተከናወነ ሲሆን ከቅዳሴው በኋላ በአጥቢያው ሕጻናት አጫጭር መዝሙራት ቀርበዋል። ። በመቀጠልም በቀሲስ ምንዳዬ ዝማሬዎችና ዕለቱን የተመለከተ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል። በመጨረሻም የዕለቱ መርሐ ግብር በአባታችን ቡራኬ ተፈጽሟል።

በነጋታው እሁድ ነሐሴ ፰፥ ዓ.ም ረፋድ ላይ የዕለቱ መርሐ ግብር ኪዳን በማድረስ የተጀመረ ሲሆን በመቀጠልም ቀሲስ ምንዳዬ ተከታታይ ዝማሬዎችን ካቀረቡ በኋላ የዕለቱ የወንጌል ትምህርት በወንድም ኃይሉ (ዶ/ር) ስለጾም አስፈላጊነት ሰፋ ያለ ትምህርት ተሰጥቷል። በስተመጨረሻም በቀሲስ ምንዳዬ የማጠቃለያ ትምህርትና ተጨማሪ ዝማሬዎች ተዘምረው የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተፈጽሟል። በዕለቱ የተገኙት ምዕመናንም ከቀሲስ ምንዳዬ ጋር የማስታወሻ ፎቶ ተነስተው በዕለቱ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀምሰው ወደየቤታቸው በሰላም ተመልሰዋል።

መርሐ ግብሩን በምስል ይመልከቱ !

ልዩ መንፈሳዊ የሕፃናት ቀን በአጥቢያችን በታላቅ ድምቀት ተከበረ

በአይነቱ ልዩ የሆነና ሕጻናትን ያማከለ መርሐ ግብር በአጥቢያችን የቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሄም ሰኔ ፲፪፥ ፳፻፰ ዓ.ም (June 19, 2016) ተካሄደ።

የዕለቱ ዝግጅት በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ሕፃን ሕርያቆስ እና ሕፃን ሊድያ በጋራ በመሆን በጣፋጭ የሕፃን አንደበታቸው አባታችን ሆይ በማድረስ የሕጻናቱ መርሐ ግብር በይፋ የተጀመረ ሲሆን የምሥጢራት ሁሉ መጀመርያ የሆነው ምሥጢረ ሥላሴን ሕፃን ሔርሜላ፣ ሕፃን ማሪያና፣ ሕፃን ቢቲ እና ሕፃን ቲና በመቀባበል በምልልስ መልኩ በዜማ አቅርበዋል። በማስከተልም የዕለቱን ክፍል አንድ ትምህርት ሕፃን ሔርሜላ የአባታችን የኖኅን ታሪክ በመተረክ ስለኃጢያት አስከፊነትና ለእግዚአብሔር ስለመታዘዝ አጠር ያለ ትምህርት አቅርባለች። ከዚያም በመቀጠል ሁሉም ሕፃናት ዓውደ ምህረቱ ላይ “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” እንደተባለ ጣፋጭ ዝማሬዎችን አከታትለው አቅርበዋል።

በክፍል ሁለት ሕፃን ቢቲ በነብዩ ዮናስ ታሪክ ላይ ተመስርታ ስለ እግዚአብሔር መሃሪነት፣ ለፍጥረቱ ያለውን ፍቅር፣ ለእርሱ ስለመታዘዝ አስፈላጊነት የሚያስረዳ ትምህርት አዘል ጽሁፍ አቅርባለች። ቀጣዩ የጥያቄና መልስ መርሐ ግብርም በዓሉን ለመታደም ከላቫንገር ከተማ ለመጡት ሕፃን ዳግማዊ እና ሕፃን ካሌብ ቀርቦ ሕጻናቱ የቀረቡላቸውን ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች በሙሉ በመመለስ ምዕመናንን አስገርመዋል።

በመቀጠልም ለሕፃናት የምሳ ግብዣ ተካሂዶ ለወላጆች በልጆች አስተዳደግ ዙርያ አጠር ያለ ገለጻ ከቀረበ በኋላ በጉዳዩ ላይ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ወላጆች ልምድ በቃለ መጠይቅ መልክ ቀርቧል።

በመጨረሻም በዕለቱ ለተገኙት ሁሉም ሕጻናት ስጦታ ተሰጥቶ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተደምድሟል። ምዕመናንም የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀመሰው በሰላም ወደየቤታቸው ተመልሰዋል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!