የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ግንቦት ፭ እና ፮፥፳፻፰ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፰ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ከኢትዮጵያ ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ዓርብ ግንቦት ፭ እና ቅዳሜ ግንቦት ፮፥፳፻፰ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ዓርብ እለት ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተጀምሮ በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬዎች ከቀረበ በኋላ የወንጌል ትምህርቶች በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ እና በመጋቤ ብሉይ ለማ በእሱፈቃድ በሰፊው የተሰጠ ሲሆን በየመካከሉም በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል። ቀጥሎም ትምህርትና በዓሉን የሚያወድስ ወረብ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እንዲሁም የአጥቢያው መዘምራን እና የቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በተከታታይ ወረብ አቅርበዋል። በመጨረሻም የዓርቡ ጉባዔ በመልአከ ምህረት አባ ዘሚካኤል ደሬሳ ማሳረጊያ ትምህርትና ቡራኬ ተፈጽሟል።

ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማሕሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። በመቀጠልም የነግህ ኪዳንና የቅዳሴው ስርዓት ተጠናቆ በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር ሲቀርብ፤ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል ደግሞ በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግሥ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በአባቶች የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፤ ምእመናኑም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!