የ፳፻፰ ዓ.ም ጰራቅሊጦስ በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የ፳፻፰ ዓ.ም ጰራቅሊጦስ በዓል ሰኔ ፲፩፥፳፻፰ ዓ.ም (June 18, 2016) በቅዳሴ፣ በያሬዳዊ ዝማሬዎችና በስብከት ተከበረ። በዕለቱ ከዴንማርክ የተጋብዙት አባ ዘሚካኤል ዴሬሳ ፣ ከቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ዲያቆናት እንዲሁም በትሮንዳሄምና አካባቢው የሚኖሩ ምእመናን የተገኙ ሲሆን መርሐ ግብሩ ከንጋቱ 12:30 (06:30AM) ሰዓት በጸሎትና በምንባባት ከተጀመረ በኋላ በቅዳሴ መርሃ ግብር እስከ ረፋድ ድረስ ቀጥሏል።

ከቅዳሴ ሥርዓቱ በኋላ ዕለቱን የተመለከቱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች በጋራ ከተዘመሩ በኋላ በአባታችን አባ ዘሚካኤል ቀኑን የተመለከተ ሰፋ ያለ የወንጌል ትምህርትና ምክር ተሰጥቷል። በመጨረሻም የማሳረጊያ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ መርሃ ግብር ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያን የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ እየቀመሰ ወደየቤቱ በሰላም ተመልሷል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ግንቦት ፭ እና ፮፥፳፻፰ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፰ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እና ከኢትዮጵያ ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ዓርብ ግንቦት ፭ እና ቅዳሜ ግንቦት ፮፥፳፻፰ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ዓርብ እለት ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተጀምሮ በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬዎች ከቀረበ በኋላ የወንጌል ትምህርቶች በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ እና በመጋቤ ብሉይ ለማ በእሱፈቃድ በሰፊው የተሰጠ ሲሆን በየመካከሉም በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል። ቀጥሎም ትምህርትና በዓሉን የሚያወድስ ወረብ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እንዲሁም የአጥቢያው መዘምራን እና የቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በተከታታይ ወረብ አቅርበዋል። በመጨረሻም የዓርቡ ጉባዔ በመልአከ ምህረት አባ ዘሚካኤል ደሬሳ ማሳረጊያ ትምህርትና ቡራኬ ተፈጽሟል።

ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማሕሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። በመቀጠልም የነግህ ኪዳንና የቅዳሴው ስርዓት ተጠናቆ በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር ሲቀርብ፤ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል ደግሞ በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግሥ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በአባቶች የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፤ ምእመናኑም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ተከበረ

&nbsp

ክርስቶስ ተንስአ እሙታን…….በዐቢይ ኃይል ወስልጣን

አሰሮ ለሰይጣን ………….አግአዞ ለአዳም

ሰላም…………እምይእዜሰ

ኮነ …………….ፍስሀ ወሰላም

&nbsp

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ተከበረ።

“እም ሐና ወኢያቄም ተወለድኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ – በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” – አባ ሕርያቆስ

ሰማይና ምድርን የፈጠረ፣ ፈጥሮም የሚመግብ ንጉሠ ሰማይ ወምድር የሆነን የእግዚአብሔር ቃል ለመቀበል የተገባት ሆና የተገኘች፣ አምላክን የወለደች የባህርያችን(ሰውነት) መመኪያ የሆነች የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ንጽኅተ ንጹኃን ድንግል ማርያም የልደት በዓል ግንቦት ፩፣ ፳፻፰ዓ.ም. (ሜይ 09፥2016) በአጥቢያችን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ በተዓምረ ማርያም “ሰላም ለኪ ኦ ሐና እማ ለጸሐየ ጽድቅ ወላዲቱ ወምሕየውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ – ጸሐየ ጽድቅ የተባለ ክርስቶስ የምትወልድ እናት እና የጽድቁ ጸሐይ አያት የምትሆኝ ሐና ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ” ተብሎ እንደተመዘገበ የተስፋችን ሁሉ መፈፀሚያ የሆነች እመቤታችንን እና ወላጆቿን ክብር የሚያወሳ ሰፋ ያለ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ መምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማንአየ ተሰጥቷል፤ እመቤታችንን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎችም ተዘምረዋል።

ከመርሐ ግብሩ ፍጻሜ በኋላ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ደጅ ላይ በመሰባሰብ የተዘጋጀው ጸበል ጸዲቅ ከተቀመሰ በኋላ ዝማሬዎች በማኅበር ተዘምረው ምዕመናን ወደየቤታቸው በሰላም ተሸኝተዋል።

“በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት፤ ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ። ስለሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን።” – ቅዱስ ኤፍሬም

ድንግል ሆይ የልደትሽ ቀን በእውነትም የልደታችን ቀን ነው!

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

የጌታችን ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

&nbsp

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

ሞተ ወኬዶ ለሞት

ለእለ ውስተ መቃብር

ወሀበ ሕይወተ ዘለዓለመ ዕረፍተ።

&nbsp

&nbsp

የ፳፻፰ ዓ.ም የጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም በድምቀት ተከበረ። በዓላቱ በአባታችን አባ ገብረ ማርያም ቢምረው እና መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ መሪነት እና በርካታ ቁጥር ባለው ምእመን ሱታፌ በተለያዩ አገልግሎቶች ተከብረዋል።

ዕለተ አርብ ሚያዝያ ፳፩፥፳፻፰ ዓ.ም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታችንን ስቅለት በሚያወሱ ምንባባት፣ ሕማሙን በሚዘክሩ ጸሎቶች እንዲሁም በስግደት ያለፈ ሲሆን፤ “አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል” እንደተባለ የጌታችንን ረቂቅ የማዳን ሥራ እና ነገረ-መስቀሉን በተመለከተ በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ትምህርት ተሰጥቷል።

ቅዳሜ ማለዳ ለቀዳም ስዑር እለት የሚደረጉት ጸሎትና ምንባባት ከተከናወኑ በኋላ ቀኑን የተመለከተ አጠር ያለ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ተሰጥቶ የማለዳው መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።

ቅዳሜ ምሽት ከ 22:00 ሰዓት ጀምሮ የጌታችንን ትንሳዔ የሚያወድስ ሥርዓት ከምንባባትና ወረቦች ጋር ከተከናወነ በኋላ በኪዳንና በሥርዓተ ቅዳሴ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን የጾም መፈሰኪያ ጸበል ጸዲቅ እየቀመሰ ወደየቤቱ በሰላም ተመልሷል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሔም የሆሳዕና በዓል በድምቀት ተከበረ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የሆሳዕና በዓል በጸሎት፣ በስብከተ ወንጌል እና በያሬዳዊ ዝማሬዎች እጅግ በርካታ የትሮንዳሔምና የአካባቢው ምዕመናን በተገኙበት በድምቀት ተከበረ።

በዕለቱ “እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ/ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” (መዝ. ፰፥፪) ተብሎ እንደተጻፈ የቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ የሆኑት ሕፃናት እና ታዳጊዎች በጣፈጠ አንደበታቸው በዓሉን የሚያወሱ ዝማሬዎችን አቅርበዋል። በመቀጠልም እለቱን የተመለከተ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተደምድሟል።

በመጨረሻም መርሐ ግብሩን የተሳተፈው ማኅበረ ምእመን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ለበረከት እየቀመሰ በሰላም ወደ ቤቱ ተሸኝቷል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓም የደብረ ዘይት በዓልን በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌል እና በያሬዳዊ ዝማሬ ከስቶክሆልም ስዊድን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ ካሣዬን በመጋበዝ፤ በትሮንዳሄምና አካባቢው የሚገኙ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን በተገኙበት በዓሉ በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ በመካከለኛው አውሮፓ የስዓት አቆጣጠር ከንጋቱ 06:00 ሰዓት በጸሎት ተጀምሮ በዓሉን የሚያወሱ ከቅዱሳት መጽሃፍት በመነበብ የኪዳንና የቅዳሴ መርሃ ግብር ተካሂዷል። ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ እለቱን የተመለከቱ የንስሃ መዝሙራት በአጥቢያው መዘምራን ቀርቧል። በመቀጠልም የደብረ ዘይት በዓልን በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት በመልአከ ብርሃን አባ ገብረ ጊዮርጊስ ቀረቦ የእለቱ መርሐ ግብር በአባታችን የማሳረጊያ ጸሎት ተፈጽሟል።

በመጨረሻም በመርሃ ግብሩ የተሳተፈው ምእመናን ወ ምእመናት ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ለበረከት እየቀመሰ በሰላም ወደ ቤቱ ተሸኝቷል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል

TSGC-KibreBealMastawekia 7በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
 
የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል ግንቦት ፭ እና ፮ በትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ይከበራል።
የ፳፻፰ ዓ.ም. የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የንግስ ክብረ በዓል ከጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ ጋር በመግጠሙ ከአባቶች ጋር በመነጋገር በተወሰነው መሰረት ክብረ በዓሉ ዓርብ ግንቦት ፭ እና ቅዳሜ ግንቦት ፮ ፣ ፳፻፰ ዓ.ም. ለማክበር ታቅዷል። 
በበዓሉ ላይ በርካታ የቤተክርስቲያን አባቶች ከተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት እና ከሀገረ ኖርዌይ እንዲሁም መጋቤ ሐዲስ ምስጢረ ሥላሴ ማናዬ ከኢትዮጵያ እንደሚገኙ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ከመላው ኖርዌይ በሚሰባሰቡ ምዕመናን፣ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አባላት እና የቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች/ወንድሞች/እህቶች በተገኙበት በአንድነት በዓሉ በትሮንዳሔም በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፤ አሜን።

የ፳፻፰ ዓ.ም የልደት በዓል በድምቀት ተከበረ

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም አጥቢያ በሚገኙ ምእመናን በደመቀ ሥርዓት በቅዳሴ፣ በዝማሬና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተከብሮ ዋለ።

እሁድ ጥር ፩፥፳፻፰ በተጋበዙ አባቶችና ዲያቆናት በኪዳንና ቅዳሴ የተጀመረው መርሐ ግብር በአጥቢያው መዘምራን በዓሉን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች በማቅረብ የቀጠለ ሲሆን በመጨረሻም የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በአባቶች ተሰጥቶ ቅዳሴው ተፈጽሟል። ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

ቤተ ክርስቲያናችን መንበረ ፕትርክናው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር በአስተዳደራዊ መዋቅር መታቀፏን ስለማሳዎቅ

letter1 107x151ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪኩ እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ትሮንዳሄም፣ ኖርዌይ በመጡ ቀናኢ የቤተክርስቲያን ልጆች አማካኝነት በሰንበት ትምህርት ቤትነት ደረጃ በመቋቋም ነበር። ሰንበት ት/ቤት በነበረበት ወቅት እ.ኤ.አ በ2010 ህጋዊ ሆኖ በኖርዌይ ሀገር በሃይማኖት ተቋምነት የተመዘገበ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመባል እ.ኤ.አ በ2012 በአቅራቢያው እየመጡ በሚያገለግሉን አባቶች ተሰይሟል። እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ በአባቶች ተባርኮ መጥቶ ከሰንበት ትምህርት ቤትነት ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንነት በማደግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመስርቷል። በዚህ ጉዞዋ ቤተ ክስቲያናችን በዚህ መዋቅር ነኝ ብላ ባታውጅም፤ ከአባቶቻችን እንደተማርነው ያለመዋቅርና ያለስርዓት መጓዝ ጥሩና አግባብ ባለመሆኑ /መዝ. ፻፲፰፥፻፲፰ ፡ ፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፬ ፡ ፪ኛ ተሰ. ፫፥፮/ አጥቢያችን በአስተዳደራዊ መዋቅር ስር ገብታ ትተዳደር ዘንድ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናዊና ሀይማኖታዊ ህግ መሆኑ ግልጽ ነው። ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ይህን ሃይማኖታዊ ስርዓት ሰፊ ጊዜ በመውሰድ የተወያየበት ሲሆን ከአባቶችም ጋር እንደዚሁ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ምዕመናን በጉዳዩ ዙርያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ይህን አጀንዳ በሃይማኖትና በእምነት መነጸር ብቻ እንዲመለከቱት የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እና ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ህግ ይሆን ዘንድ ባወጣው ቃለ ዓዋዲ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ጥረት ተደርጓል።

 

ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ህግ አንፃር፣ እንዲሁም ይህች ቤተ ክርስቲያናችን ስትመሰረት ታቦተ ህጋችን በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ከሀገር ቤት እንደመምጣቱ መጠን፤ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ነገሮችን በእርጋታ ተመልክቶ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስር እንድትሆን አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባራውነቱ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም መሰረት በጉዳይ ላይ ከምዕመኑ ጋር ለመነጋገር ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ኅዳር ፳፭፥ ፳፻፰ ዓ.ም ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በትሮንዳሔም የቤተ ክርስትያን መዋቅርና የቤተ ክርስቲያኗን የበላይ ጠባቂ በግልጽ ስለ ማሳወቅ በሚል ርዕስ አባቶች በተገኙበት አወያይቷል። በዕለቱም ስለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲሁም ስለቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በትሮንዳሔም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ጉዳይ ገለፃ ተሰጥቶ ግልፅ ውይይት ተደርጓል። ጠቅላላ ጉባኤውም የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፕትርክናው ኢትዮጵያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ቤተ ክርስቲያናዊ መዋቅርን ጠብቃና አክብራ መተዳደር አለባት በማለት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል።

 

 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መዋቅር ስር መሆናችንን ስለማሳወቅ ለብጹዕ አቡነ እንጦንስ ለሰ/ሰ/ምዕ/ አውሮፓ ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተጻፈ ደብዳቤ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሄም ተከታታይ መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት፤ ህዳር 18-19/2008ዓ.ም (November 28-29, 2015) እና ህዳር 25-26/ 2008ዓ.ም (December 05-06/2015) ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤ በትሮንዳሄምና በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን በተገኙበት ተካሄደ። በጉባኤው መጀመርያ ቀን ቅዳሜ ህዳር 18 በአባታችን መልዓከ ሃይል መምህር አባ ዘድንግል (በጣልያን ባሪ ከተማበሚገኘው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ) እና በዲ/ን ዶ/ር አለማየሁ በጸሎተ ኪዳን ተጀምሯል። በእለቱም በዲ/ን ዶ/ር አለማየሁ እና በአባታችን በአባ ዘድንግል ትምህርተ ወንጌል ሰፋ ባለ መልኩተሰጥቷል። እንዲሁም በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙራት ከቀረቡ በኋላ የእለቱን መርሃ ግብር አባታችን በጸሎት አሳርገው ጉባኤው ተጠናቋል።

 ጉባኤው በመቀጠል እሁድ፣ ህዳር 19 በጠዋቱ የቅዳሴ ስርዓት ከተከናወነ በኋላ በአባታችን አባ ዘድንግል ሰፋ ያለ ትምህርት ተሰጥቶ የዕለቱ ጉባኤ ፍጻሜ ሆኗል።

 በቀጣዩ ሳምንት፤ ቅዳሜ ህዳር 25 ጠዋት ጸሎተ ኪዳን ደርሶ ከሰዓት በኋላ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ያተኮረ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል። የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤው ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ታሪክና በመዋቅር ስር መሆናችን ለቤተ ክርስቲያናችን ያለውን አስፈላጊነት እንዲሁም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዴት እንደሚታይ አጠር ያለ ማብራሪያ ለምዕመናን በመግለጽ ሰፊ ውይይት እንዲካሄድ ተደርጓል። በተነሱ ጥያቄዎችም ላይ በአባታችን መልዓከ ሃይል አባ ዘድንግል እና በወንድማችን ዲ/ን ሰሎሞን ገብረሚካኤል ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንንና ቃለ ዓዋዲን መሰረት አድርጎ ለጠቅላላ ጉባኤው በዝርዝር ግንዛቤ ተሰጥቷል። ከዚህም በመነሳት አንዲት፣ ቅድስትና ሐዋርያዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችን በመዋቅር ታቅፋ ትተዳደር ዘንድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስርእንድትሆን በማለት ጠቅላላ ጉባኤው ወስኗል።

  በጉባኤው መጨረሻም ቀን ዕሁድ ጠዋት ስርዓተ ቅዳሴ ተከናውኖ በአባ ዘድንግል የወንጌል ትምህርት እንዲሁም በዲ/ንሰሎሞን ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ መርሃ ግብሩ በጸሎት ተፈጽሟል።

የጉባዔውን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!