ልዩ መንፈሳዊ የሕፃናት ቀን በአጥቢያችን በታላቅ ድምቀት ተከበረ

በአይነቱ ልዩ የሆነና ሕጻናትን ያማከለ መርሐ ግብር በአጥቢያችን የቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሄም ሰኔ ፲፪፥ ፳፻፰ ዓ.ም (June 19, 2016) ተካሄደ።

የዕለቱ ዝግጅት በጸሎት ከተጀመረ በኋላ ሕፃን ሕርያቆስ እና ሕፃን ሊድያ በጋራ በመሆን በጣፋጭ የሕፃን አንደበታቸው አባታችን ሆይ በማድረስ የሕጻናቱ መርሐ ግብር በይፋ የተጀመረ ሲሆን የምሥጢራት ሁሉ መጀመርያ የሆነው ምሥጢረ ሥላሴን ሕፃን ሔርሜላ፣ ሕፃን ማሪያና፣ ሕፃን ቢቲ እና ሕፃን ቲና በመቀባበል በምልልስ መልኩ በዜማ አቅርበዋል። በማስከተልም የዕለቱን ክፍል አንድ ትምህርት ሕፃን ሔርሜላ የአባታችን የኖኅን ታሪክ በመተረክ ስለኃጢያት አስከፊነትና ለእግዚአብሔር ስለመታዘዝ አጠር ያለ ትምህርት አቅርባለች። ከዚያም በመቀጠል ሁሉም ሕፃናት ዓውደ ምህረቱ ላይ “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” እንደተባለ ጣፋጭ ዝማሬዎችን አከታትለው አቅርበዋል።

በክፍል ሁለት ሕፃን ቢቲ በነብዩ ዮናስ ታሪክ ላይ ተመስርታ ስለ እግዚአብሔር መሃሪነት፣ ለፍጥረቱ ያለውን ፍቅር፣ ለእርሱ ስለመታዘዝ አስፈላጊነት የሚያስረዳ ትምህርት አዘል ጽሁፍ አቅርባለች። ቀጣዩ የጥያቄና መልስ መርሐ ግብርም በዓሉን ለመታደም ከላቫንገር ከተማ ለመጡት ሕፃን ዳግማዊ እና ሕፃን ካሌብ ቀርቦ ሕጻናቱ የቀረቡላቸውን ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች በሙሉ በመመለስ ምዕመናንን አስገርመዋል።

በመቀጠልም ለሕፃናት የምሳ ግብዣ ተካሂዶ ለወላጆች በልጆች አስተዳደግ ዙርያ አጠር ያለ ገለጻ ከቀረበ በኋላ በጉዳዩ ላይ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ወላጆች ልምድ በቃለ መጠይቅ መልክ ቀርቧል።

በመጨረሻም በዕለቱ ለተገኙት ሁሉም ሕጻናት ስጦታ ተሰጥቶ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተደምድሟል። ምዕመናንም የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀመሰው በሰላም ወደየቤታቸው ተመልሰዋል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!