ዘመነ ስብከት

ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ስብከት: የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ‹‹ስብከት›› ይባላል፡፡ በዚህ ቀንም በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያትም አስቀድሞ ስለ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ትንቢት ተነግሮ፣ ምሳሌ ተመስሎ፣ ሱባዔ ተቆጥሮ እንደ ነበር ይነገራል፤ ይሰበካልም፡፡

እምኦሪተ ሙሴ እስከ ነቢያት ሰበኩ ምጽአቶ ንህነ ነአምን ስብከቶ ፣ ከኦሪተ ሙሴ አንስቶ እስከ ነቢያት የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት ሰበኩ አስተማሩ እኛም ሙሴና ነቢያት የሰበኩት ስብከት አምነን እንቀበላለን ፣እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ )

ቅዱሳን ነቢያቱ አስቀድመው መምጣቱን ሰብከው ስለነበር ያንን ለማሰብ ይህ ዕለት ‹‹ስብከት›› ይባላል፣ ስብከት ማለት ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከአብርሃም እስከ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡

የነቢያት ስብከት: በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደ ጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል (ዮሐ 1፡44)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ፈኑ እዴከ እም አርያም » እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም› (መዝ 143፡7) በማለት ስለክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡ ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› (ኢሳ 64፡1) ብሎ ስለክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ፣ ከድንግል ማርያምም መወለድ የተናገረውን ትንቢት ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡

የቤተክርስቲያናችን ስብከት: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (2ኛ ቆሮ 4፡5) እንዳለው ቤተክርስቲያን በተለይ በዘመነ ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠውንና የፈጸመውን የማዳን ተስፋ ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ “ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን” እንዳለ ቤተክርስቲያናችን ፣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ በችግርም በደስታም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና አምላክ ወልደ አምላክ ክርስቶስን ትሰብካለች፤

አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን በረከየተ ያድለን፣ አሜን።