• ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

  • "ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት" መዝ 150፥5

ዜናዎች እና ወቅታዊ ክንውኖች

የደብረ ታቦር በዓል እና ጾመ ፍልሰታን ምክንያት በማድረግ ጉባኤ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም የደብረ ታቦር በዓልና ጾመ ፍልሰታን ምክንያት በማድረግ ለ፪ ቀናት ማለትም ነሐሴ ፳፫ እና ፳፬ ፳፻፮ ዓ.ም የአካባቢው ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሄደ። በጉባኤውም ላይ መላከ ጽዮን ቆሞስ አባ ሙሴ በመገኘት የስብከተ ወንጌል አገልግሎትና ስርዓተ ቅዳሴ እንዲከናወን በማድረግ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል። ጉባኤውን በፎቶ ይመልከቱ

የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ ከነሐሴ ፪ እስከ ፬ ፳፻፮ ዓ.ም መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሄደ። በጉባኤውም ላይ በአካባቢው ለሚኖሩ ምእመናንና ምእመናት የሦስት ቀን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተካፋይ እንዲሆኑ ተደርጓል። ጉባኤውም በስርዓተ ጸሎት ተጀምሮ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ በጸሎት ተጠናቋል። ጉባኤውን በፎቶ ይመልከቱ

የ፳፻፮ ዓ.ም. የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ መልኩ ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር የ፳፻፮ ዓ.ም. የዳግም ትንሣኤንና የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናን እና ምእመናት በተገኙበት ዓርብ ሚያዚያ ፲፯ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፲፰ በታላቅ ድምቀት አከበረ። በዓሉ በማሕሌት፣ በቅዳሴ፣ በትምህርተ ወንጌልና በመዝሙር የተከበረ ሲሆን ያሬዳዊ ዝማሬም በደብሩ መዘምራን ቀርቧል። በተጨማሪም የላቫንጋርና […]

የ፳፻፮ ዓ.ም. የስቅለትና የትንሣኤ በዓላት አከባበር

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለትና በዓለ ትንሣኤ በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም አጥቢያ በሚገኙ ምእመናን እና ምእመናት በዕለቱ ተከብሮ ዋለ። የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

የ፳፻፮ ዓ.ም. ደብረዘይት በዓል በደመቀ መልኩ ተከበረ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረዘይት በዓልን ከመጋቢት ፲፪ እስከ ፲፫፣ ፳፻፮ ዓ.ም. ከተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ከመጡ አባቶች ካህናት እና ወንድሞች ዲያቆናት እንዲሁም በአካባቢው ከሚኖሩ ምእመናንና ምእመናትጋር በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌልና በያሬዳዊ ዝማሬ በታላቅ ድምቀት አከበረ። የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

በፌስቡክ ያግኙን

የአስተዳዳሪው መልእክት

ያለ ሥርዓት አልሄድንም  (2ኛ ተሰ 3÷7)

ማንኛውም ፍጡር በተፈጥሮ የተሰጠው ሕግና ሥርዓት አለው ይልቁንም ሰው የተፈጠረውና የሚኖረው ሲመራም የኖረበት ሥርዓት አለው። አፈጻጸማቸውና አጠቃቀማቸው ስለ ሥርዓትም ያላቸው ግንዛቤና የሚሰጡት ዋጋ የተለያየ ይሁን እንጅ በዓለም ላይ ያሉ የእምነት ተቋማት ሁሉ ያለ ሥርዓት መቆም መኖር መገኘት አልቻሉም አይችሉምም ።

እያንዳንዱ የእምነት ተቋም በሕግና በሥርዓት የመኖሩ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም የአይሁድ እምነት ሥርዓትና ወግ ባህል ትውፊት ልዩ ቦታ የሚሰጠው በሰዎች ዘንድ ሁሉ የታወቀ ነበር ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስትናው ሲመሠረትም ራሱን የቻለ የታወቀ ሕግና ሥርዓት አፈጻጸም ያለው ሆኖ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ (1ኛ ቆሮ 14÷40) ላይ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ብሏል ይህም ማለት የአማንያኑ የእምነት አፈጻጸም ሕግና ሥርዓት ያለው መሆን እንዳለበትና በአግባቡ መፈጸም እንዳለበት ያስረዳናል ።

ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚከናወንበት ሥርአት አለው ካህናቱ ሥርዓተ አምልኮውን (አግልግሎቱን) ሲፈጽሙ በሥርዓትና በአግባቡ መሆን እንዳለበት ምእመናኑም ለማገልገልም ሆነ ለመገልገል ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዘንድ ልዩ የሚሆነው ጉዳይ ይኸ ሥርዓት አግባብ አለው ውይስ የለውም የሚለው ነው የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ስለ ሥርዓት እንኳን ያላቸው ግንዛቤ ከዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ እያየን ነው። በዚህም ምክንያት እምነት በየጊዜው የሚለዋወጥ የተበከለ የተመረዘ ሕግንና ሥርዓትን ያልጠበቀ የቀደሙ አበው የሐዋርያት የሊቃውንትን አሰረ ፍኖት ያልተከተለ መሥመር የለቀቀ ሆኖ ይገኛል።

ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ተሰ 2÷15 ላይ “አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን ያስተማርናችሁንና የሠራንላችሁን ሥርዓት ያዙ” በማለት አስረግጦ አስተምሮናል ስለሆነም ሥርአት ምንድን ነው ስንል በተፈጥሮ የተገኘና ፍጡራን በየጊዜው በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚፈጽሙት የእምነት ቀኖናቸውን የሚጠብቁበት እራሳቸውን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት የሚያስተካክሉበት የሚገዙበት ስህተታቸውን የሚያርሙበት ድርጊት ነው ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ሕይወት ላላቸው እንስሳትም ሆነ ለሰማያውያን መላክት ጭምር በየድርሻቸው የተሠራና እስከ ምጽአት ድረስ የሚሠራ ነው።

በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳት ሁሉ ታጠግባለህ(መዝ 144÷16) ይሁን እንጅ ሥርዓትን ለመማር ሥርዓትን ለማወቅ ሥርዓትን ለመሥራት መጀመሪያውና ቀዳሚው ተግባር መጻሕፍትን ማንበብና መምህራንን መጠየቅ በዕውቀት ሙሉ ሆኖ መገኘት ሲሆን እነዚህንም ተግባራት ለማከናወን ይረዳን ዘንድ የደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም ይህን ድረ ገጽ ሲያዘጋጅ ምእመናን የሚሰጠውን ትምህርት የሚተላለፈውን መልእክት አንብበው በትምህርቱ እራሳቸውን በዕውቀት ለማጠንከርና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ለመኖር የሚረዳቸውን ዕውቀት የሚገበዩበት መንፈሳዊ የነፃ ገበያ እንዲሆን ታስቦ ነው። ስለሆነም የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ምግብ በነፃ በመሸመት የመንፈሳዊ ሕይወት ረሀብ የያዛችሁ በድርቅ የተመታችሁ ሁሉ እንድታገግሙበት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች።

መጋቤ ብሉይ አባ ቀለመወርቅ አቡኔ
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ

መንፈሳዊ አገልግሎት

የሰንበት ት/ቤት እና ህጻናት አገልግሎት

ያግኙን