ዜናዎች እና ወቅታዊ ክንውኖች
ያለ ሥርዓት አልሄድንም (2ኛ ተሰ 3÷7)
ማንኛውም ፍጡር በተፈጥሮ የተሰጠው ሕግና ሥርዓት አለው ይልቁንም ሰው የተፈጠረውና የሚኖረው ሲመራም የኖረበት ሥርዓት አለው። አፈጻጸማቸውና አጠቃቀማቸው ስለ ሥርዓትም ያላቸው ግንዛቤና የሚሰጡት ዋጋ የተለያየ ይሁን እንጅ በዓለም ላይ ያሉ የእምነት ተቋማት ሁሉ ያለ ሥርዓት መቆም መኖር መገኘት አልቻሉም አይችሉምም ።
እያንዳንዱ የእምነት ተቋም በሕግና በሥርዓት የመኖሩ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም የአይሁድ እምነት ሥርዓትና ወግ ባህል ትውፊት ልዩ ቦታ የሚሰጠው በሰዎች ዘንድ ሁሉ የታወቀ ነበር ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስትናው ሲመሠረትም ራሱን የቻለ የታወቀ ሕግና ሥርዓት አፈጻጸም ያለው ሆኖ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ (1ኛ ቆሮ 14÷40) ላይ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ብሏል ይህም ማለት የአማንያኑ የእምነት አፈጻጸም ሕግና ሥርዓት ያለው መሆን እንዳለበትና በአግባቡ መፈጸም እንዳለበት ያስረዳናል ።
ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚከናወንበት ሥርአት አለው ካህናቱ ሥርዓተ አምልኮውን (አግልግሎቱን) ሲፈጽሙ በሥርዓትና በአግባቡ መሆን እንዳለበት ምእመናኑም ለማገልገልም ሆነ ለመገልገል ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዘንድ ልዩ የሚሆነው ጉዳይ ይኸ ሥርዓት አግባብ አለው ውይስ የለውም የሚለው ነው የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ስለ ሥርዓት እንኳን ያላቸው ግንዛቤ ከዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ እያየን ነው። በዚህም ምክንያት እምነት በየጊዜው የሚለዋወጥ የተበከለ የተመረዘ ሕግንና ሥርዓትን ያልጠበቀ የቀደሙ አበው የሐዋርያት የሊቃውንትን አሰረ ፍኖት ያልተከተለ መሥመር የለቀቀ ሆኖ ይገኛል።
ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ተሰ 2÷15 ላይ “አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን ያስተማርናችሁንና የሠራንላችሁን ሥርዓት ያዙ” በማለት አስረግጦ አስተምሮናል ስለሆነም ሥርአት ምንድን ነው ስንል በተፈጥሮ የተገኘና ፍጡራን በየጊዜው በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚፈጽሙት የእምነት ቀኖናቸውን የሚጠብቁበት እራሳቸውን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት የሚያስተካክሉበት የሚገዙበት ስህተታቸውን የሚያርሙበት ድርጊት ነው ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ሕይወት ላላቸው እንስሳትም ሆነ ለሰማያውያን መላክት ጭምር በየድርሻቸው የተሠራና እስከ ምጽአት ድረስ የሚሠራ ነው።
በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳት ሁሉ ታጠግባለህ(መዝ 144÷16) ይሁን እንጅ ሥርዓትን ለመማር ሥርዓትን ለማወቅ ሥርዓትን ለመሥራት መጀመሪያውና ቀዳሚው ተግባር መጻሕፍትን ማንበብና መምህራንን መጠየቅ በዕውቀት ሙሉ ሆኖ መገኘት ሲሆን እነዚህንም ተግባራት ለማከናወን ይረዳን ዘንድ የደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም ይህን ድረ ገጽ ሲያዘጋጅ ምእመናን የሚሰጠውን ትምህርት የሚተላለፈውን መልእክት አንብበው በትምህርቱ እራሳቸውን በዕውቀት ለማጠንከርና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ለመኖር የሚረዳቸውን ዕውቀት የሚገበዩበት መንፈሳዊ የነፃ ገበያ እንዲሆን ታስቦ ነው። ስለሆነም የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ምግብ በነፃ በመሸመት የመንፈሳዊ ሕይወት ረሀብ የያዛችሁ በድርቅ የተመታችሁ ሁሉ እንድታገግሙበት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች።
መጋቤ ብሉይ አባ ቀለመወርቅ አቡኔ
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ
ብርሃን
የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ብርሃን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡
ዘመነ ስብከት
ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡
አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ
የተወደዳችሁ በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ምእመናን ወምእመናት እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን !!
ኅዳር 7 የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል በትሮንድሃይም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ።
ኅዳር 7 ቀን በቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገር በልዳ በስሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተክርስቲያን የታነፀበት ዕለት ነው። ይህ ታላቅ በዓል በትሮንድሃይም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማኅሌት፣ በቅዳሴ እና ፣ በዝማሬ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።
እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።
«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል”
(ቅዱስ ያሬድ)
እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!
በዛሬው ዕለት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ የቅድስት ኢየሉጣ አመታዊ ክብረ በዓል ነው።
በዚህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸው ታሪክ ይናገራል።