• ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

  • "ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት፤ እልልታ ባለው ጸናጽል አመስግኑት" መዝ 150፥5

የ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መልእክት

“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት” ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2ጢሞ 3÷1

+ + +

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለ2012 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ በሰላም በጤና አሸጋገረን አሸጋገራችሁ ።

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ሲቆጠር 7512 ዓ/ዓ ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ከወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ከተወለደ ደግሞ 2012 ዓ/ም ይሆናል ።

ማይክሮ – ሰከንዶች – ሰከንዶችን – ሰከንዶች ሰዓታትን – ሰዓታት – ቀናትን – ቀናት-ሳምንታትን – ሳምንታት – ወራትን- ወራት- ዓመታትን እየወለዱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር 64÷12 ላይ ” ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ” ዓመታትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ (አንድም) የምሕረት አመታትን በቸርነትህ ለሰዎች ታድላለህ ብሎ እንደተናገረ እየተፈራረቁ ዘመናት በዘመናት እየተተኩ ዛሬ ካለንባት ጊዜና ዘመን ደርሰናል ።

ነገር ግን አባቶቻችን ዘመንን የሚቆጥሩት በሕይወት የኖሩበትን ዘመን ነበር እኛ ደግሞ ዛሬ ዘመን በሕይወት የምንኖርበት ሳይሆን በሥጋ የምንኖርበት ብቻ ሁኗል የሰዎች የክፋትም ሆነ የደግነት፣ የመልካም ሥራም ሆነ የክፉ ሥራ ውጤት በዘመን ይገለጣል ለዚህ ነው ሐዋርያው በመጨረሻው ዘመን ያለው እንደ እድል ሆኖ የኛ ዘመን ከመልካም ይልቅ ክፋት የበዛበት ከእውነት ይልቅ ውሸት የሚታመንበት ከፍቅር ይልቅ ጸብ የሚወደድበት ከሰላም ይልቅ ሁከት የሚፈለግበት ከምሕረት ይልቅ መዓት የሚሰማበት ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአት የነገሠበት ከመረዳዳት ይልቅ መገፋፋት የሚቀናበት ከመተሳሰብ ይልቅ መረሳሳት የተለመደበት ከማመስገን ይልቅ መካሰስ የበዛበት ከትእግሥት ይልቅ ቁጣ የፈጠነበት ከትሕትና ይልቅ ትእቢት ከሥራ ይልቅ ስርቆት የሞላበት የመከራው ዘመን ነው ።

ዓለም እንደፈለገ የሚጋልብበት የውድድር ሜዳ አጥር ቅጥሩ የፈረሰበት ዘመን እየሆነ መጥቷል እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ለተፈጠርንለት አላማ ሳይሆን በራሳችን አዙሪት እየተሽከረከርን መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል ጥንቱን ሰው የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነበር እሱም እንደ መላእክት ያለዕረፍታና ያለመታከት ያለድካም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ዓለም ግን መሥመር እየሳተ አቅጣጫ እየቀየረ መንገድ እየለቀቀ ነው ።

ይህንን ነበር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “የሚአስጨንቅ ዘመን እንዲመጣይህንን እወቅ ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ” ብሎ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን በዝርዝ የነገረው ።  ቅዱስ ጳውሎስ ወረድ ብሎ ከቁጥር 14 ላይ እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ቃል መሠረት በማድረግ እንደ ደቀ መዝሙሩ እንደ ጢሞቴዎስ ታዛዦች በመሆን አዲሱና የሚመጣው ዓመት እኛ ተለውጠን ሌሎችን የምንለውጥበት እኛ ከብረን የምናከብርበት ሰርተን ዋጋ የምናገኝበት ያለፈውን ድክመታችንን የምናስተካክልበት ባለፈው ያባከነውን ጊዜ ሐዋርያው ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ እንዳለ በቁጭት የምናስብበት ያስቀየምነውን ይቅርታ የምንጠይቅበት የቀማነውን የምንመልስበት ያጣነውን ሕይወታችንን ፈልገን የምናገኝበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የምንመለስበት ንስሐ ገብተን ባጠፋነው ክሰን የምንችል ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት የማንችል ሁሉን ወደሚችል አምላክ እንዲያስችለንና ለሥጋው ለደሙ እንዲያበቃን በጽኑ እምነት በቁርጥ ኅሊና በጠነከረ ልብ በበረታ ጉልበት ለጾም ለጸሎት የምንዘጋጅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ እንዲአደርግልንም ተግቸ እጸልያለሁ ።

እናንተም እንደ ጢሞቴዎስ በተማራችሁበትና በተረዳችሁበት ነገር ጸንታችሁ እንድትኖሩ አደራ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።

መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመወርቅ

ቤተ ክርስቲያናችን መንበረ ፕትርክናው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር በአስተዳደራዊ መዋቅር መታቀፏን ስለማሳዎቅ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪኩ እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ትሮንዳሄም፣ ኖርዌይ በመጡ ቀናኢ የቤተክርስቲያን ልጆች አማካኝነት በሰንበት ትምህርት ቤትነት ደረጃ በመቋቋም ነበር። ሰንበት ት/ቤት በነበረበት ወቅት እ.ኤ.አ በ2010 ህጋዊ ሆኖ በኖርዌይ ሀገር በሃይማኖት ተቋምነት የተመዘገበ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመባል እ.ኤ.አ በ2012 በአቅራቢያው እየመጡ በሚያገለግሉን አባቶች ተሰይሟል። እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ ታቦተ […]

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሄም ተከታታይ መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት፤ ህዳር 18-19/2008ዓ.ም (November 28-29, 2015) እና ህዳር 25-26/ 2008ዓ.ም (December 05-06/2015) ልዩ መንፈሳዊ ጉባኤ በትሮንዳሄምና በአካባቢው የሚገኙ ምዕመናን በተገኙበት ተካሄደ። በጉባኤው መጀመርያ ቀን ቅዳሜ ህዳር 18 በአባታችን መልዓከ ሃይል መምህር አባ ዘድንግል (በጣልያን ባሪ ከተማበሚገኘው በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ) እና በዲ/ን ዶ/ር […]

የ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የ ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመጡ ካህናት እና መዘምራን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ በርካታ ምእመናን እሁድ መስከረም ፲፮ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። በዓሉ እሁድ እለት ከሰዓት በኋላ በካህናት አባቶች ጸሎት የተጀመረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ […]

የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባዔ ተካሄደ፤ የ፳፻፰ ዓ.ም ቅዱስ ዮሐንስ በዓልም በድምቀት ተከበረ

በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። መዝ ፷፭፥፲፩ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። የቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በትሮንዳሔም ከጷግሜ ፮፥፳፻፯ ዓ.ም እስከ መስከረም ፪፥፳፻፰ ዓ.ም ለሦስት ተከታታይ ቀናት የቆየ መንፈሳዊ ጉባኤና የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ከኢትዮጵያ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ተጋብዘው ወደ አውሮፓ በመጡት መምህር (ቀሲስ) […]

የሊቀ ሰማዕታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ መልኩ ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፣ ፳፻፯ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ ምእመናን ዓርብ ሚያዚያ ፳፫ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፬ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። በዓሉ ዓርብ እለት ከሰዓት በኋላ በጸሎት […]

በትሮንዳሄም የ፳፻፯ ዓ.ም. የስቅለትና የትንሣኤ በዓላት አከባበር

ክርስቶስ ተንስአ እሙታን…….በዐብይ ኃይል ወስልጣን አሰሮ ለሰይጣን ………….አግአዞ ለአዳም ሰላም…………እምይእዜሰ ኮነ …………….ፍስሀ ወሰላም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ስቅለትና ትንሣኤ በትሮንዳሄም ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከበረ። ዕለታቱን በአባ ገብረ ማሪያም ቢምረው እና በቀሲስ ካሳዬ አንተነህ የትሮንዳሄም አጥቢያና አካባቢው ምእመናን በተገኙበት ዓርብ ስቅለትን በስግደት እንዲሁም ቅዳሜ ሌሊት ደግሞ የትንሣኤን በዓል በቅዳሴ፣ በወረብና […]

በትሮንዳሄም የሆሳዕና በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሄም የሆሳዕና በዓል መጋቢት ፳፯፥፳፻፯ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ። መርሃ ግብሩ በጸሎት ተጀምሮ በህጻናትና በአጥቢያው መዘምራን በዓሉን የተመለከተ ያሬዳዊ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌል በቀሲስ ወንድወሰን ተሰጥቷል።በመጨረሻም ቀጣዩ ሳምንት “ሰሙነ ህማማት” በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ስርዓት መሠረት ለምእመናን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጎ የዕለቱ መርሃ ግብር በጸሎት ተፈጽሟል፡፡ የበዓሉን አከባበር በፎቶ […]

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓል በድምቀት ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የደብረ ዘይት በዓልን ከመጋቢት ፭ እስከ ፮፥ ፳፻፯ ዓ.ም. ከተለያዩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት በመጡ አባቶች ካህናት እና ወንድሞች ዲያቆናት እንዲሁም በአካባቢው ከሚኖሩ ምእመናን ጋር በቅዳሴ፣ በስብከተ ወንጌልና በያሬዳዊ ዝማሬ በድምቀት ተከብሯል። በዚህ በዓል ላይ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ዓመታዊ የእረፍት ቀንም ታስቦ ውሏል። በበዓሉም ላይ በመልዓከ ጽዮን […]

የ፳፻፯ ዓ.ም. የልደት በዓል አከባበር

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም አጥቢያ በሚገኙ ምእመናን እና ምእመናት በዓሉ በቅዳሴ፣ በዝማሬና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተከብሮ ዋለ። የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ

በትሮንዳሔም የ ፩ ቀን ጉባኤ ተካሄደ

ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ተጋብዘው ኖርዌይ በመጡት በዘማሪ ዲያቆን እንግዳወርቅ በቀለ እሁድ ህዳር ፳፰ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም በትሮንዳሔምና አካባቢው ለሚገኙ ምእመናን ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዝሙርና ስብከተ ወንጌልን ያካተተ ጉባኤ አካሄደ። ጉባኤውን በፎቶ ይመልከቱ

የአስተዳዳሪው መልእክት

ያለ ሥርዓት አልሄድንም  (2ኛ ተሰ 3÷7)

ማንኛውም ፍጡር በተፈጥሮ የተሰጠው ሕግና ሥርዓት አለው ይልቁንም ሰው የተፈጠረውና የሚኖረው ሲመራም የኖረበት ሥርዓት አለው። አፈጻጸማቸውና አጠቃቀማቸው ስለ ሥርዓትም ያላቸው ግንዛቤና የሚሰጡት ዋጋ የተለያየ ይሁን እንጅ በዓለም ላይ ያሉ የእምነት ተቋማት ሁሉ ያለ ሥርዓት መቆም መኖር መገኘት አልቻሉም አይችሉምም ።

እያንዳንዱ የእምነት ተቋም በሕግና በሥርዓት የመኖሩ ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም የአይሁድ እምነት ሥርዓትና ወግ ባህል ትውፊት ልዩ ቦታ የሚሰጠው በሰዎች ዘንድ ሁሉ የታወቀ ነበር ። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ክርስትናው ሲመሠረትም ራሱን የቻለ የታወቀ ሕግና ሥርዓት አፈጻጸም ያለው ሆኖ ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ (1ኛ ቆሮ 14÷40) ላይ ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን ብሏል ይህም ማለት የአማንያኑ የእምነት አፈጻጸም ሕግና ሥርዓት ያለው መሆን እንዳለበትና በአግባቡ መፈጸም እንዳለበት ያስረዳናል ።

ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚከናወንበት ሥርአት አለው ካህናቱ ሥርዓተ አምልኮውን (አግልግሎቱን) ሲፈጽሙ በሥርዓትና በአግባቡ መሆን እንዳለበት ምእመናኑም ለማገልገልም ሆነ ለመገልገል ሥርዓት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል በየአብያተ ክርስቲያናቱ ዘንድ ልዩ የሚሆነው ጉዳይ ይኸ ሥርዓት አግባብ አለው ውይስ የለውም የሚለው ነው የተለያዩ የእምነት ድርጅቶች ስለ ሥርዓት እንኳን ያላቸው ግንዛቤ ከዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ እያየን ነው። በዚህም ምክንያት እምነት በየጊዜው የሚለዋወጥ የተበከለ የተመረዘ ሕግንና ሥርዓትን ያልጠበቀ የቀደሙ አበው የሐዋርያት የሊቃውንትን አሰረ ፍኖት ያልተከተለ መሥመር የለቀቀ ሆኖ ይገኛል።

ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ተሰ 2÷15 ላይ “አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን ያስተማርናችሁንና የሠራንላችሁን ሥርዓት ያዙ” በማለት አስረግጦ አስተምሮናል ስለሆነም ሥርአት ምንድን ነው ስንል በተፈጥሮ የተገኘና ፍጡራን በየጊዜው በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው የሚፈጽሙት የእምነት ቀኖናቸውን የሚጠብቁበት እራሳቸውን የሚያዩበትና የሚመዝኑበት የሚያስተካክሉበት የሚገዙበት ስህተታቸውን የሚያርሙበት ድርጊት ነው ይህ ደግሞ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ሕይወት ላላቸው እንስሳትም ሆነ ለሰማያውያን መላክት ጭምር በየድርሻቸው የተሠራና እስከ ምጽአት ድረስ የሚሠራ ነው።

በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳት ሁሉ ታጠግባለህ(መዝ 144÷16) ይሁን እንጅ ሥርዓትን ለመማር ሥርዓትን ለማወቅ ሥርዓትን ለመሥራት መጀመሪያውና ቀዳሚው ተግባር መጻሕፍትን ማንበብና መምህራንን መጠየቅ በዕውቀት ሙሉ ሆኖ መገኘት ሲሆን እነዚህንም ተግባራት ለማከናወን ይረዳን ዘንድ የደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም ይህን ድረ ገጽ ሲያዘጋጅ ምእመናን የሚሰጠውን ትምህርት የሚተላለፈውን መልእክት አንብበው በትምህርቱ እራሳቸውን በዕውቀት ለማጠንከርና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን ለመኖር የሚረዳቸውን ዕውቀት የሚገበዩበት መንፈሳዊ የነፃ ገበያ እንዲሆን ታስቦ ነው። ስለሆነም የሚተላለፈውን መንፈሳዊ ምግብ በነፃ በመሸመት የመንፈሳዊ ሕይወት ረሀብ የያዛችሁ በድርቅ የተመታችሁ ሁሉ እንድታገግሙበት ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላለች።

መጋቤ ብሉይ አባ ቀለመወርቅ አቡኔ
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ

በፌስቡክ ያግኙን

ግጻዌ

መንፈሳዊ አገልግሎት

የሰንበት ት/ቤት እና ህጻናት አገልግሎት

ያግኙን