የ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የ ፳፻፰ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል ከኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመጡ ካህናት እና መዘምራን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ በርካታ ምእመናን እሁድ መስከረም ፲፮ በታላቅ ድምቀት ተከበረ። በዓሉ እሁድ እለት ከሰዓት በኋላ በካህናት አባቶች ጸሎት የተጀመረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ መዘምራን በዓሉን የተመለከቱ መዝሙራትን አቅርበዋል፣ የወንጌል ትምህርት ደግሞ ሥርዓተ ጸሎቱን በመሩት አባታችን ቀሲስ ተስፋዬ ከተሰጠ በኋላ በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን እንዲሁ በዓሉን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል።በማስከተልም ደመራው ተባርኮ የተለኮሰ ሲሆን መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል፤በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል። በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት ላደረጋችሁት መንፈሳዊ አስትዋጾ ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።