መጻጉዕ

መጻጉዕ

የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ የሚዘመረው ዝማሬ የሚነበበው ምንባብ ፣ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚገልጥ በመሆኑ ነው፡፡

«ሠላሳ ስምንት ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው “ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም” አለው። “ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ” ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ “የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ” እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ “በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና “በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ” እያለ ሠላሳ ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ይናገራል

የሕሙማን መታሰቢያ ሳምንት ማለት ነው።
የስያሜው ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
➾ 1ኛ.ለአምስተ ሺህ አምስት መቶ ዘመን በዚህ ዓለም በሥጋ በአካለ ነፍስም በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት እየተረገጡ ይኖሩ የነበሩት ሕሙማነ ሥጋን እና ሕሙማነ ነፍስን የምናስብበት ሰሙን ማለት ነው።
➾ 2ኛ.መድኅን ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ የሆኑትን በማዳን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ያስተማረበትን ዘመን የምናስብበት ነው።
“ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።”ማቴ. 4 ፥ 23 እንዲል።
➾ 3ኛ.ሥግው መለኮት ሕማማችንን ሕማም አድርጎ በዕለተ ዓርብ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን፤በአካለ ነፍስ ወደ ሢኦል ወርዶ ዕዳ በደልን ያጠፋበትን የምናስብበት ነው።በዚህ ዓለም ያለው ደዌ ሥጋ የዚህ ዓለም ምሳሌ ነው።ፈውሰ ሥጋ የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው።
“በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል።”ኢሳ 53 ፥ 4 እንዲል።
➾ 4ኛ.እስከ ዕለተ ምጽአት እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ሕሙማንን ብንችል እየፈወስን ካልቻልን እየጠየቅን የወንጌልን ሕግ እንፈጽም ዘንድ መታዘዛችንን የምናስብበት ሳምንት ነው።”ታምሜ ጠይቃችሁኛልና።”ማቴ. 25 ፥ 36 እንዲል።
5ኛ.ኃጢአትን በንስሐ እያስወገድን ከደዌ ነፍስ እየተላቀቅን እንኖር ዘንድ የምናስብበት ሰሙን ነው።
➢ በኃጢያት መያዝ የደዌ ፦ በንስሐ መታጠብ የፈውስ ምሳሌ ነውና።..
“ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ።”ማቴ. 8 ፥ 4 እንዲል።

ይኸ ሁሉ የክርስቶስ ሥራው፣ መግቦቱ ፣ ቸርነቱ የተቋረጠ አይደለምና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስናስበው ስንፈጽመው እንኖራለን።
“አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ።”ዮሐ. 5 ፥ 17
ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰን አሜን ።

ይቆየን፤

ምኵራብ

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፤
ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ፤ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ቦአ ምኲራቦሙ ወገሠጾሙ ያርምሙ፤አንከሩ ምሕሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዐ አፉሁ።

ትርጉም
ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤የሃማኖት ትምህርትን አስተማረ፤ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው፤የሰንበት ጌታ የይቅርታ አባት እኔ ነኝ፤የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት፤ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ወደምኵራባቸው ገባ፤ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው፤ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ የነገሩን ጣዕም የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።
(ቅዱስ ያሬድ)

➾ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት ፣
ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው

➣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ወደምኵራብ ገባ ነገር ግን በምኵራብ ወርቅና ብር የሚለውጡትን በጉን በሬውን ርግቡን የሚሸጡትን አየ እሱም የአባቴን ቤት ወይም ቤቴ የጸሎት ቤት ነው የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የገበያ አዳራሽ የሌቦች ዋሻ የቀማኞች መሸሻ አደረጋችሁት ብሎ
እየገረፈ አስወጣቸው እና ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው ይላል ለምን እንዲህ አለ ብንል ለመሥዋዕት የሚያቀርቡ ከዚህ እየገዙ ነበር ፣
➢ ለበዓል የሚወጡ ሰዎች ከሩቅ ቦታ የሁለት ቀን የሶስት ቀን የሳምንት ጎዳና እየነዱ መጥተው ሲደርሱ በዚያ ያሉ የጊዜው ነጋዴዎች ይኸማ ከስቷል ቀጥኗል ደክሟል ለመሥዋዕት አይሆንም ይሏቸዋል፣
➣ አና ምን ይሻላል ሲሏቸው እኛጋ የሰባ የወፈረ ያማረ ለመሥዋዕት የሚሆን አለን በሁለት አንድ ለውጣችሁ ወሰዱና ሠው እያሉ ምክንያት እየፈጠሩ ያጭበረብሩ ነበር ጌታ ይህን አይቶ ከመሥዋዕት ይልቅ ለሰዎች ማሰብን ለሰዎች መስጠትን ለሌሎች መራራትን ለሌለው ማካፈልን እወዳለሁ እንጅ እናንተ በማጭበርበር የምትነገዱበትን አይደለም ብሎ እየገረፈ አስወጣቸው ይላል ፣
➾ ስለዚህ ዛሬ ቤተ መቅደሱን ጌታችን ኢየሱስ ያጸዳበት ቀን ነው።
➢ አዎ ቤተ መቅደሱ በነጋዴዎች ተሞልቷል መቅደሱ በሌቦች በአጭበርባሪዎች በአስመሳዮች በግብዞች በውሸታሞች ተሞልቷል መጽዳት ይገባዋል።
መቅደሱ ለታለመለት አላማ ለምስጋና ለጸሎት የተገባ ሊሆን ያስፈልጋል ፣፣
➢ አንድም መቅደስ ሰውነታችን የተለያዩ ችግሮች ነግሠውበታል ውሸት ሐሜት ስርቆት ክፋት ተንኮል ምቀኝነት ዘረኝነት ሌብነት ዝሙት ሱሰኝነት በአጠቃላይ ምልዓተ ኃጢአት ሞልቶታል መጽዳት አለበት ።
➣ አሁን አሁን አብዛኛዎቻችን ሀሳባችን እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ አገልጋዮችን ስለእኛ ሕይወት መጥፋትም ሆነ ለሚሰራው ጥፋት ተጠያቂ በማድረግ እነርሱን እንደ አይሁድ በጅራፍም ሆነ በሥልጣኑ እንዲገሥፃቸው እንፈልጋለን ነገር ግን በሰውነታችን ፣በልቡናችን ላቆምነው ጣኦት፣ሕዋሳቶቻችን ጽድቅን በርኩሰት፣ጾምን በሆዳምነት፣ዕውቀትን በድንቁርና እየለዋወጥን ላለን ሰዎችምኮ ተግሣጽ አለብን ።
ሕዋሳቶቻችንን በምጽዋት ፣ በፆም ፣ በጸሎት፣ በስግደት ያነጻን እንደሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ወደ ሕይወታችን የሚገባው በጅራፍ፣በተግሣጽ ሳይሆን በምሕረት በጸጋ ይሆናል እንዲሁም የሚፈታተኑንን ኀጣውእን ፣ ርኩሳትን አጋንንትን ከሰውነታችን ከቤቴ፣ከማደሪያዬ ምዕመን ውጣ በማለት ጠላታችን ኀጢአትን፣ዲያብሎስን ይገሥጽልናል። ሰውነታችን የልዩ ልዩ ክፉ ነገሮች መገበያያ ሆኗልና አምላካችን በመምህራን ትምህርት ፣በካህናት ሥልጣነ ክህነት ፤በምሕረቱ በቸርነቱ ያንጻን፣
እግዚአብሔር መቅደሱን ያጽዳልን ። አሜን

ይቆየን

ቅድስት

“እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ኤፌሶን 5 ÷ 27

የአብይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት የሚከተሉት ናቸው።

  • የቅድስና ትርጉም፡ “ቅድስት” ማለት “የተቀደሰች፣ የተለየች” የከበረች ” ማለት ነው። ይህ ሳምንት በልዩ መንፈሳዊ ትኩረት እና በጸሎት፣ በጾም እና በንስሃ ስለሚታለፍ ቅድስት ተብሎ ይጠራል።
  • በዚ ሳምንት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ የጀመረው የ40 ቀን እና ሌሊት ጾም የሚታሰብበት በመሆኑ ቅድስት ይባላል።
  • ስያሜው ከኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ አስተምህሮ ነው፡፡

ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርት፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ እና ወንጌላቱም ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ፣ የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራው በውስጡ ባለው መንፈሳዊ ትኩረት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ትውስታ እና በቤተክርስቲያን ትምህርት ነው።

ስለዚህ ቅድስት ሲባል የሚጠቁመን እራሳችንን ቁዱስና እና ንጹህ አድርገን በንስሐ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበልን እኔ ቅዱስ ነኘና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዳለ ከሐጢአት ከበደል ከክፋት ከተንኮል ከቂም ከበቀል ከሐሜት ከሐሰት ከምቀኝነት ከዘረኝነት ወጥተን በጎ በጎውን በማሰብ መልካም ሥራ በመሥራት መንፈሳዊ ሰው በመሆን ልንኖር ይገባል ፣አምላካችን መልካሙን ሁሉ እንድናደርግ ይርዳን አሜን ፣

ይቆየን ።

ዘወረደ

“ወአልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ዘውእቱ ይነብር ውስተ ሰማይ።
ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” ዮሐንስ 3 ÷ 13

ዘወረደ ፦ ማለት! ከክብር አንድም ከከፍታ አንድም ከንጽሕና አንድም ከጽድቅ የወረደ የተለየ ማለት ነው ፣ለጌታ ሲሆን ከሰማየ ሰማያት ከልዕልና ከመስቀል የወረደ ማለት ነው ።

እግዚአብሔር አዳምን በጥንተ ተፈጥሮ በልጅነት አክብሮ በቦታ አልቆ በገነት አኑሮት ነበር ነገር ግን ሕግ ባለማክበሩ ከክብሩ ተዋርዷል ፣

  • ከንጽሕና ፦ አዳም በክብር በልጅነት ከብሮ ከሚኖርባት ገነት በኃጢአት ቆሽሾ መውጣቱን ፣ የሰው ልጅ ሰማያዊ መንግሥትን እንዳይወርስ በምድራዊ በኃላፊው በሚጠፋው በሚቀረው ቁሳዊ ዓለም ተጠምዶ በኃጢአት ተውጦ መኖሩን መናገር ነው ፣
  • ከሰማይ፦ በዚህ ሁሉ ምክንያት የተዋረደ አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ የተዋረደውን የአዳምን ሥጋ ለብሶ ሰው መሆኑን አንድም ከልዕልና መውረዱን መናገር ነው ፣

ስለዚህ ወንጌላዊ ከወረደው በቀር የወጣ የለም ሲል ወደ ሲኦል የወረደ አዳም ወደ ገነት ተመልሶ ርስቱን መውረሱን በኃጢአት በበደል የወረደው ወደ ጽድቅ ፣ በውርደት የተሰደደው ወደክብር ፣ በሞት የተቀጣው ወደ ሕይወት ፣ በኀዘን የተዋጠው ወደ ደስታ ፣ በጭንቀት የተያዘው ወደ ሰላም ፣ በፍዳ በመከራ የወደቀው አዳም ወደ ነጻነት ተመለሰ ማለት ነው ።

አንድም ከአደባባይ ወደ መስቀል ፣ ከግዘፍ ወደ ርቀት ከትሕትና ወደ ልዕልና ከከመቃብር ወደ ትንሣኤ ከምድር ወደ ሰማይ የወጣ እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረው በማዕከለ ዓለም የተገለጠው ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው መንግሥቱ ዘለዐለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየሰማያት የወረደው ዝቅ ያለው ከድሆች ጋር የተመላለሰው ከኃጢአተኞች ጋር የተቆጠረው ተዋርዶ የነበረውን ሰው ወደላይ ከፍ ያደረገው በትህትና ውስጥ እየተመላለሰ ነው ፣
የክብር ባለቤ ኢየሱስ ክስቶስ በኃጢአት የተዋረድነውን ሁሉ በመሐሪነቱ በንስሐ ይመልሰን ፣ አሜን ።

ይቆየን

በዓለ መስቀል

በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል
አይሁድ በምቀኝነት በጎልጎታ የቀበሩት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፀ ምስቀል እነሆ ዛሬ ተገኘ
(ቅዱስ ያሬድ )

በዓለ መስቀል በክርስትና ኃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮአደባባይ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ክፋትና ምቀኝነት ለ300 ዓመታት ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በድምቀት ታከብራለች።

“መስከረም በአበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” እንዲሉ አበው። የመስከረም ወር ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ የአበባ የጽጌ የብርሃን ወቅት በመሆኑ በዚህ ወር የመስቀል በዓል መከበሩ እጅግ ድምቀት እንዲያገኝ አድርጎታል ። እናም ኢትዮጵያውያን በርዕሰ በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርኃ መስከረም፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከነዚህም ውስጥ ከእንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሠፊው የሚታወቀው በዓለ መስቀል ነው።

መስቀል ምንም እንኳ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ፣ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የኅብረተሰብ ክፍሎችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ለምሣሌ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚደረጉት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ስለመስቀል በዓል አከባበር ፣ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ምልክት የታየበት ሕሙማን የሚድኑበት ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ለ300 ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ቦታ ቀብረውት ቆይቶ ነበር።

ይሁንና በ326 ዓ/ም የቄሳር / ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራኮስ በተባለ አንድ ታሪክ አዋቂና ፈላስፋ ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም
በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች። ንግሥተ ዕሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣችው ይነግረናል። ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ተከትሎ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል ።

በነገራችን ላይ ስለመስቀል በዓል ስናነሳ፣ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ቢያከብሩትም በልዩ ክብር እና ደማቅ ሁኔታ የሚከበረው ግን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ መሆኑን መናገር ይቻላል። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ መሞትና በመስቀሉ የማይረሳ ውለታ የሰው ልጅ መዳኑን ቢያምኑም እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ትውፊትን ስለማይቀበሉ፣ የመስቀልን በዓል ኃይማኖታዊ በዓል አድርገው አይመለከቱትም።ይሁን እንጅ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን አስቆፍሮ ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል ፈጅቶ “መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን ነው፣ ይህ ወር ግን የየዓቢይ ጾም ወቅት በመሆኑ በዓሉ በመስከረም 17 ቀን እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውናል” ።

በኢትዮጵያችን ሌላው የጌታችንን መስቀል ልዩ ሥፍራ እና ክብር የሚሰጠው ጉዳይ ደግሞ በ15 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መቀመጡ ነው። ስለ መስቀሉ መምጣት ታሪክ እንደሚያስረዳን፣ ንጉሡ አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸግሯቸው ሲጨነቁ ፡ በመጨረሻ ግን “አንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል። (መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጠው)” የሚል መለኮታዊ ራዕይ ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼን አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ/ም እንዳሳረፉት የታሪክ መዛግብት
ያስረዳሉ። የግሸን ደብረ ከርቤ (አምባ ማርያም) ቦታ የተመረጠበት ምክንያት መስቀለኛ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመሆኑ ከራዕያቸው ጋራ ስለስማማላቸውና ስለተፈቀደላቸው ነው።

የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች ዛሬም እኛ ከአባቶቻችን በቅብብሎሽ የተረከብነውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት አስቀጥለን በዓለ መስቀልን አክብረንና አስከብረን አባቶቻችን የወረሱትን የመስቀሉን ጸጋና በረከት አምላካችን እግዚአብሔር ያድለን አሜን ።

“እግዚአብሔር ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ያስብልን፤ ህዝቦቹንም ይጠብቀን፡፡”
ይቆየን ።

በዓለ ሆሣዕና

ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡

ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ይነግራቸዋል፡፡

በተናቀች ግርግም በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ላምና አህያ ትንፋሻቸውን እንደገበሩለት፤ አኹንም በሰዎች በተናቀች አህያ በጌትነት ተቀምጦ እንዲመሰገንባት መርጧታል፡፡

በልደቱ ማንም ያልገባባት የማይገባባት የሕዝቅኤል የታተመች መቅደስ የተባለች ዘላለማዊት ድንግል እመቤታችንን እንደመረጠ ዛሬም በሆሣዕና ማንም ሰው ያልተቀመጠባት አህያን ከውርንጫዋ ጋር እንዲያመጡ አዘዘ።

ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋልና።

ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡”

ሊቁ አምብሮስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው የማሰር የመፍታት ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑን ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል።

አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ። ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ፡፡ በተጨማሪም ልብስ በልጅነት ይመሰላልና የተገፈፍነውን የጸጋ ልብሳችን (ልጅነትን) ትመልስልናለህ ሲል፨

ቅዱስ ኤፍሬም ይኽነን ሲተረጉም “ልብሳቸውን አውልቀው ያነጠፉለት ሰዎች አሮጌውን ማንነታቸውን ትተው ዐዲሱን ልብስ ክርስቶስን መልበሳቸውን ያስረዳል። ሐዋርያ ጳውሎስ “አሮጌውን ሰውነት አስወግዳችሁ አዲሱን ሰው ልበሱት” እንዳለው (ኤፌ.4፣23) ይኸውም ጥምቀት ነው” ይላል።

ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማነ ሐዲስ በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡ 2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡

ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ። በተጨማሪም መተርጉማን እንዳመሰጠሩት በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡

ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት አመስጥሯል፡፡

፦ ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው (መዝ.49፡12)፡፡ በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደ አህያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጿል፡፡

ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባትም ሲሉ ነበር። እንስሳዋ እንኳን ጌታ ቢቀመጥባት እንዲህ ክብር ያገኘች ከሆነ ያደረባቸው ቅዱሳንማ የሚገባቸው ክብር ምን ያህል ይሆን? ይልቁኑ 9 ወር ከ5 ቀናት በማሕፀኗ የተሸከመችው ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ሰው የሆነውን አምላክ የወለደችው የቅድስት ድንግል ማርያም ክብርማ እጅጉን ታላቅ ነው።

ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። ይኽም ዘንባባ ብዙ ምሳሌ ያለው ነው፤ ይኸውም በእስራኤል ያለው ሰሌን፣ ተምር፣ ዘይት ነበርና ያነን ቈርጠው አመስግነውታል፤ ይኽም ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኽም ሰሌን እሾኻማ እንደኾነ ትእምርተ ኀይል ትእምርተ መዊእ አለኽ ሲሉ ነው፤ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እንደማያቃጥለው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነው፡፡

በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ የተለጠፈ)

 

እግዚአብሔር  በዓሉን የበረከት  ያድርግልን

ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት:- የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑና   ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት እየተባለ ይጠራል። (ማቴ.24÷ 3)

ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬሕይወት”

ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል። የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።” በማለት ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24  ላይ ያለውን ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው ከአሁን በፊት በመጣበት መንገድ  በትሕትና ሳይሆን በልዕልና በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ሳይሆን በምልዓት በስፋት በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ነው። በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል። ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ። ከእናቱ ጡትን እየለመነ ሳይሆን፣ ለፍጥረት ሁሉ  ዋጋ ለመስጠት ። ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ  የሚሸሹለት  ሆኖ  ይመጣል ። የጌታችን ዳግም ምጽአት ፡-

  1. የጸሎታችን መልስ ነው።
  2. የፍጥረት የምጥ ዕረፍት ነው።
  3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
  4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
  5. የእምነታችን ክብር ነው።
  6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
  7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡

1.  የጸሎታችን መልስ ነው:-

ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ። ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው። የምንፈራውና ይቅርብን የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥትህ ትምጣ” እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው። የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው። በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ.14÷17) ። የክርስቶስ መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው። ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው።

2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው:-

ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል። (ሮሜ.8÷19)ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል ቁ.22) ። በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው። እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው። ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግድ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል። የራሱም ዕረፍት ነውና። ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን። ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን። የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።

3.  የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው:-

“ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.22÷20)። ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት ጣር ካየበኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህም ማራናታ አለ። የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው። በመጀመሪያው  ምጽአቱ ሞት እንደ ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱም መከራ ገደብ ያገኛል።

4.  የተስፋችን ፍጻሜ ነው:-

የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡። የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም። ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እንዳያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ቀዱስ ጳውሎስ፡- “የተባረከው ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ.2÷12 13) ይላል። ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ። እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው። የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው። ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው።

5.  የእምነታችን ክብር ነው:-

ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን  እረኛችንን ተከትለን  ወደ ዘለዓለም  ደስታ  እንገባለን።

6.  የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው:-

በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ.21÷1) ። አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው። አሁን ፍጥረት አርጅቷል። በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨለመ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው። ይህን ሁሉ አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት ነው። ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል።

7.  የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው:-

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች። ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ። ገነት ጊዜያዊ የነፍሳት ማረፊያ ናትና። ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ። መንግሥተ ሰማያትና  ገሃነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41) ።
ዘለዓለማዊው  ርስትም  ይከፈታል። ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን።
የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው። ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው። ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል።

የእግዚአብሔር ፍቅርና  ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን
አሜን ።

ኖላዊ

የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ‹‹ኖላዊ›› ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት ‹‹እረኛ›› ወይም ‹‹ጠባቂ›› ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ቅዱሳን ነቢያት አምላክ ወልደ አምላክ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው ትንቢት መናገራቸው እና ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ኖላዊ ዘበአማን እውነተኛ ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቤተክርስቲያናችን የምታስተምርበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ፤ ብሎም ዓለምን ፤ እንደ በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ ይታሰባል። ቤተክርስቲያን ፦

“ ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አፅምእ፤
ዘይርዕዮሙ ከመ አባግዕ ለዮሴፍ፤
ዘይነብር ላዕለ ኪሩቤል አስተርአየ።
በቅድመ ኤፍሬም ወብንያም ወምናሴ፤
አንሥእ ኀይለከ ፥ ወነዐ አድኅነነ።

እረኛ የሌለው የበግ መንጋ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ 79፡1) በማለት ይማፀኑ እንደ ነበር ታስተምራለች።

ቸር ጠባቂ: የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል›› ዮሐ፣ 10፥11 በማለት እውነተኛ አእረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል። ስለራሱም ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።›› ዮሐ 10፡15 በማለት አስተምሯል፡፡

በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ (22፡1) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተበትነናልና ሰብስበን ጠፍተናልና ፈልገን አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ሁሉን ወደ ሚችል ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

ከተኩላዎች ተጠበቁ: ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› ብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛና ምንደኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ ስለበጎቹም ይገደዋል ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። (ማቴ 7፡15)፡ ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው እየታገሉ ነው ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል ከቅዱሳን ነቢያት በረከት ያድለን አሜን፣

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ብርሃን

የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ብርሃን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት የነበሩበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው። በዚህ ሳምንት ከዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ዘመን ( 14 ትውልድ) ይታሰብበታል፡፡

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከአስተማሩባቸውና፣ ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣ “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ 42፡3) በማለት ይጸልይ ነበር፡፡ ይህም ማለት ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድን) ላክልን፤ እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው (ኢሳ 49)፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ እውነተኛ ብርሃን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት አስረግጦ ይነግረናል፣ (ዮሐ 1፡1-11)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ 8:12) ብሎ ስለ እርሱ እውነተኛ ብርሃንነትና አምላክነት በሚገባ አስተምሯል፡፡

በዚህ ዕለት ‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን›› እንዲሁም ‹‹የማይነገር ብርሃን›› የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ አስረግጦልናል፡፡ ‹‹ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ እንዳስተማረን። ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ‹‹በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ፤ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና። የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን፤ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን የሕይወታችን ብርሃን የሆነውን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ረድኤቱን ይላክልን ፣ አሜን ፣

ዘመነ ስብከት

ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ስብከት: የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ‹‹ስብከት›› ይባላል፡፡ በዚህ ቀንም በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያትም አስቀድሞ ስለ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ትንቢት ተነግሮ፣ ምሳሌ ተመስሎ፣ ሱባዔ ተቆጥሮ እንደ ነበር ይነገራል፤ ይሰበካልም፡፡

እምኦሪተ ሙሴ እስከ ነቢያት ሰበኩ ምጽአቶ ንህነ ነአምን ስብከቶ ፣ ከኦሪተ ሙሴ አንስቶ እስከ ነቢያት የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት ሰበኩ አስተማሩ እኛም ሙሴና ነቢያት የሰበኩት ስብከት አምነን እንቀበላለን ፣እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ )

ቅዱሳን ነቢያቱ አስቀድመው መምጣቱን ሰብከው ስለነበር ያንን ለማሰብ ይህ ዕለት ‹‹ስብከት›› ይባላል፣ ስብከት ማለት ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከአብርሃም እስከ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡

የነቢያት ስብከት: በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደ ጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል (ዮሐ 1፡44)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ፈኑ እዴከ እም አርያም » እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም› (መዝ 143፡7) በማለት ስለክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡ ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› (ኢሳ 64፡1) ብሎ ስለክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ፣ ከድንግል ማርያምም መወለድ የተናገረውን ትንቢት ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡

የቤተክርስቲያናችን ስብከት: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (2ኛ ቆሮ 4፡5) እንዳለው ቤተክርስቲያን በተለይ በዘመነ ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠውንና የፈጸመውን የማዳን ተስፋ ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ “ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን” እንዳለ ቤተክርስቲያናችን ፣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ በችግርም በደስታም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና አምላክ ወልደ አምላክ ክርስቶስን ትሰብካለች፤

አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን በረከየተ ያድለን፣ አሜን።