ትንሣኤ

“እንደተናገረ ተነስቷል።” ማቴ  28 ፥ 6
ትንሣኤ ማለት ቀጥታ የቃሉ ትርጉም መነሣት ማለት ነው።

ብዙዎቻችንም እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን አደረሳችሁ እያልን እና እየተባባልን  ነው። ፖለቲከኛውም፣ ሰባኪውም፣ ጳጳሱም፣ ዘማሪውም  ዘፋኙም፣  አርቲስቱም፣ አክቲቪስቱም ሁሉም እንኳን አደረሳችሁ እያለ ነው። ጥሩ ነው ፥ ለምን ይባላል ማለት አይገባም ፥ ደስ ይላል ፥ መጠያየቁ  መተሳሰቡ ከልብ ከሆነ !! በሌላ መልኩ መድረስ የሚለው ቃል ናፋቂ ሆኗል ፥ ውሎ መግባት ፣ አድሮ  መገኘት ፣ ተኝቶ መነሳት ፣ ቁሞ መሔድ  ብርቅ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

➾  ጌታ ተነሣ ስንል እኛም መነሣት አለብን።  ከከፋፋይነት መቃብር ወጥተን  አንድ የሚያደርገን  ሐሳብ  መኖር  አለበት ።

  • በቂም በቀል እና በሴራ መቃብር ውስጥ ሆነን እንኳን አደረሳችሁ ብንባባል  የውሸት የይሁዳ ሰላምታ ይሆናል ።
  • እንደ ይሁዳ በልባችን ፥ ጥላቻ ፥ ፍቅረ  ነዋይ ፥ ቂምና በቀል ፥ ተንኮል ፥ ውሸት ፥ ሐሜት ፥ ሐሰት ፥ ትውዝፍት ፥ ሱሰኝነት ፥ ጣዖትን ፥ ማምለክ ፥  ምዋርት ፥ ጥል ፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት ፥  እያለ  በምንም አይነት መንገድ  የእውነት ሰላምታ ሊሆን አይችልም ስለዚህ  ከመቃብር እንውጣ ።  ያንጊዜ ትንሣኤያችን  በግልጥ  ቅዱሳት አንስት የሚያዩት ሐዋርያት የሚመልከቱት ይሆናል። በመቃብር ሆነን ስለ ትንሣኤ ብናወራ  እውነት አይሆንም  አያምርብንም።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተነሣ እኛም  በትንሣኤ ልቡና እንነሣ። የዘረኝነት፣ የውሸት፣ የጥላቻ፥ የበቀል፣ የሐሜት፣ የከንቱ ውዳሴ፣ የትዕቢት፣ የራስ ወዳድነት መቃብርን ፈንቅለን እንውጣ  ፣ በአፋችን እንኳን አደረሳችሁ እየተባባልን በልባችን ግን ቀጣይ ዓመት እንዳንደርስ እየተገዳደን ከሆነ ግን ይሁዳነት ነው። ይሁዳ ጌታን የሸጠው በአፉ ሰላም እያለ ነው ። ሁሉም ከተንኮል፣ ከሽንገላ መቃብር ይውጣ እና የፍቅር ትንሣኤን ይነሣ። እግዚአብሔር  የፍቅር  ትንሣኤ እንድናከብር አምላካችን ያድለን።

«እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና፡— ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ፥ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው።»  የማቴዎስ ወንጌል 28:6-7

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በጤና አደረሳችሁ!  አሜን ።

ይቆየን።

ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ክርስቶስ አምላካችን ራሱን ዝቅ አድርጎ የሐዋርያትን እግር ያጠበበት ዕለት ነው፡፡

በሕማማት ውስጥ ያለው ይህ ሐሙስ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል፡፡

አንደኛ፦ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኀብስቱን በባረከ ጊዜ ስለጸለየ፤  እና  ከመያዙ አስቀድሞ በጌቴሴማኒ  ደቀ መዛሙርቱ ተኝተው እርሱ ግን  ተንበርክኮ  አባት ሆይ ብትወድስ ይች ጽዋ ከእኔ ትለፍ እያለ በሰው ልጆች  (በአዳም ልጆች) ተገብት ጸልዮልናል ፡፡
ሁለተኛው፦ትዕዛዝ ሐሙስ ይባላል ፡ ምክንያቱም ከኀጽበተ እግር በኋላ ጌታ እናንተም እንዲሁ አድርጉ ብሎ  አዝዟቸዋልና ነው ከዚያም ቀጥሎ በጌቴሴማኒም  ጌታ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ ብሎ አዝዟቸዋል፤
ሦስተኛ፦ የምሥጢር ቀን ይባላል ፡ ሥርዓተ ቁርባንን ከሠራ በኋላ /ከመዝ ግብሩ ተዝካርየ/ ብሎ አዝዟል  እንዲሁም በዚህ ዕለት የተሰጡትን ሌሎችንም ትዕዛዛት ለማስታወስ ነው፡፡
አራተኛ፦ ኀጽበተ እግር  ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቀን ጌታ የደቀመዛሙርቱን እግር ስላጠበ ባዘዘንም መሠረት ዛሬ በቤተክርስቲያን መታሰቢያውን እናደርጋለን ፡፡
አምስተኛ፦የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ በዚሁ ቀን ምሽት ጌታችን ‹‹ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፡— እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው» አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡— ‹‹ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።» (ማቴ.26:28) በማለት የሰጠንን ዘለዓለማዊ ኪዳን የሚያስታውስ ስያሜ ነው፡፡

ጌታችን ተጠምቆ ተጠመቁ ፣ ጾሞም ጹሙ እንዳለን ፣ ጸልዮ ጸልዩ፤ ሰግዶም ስገዱ ሲለን እንደዚሁም የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ አርአያነቱን ሲያሳየን መምህረ ትሕትናነቱን ሲገልጥልን ነው፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱና ካህናቱ ሁሉም በየመዓርጋቸው የምእመናኑን እግር ዝቅ ብለው የሚያጥቡት የጌታን የትሕትና ሥራ ለማሰብ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ይህንን ሥርዓቱን አብነት በማድረግ በዚች ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የሕፅበተ እግር ሥርዓቱ በሚከናወንበት ጊዜ ዲያቆኑ ውኃን ያቀርባል፤ በቀረበውም ውኃ ላይ ጸሎተ አኰቴት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነብቦ ውኃው በካህኑ ወይም በሊቀ ጳጳሱ እጅ ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓቱ ከካህናት እስከ አናጕንስጢስ እንደዚሁም ከወንዶች እስከ ሴቶች ላሉት ምእመናን ሁሉ በካህናቱ እጅ ይከናወናል፡፡

ከበዓሉ በረከት  ያድለን አሜን፡፡

ሆሣዕና

ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሣዕና”  ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ክንፋቸው ትእምርተ መስቀል የሚሠራው ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዓድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት ጌታ በትሕትና ኾኖ  በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲሆን  በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡

ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ሁሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡ አህያዋ የሕዝቡ  ውርንጫዋ የአሕዛቡ ምሳሌ ናቸው፡፡

ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋል።

አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ። ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ በማለት መተርጉማን ይተነትናሉ፡፡ በተጨማሪም ልብስ በልጅነት ይመሰላልና የተገፈፍነውን የጸጋ ልብሳችን (ልጅነትን) ትመልስልናለህ ሲሉ ነው፡፡

ዛሬም  በኃጢአት  ክፋት በተንኮል በምቀኝነት በዘረኝነት  የተገፈፈ  ጸጋችንን በጽድቅ  በምሕረት በደግነት  በፍቅር  ይመልስልን አሜን ፡፡

ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ የዓቢይ ጾም  ሰባተኛ ሳምንት  ሲሆን ስያሜው  ኒቆዲሞስ በተባለ የአይሁድ አለቃ በነበረ ሰው ስም ተሰይሟል፡፡

“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤” ዮሐ 3-1

በዕለቱ በሚነበበው በዚህ  የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ ጥያቄና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ይገልጽልናል።

“ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው” ዮሐ 7-51
ቀን ቀን ከአይሁዳውያን ጋር ሲያስተምር ይውላል  ማታ ማታ  ዕውቀቱን ለማስፋት ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ሲማር ያድራል  አለቅነትን ከመምህርነት  ዕውቀትን ከትህትና   አስተባብሮ የያዘ ሰው ነበር ፣

“የምስጢረ ጥምቀት መገለጥም  ምክንያት የሆነ  እና  ምስጢረ ጥምቀትን  ከባለቤቱ ጠይቆ የተረዳ  ሰው ነው ”  ዮሐ 3  ÷ 1-21
አንዳንዴ ሳያውቁ አዋቂ ነን  ሳይማሩ መምህር ነን እናስተምር ለሚሉ ደፋር  መምህራን  ኒቆዲሞስ  ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል፣ የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡ በዚህ ሰዓት ኒቆዲሞስ ጊዜ አላጠፋም ክብሩም አላስጨነቀውም መምህርነቱም  አልገደበውም በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ ፤ በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን ።» ብሎ  እራሱ  ዝቅ አድርጎ በትህትና  ቀረበ።

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደ ሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን  አላወቁም የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ድረስ ከአንተ አንለይም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር፣ በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን  ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ  ነበር፡፡

ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?
ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ  ራሳችንን ጠምደን  የመማር አቅም አጥተናል፡፡  ቁጭ ብሎ መማር  ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ  ስንቶች እንሆን?

አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ፣ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ  እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን በመጽሐፍ ተጽፎ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ እኛስ ያወቅነውን እያሳወቅን ያላወቅነውን ብንማር  ምን ችግር አለው?  ይኸ አልሳካ ያለን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን?  ትሑት የሚያሰኘው  ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ  ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡   ኒቆዲሞስ ግን  ፈሪሳዊ ፣ የአይሁድ አለቃ ፣ መምህር ፣ ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ከመምህራን ስር ቁጭ  ብሎ መማር መታደል ነው
እኛም በምሕረቱ አደባባይ ተገኝተን በጌታ ፊት ቁጭ  ብለን  ቃሉን ለመስማት ያብቃን አሜን ።

ይቆየን፤

ገብር ኄር (መልካም አገልጋይ)

ከደብረ ዘይት ቀጥሎ ያለው ስድስተኛው የዓቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ገብር ኄር ይባላል። መልካም አገልጋይ ቸር ርኅሩኅ ማለት ነው። ይህ ዕለት መልካም አገልጋዮች በትጋታቸው የሚወደሱበት ሰነፍ አገልጋዮች ደግሞ በስንፍናቸው የሚወቀሱበት ዕለት ነው።

ስያሜውን ያገኘው፦
አንደኛ፦በብሉይ ዘመናት የነበሩ መልካም አገልጋዮቹ ነቢያትና እና ካህናት በአጠቃላይ ምእመናነ ብሉይ የአገልግሎት እና የመልካም አገልጋይነት ዋጋቸውን አግኝተው እንደምን እንደ ተመሰገኑ እነሱንና መልካም ስራቸውን የምናስብበት ዕለት ነው።

ሁለተኛው፦የትሩፋተ ሥጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪው መድኅን ክርስቶስ በተገዥ ሰውነት ተገልጦ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተመላልሶ በሕጻንነቱ ለእናቱ ለዘመዶቹ ኋላም ለሁሉም ሰው አርአያ በመሆን በሰውነቱ ማገልገሉን የምናስብበት ነው።”

የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ማቴ.20 ፥ 28 ። አርአያነት ማለት!! የትህትና ሥራውን በገለጸበት በምሴተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡም ከዚህ የተነሣ ነውና።
ስለዚህ ይኸ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነት ተልእኮ የምናስብበት ሳምንት ነው።

ሦስተኛ፦ቅዱሳን ሐዋርያት እና ተከታዮቻቸው በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው በሠሩት መልካም የወንጌል አገልግሎት የተልእኮ ሥራቸው “ቸር አገልጋዮች ተብለው ታማኝነታቸው ፣ ትሩፋታቸው፣ ክብራቸው የሚነገርበት ሳምንት ነው።

አራተኛ፦አጠቃላይ ምእመናን በተሰጣቸው የተፈጥሮ ጸጋ እና የእምነት ጸጋ፣የትሩፋተ ሥጋ፣የትሩፋተ ነፍስ ጸጋ፦ሥራ ሠርተው የጸጋ መክሊታቸውን አብዝተው አትርፈው ቢገኙ የሚመሰገኑበት ሳምንት ነው።

አምስተኛ፦በተፈጥሮ በተሰጣቸው ጸጋ እና በሃይማኖት በሹመት በተሰጣቸው ጸጋ ምግባር ትሩፋት መሥራት ሲገባቸው በስንፍና፣በፍርሀት ተሸብበው የኖሩ ሰነፍ ሰዎችም የሚወቀሱበት ሳምንት እና ክፍለ ጊዜ ነው።

ስድስተኛ፦አጠቃላይ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ የተሰጡን ነገሮች በሙሉ የሚያስጠይቁ ሀብቶች እንደሆኑ የምንማርበት ጊዜ በመሆኑ ሁሉም የሥነ ፍጥረት እና የሃይማኖት ጸጋዎች ሁሉም ሥጦታዎቻችንን
በትክክል ተቀብለን በሕይወታችን ዘመን ሙሉ ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ ልናስረክባቸው ግድ ነው። ይህንን ባናደርግ ግን መክሊት ቀባሪዎች ተብለን እንደምንወቀስ የምንማርበት ነው።

ስለዚህ መክሊቱን የሰጠን አምላክ ተመልሶ መጥቶ ሲጠይቀን ምላሽ እንዳናጣ መክሊትችንን አውጥተን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን አትራፊዎች ልንሆን ይገባል ። “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።”ማቴ.25 ፥ 15

በመጨረሻም የጸጋው ባለቤት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በመጣ እንደየ መክሊታችን አትርፈን እንድንገኝ ይርዳን አሜን

ይቆየን ፣

በዓለ ደብረ ዘይት

ደበረ ዘይት ትርጉሙ ፣ «ደብር » ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «የወይራ ዛፍ » ማለት ነው። ሲገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ ወይም በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። « የወይራ ተራራ ማለት ይሆናል።

– ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ተራራ ሲሆን የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸለየበት ቦታና በኋላም የተያዘበት ቦተ ነው ፣
– ይህ ተራራ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ሥራወቹ የተገለጡበት ቦታ ነው።
– ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ በግልጥ አስተምሯል (ማቴ.24፥3)።
– ከትንሣኤውም በኋላ በዓርባኛው ቀን በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዓርጓል (ሉቃ.24፥50)።
– ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት በዚሁ ተራራ ላይ ያድር ነበር ። በኋለኛው ዘመን በፍጻሜ ዘመን ነገረ ምጽአቱ ወይም በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል።(ዘካ. 14፥3-5)።

– በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ ተእንደተጻፈ፣

– ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው በዚሁ ተራራ ላይ አስተምሯል ።

– ጌታ ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደ ሥራው ለመክፈል በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ይመጣል፡፡
– ጊዜው ፦ ዘመነ ዮሐንስ፣ ወሩ ወርኃ መጋቢት፣ ዕለቱ ዕለተ እሑድ፣ ሰአቱ መንፈቀ ሌሊት፣ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
– ምነው ‹‹ የሚያውቀው የለም ይል የለምን? ቢሉ! ማቴ 24 ÷ 42 እንዲህ ማለቱ ብዙ ፤ የዮሓንስ ዘመን ፤ ብዙ የመጋቢት ወር ፤ ብዙ ዕለተ እሑድ ፤ በዙ ሌሊቶች አሉና በዚህ ቀን ነው ብሎ ለይቶ የሚያውቅ የለም ለማለት ነው፡፡
– ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም ባለ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱን ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሳል፡፡
– እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ገላትያ 6 ÷ 5

– ወንዱ የ30 ዓመት ሴቲቱ የ15 ዓመት ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው ይነሳሉ ማቴ 13፡43 ኃጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን ስለሠሩት መልካም ሥራ ፦ ኑ የአባቴ ቡሩካን ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ኃጥአንን ስለክፉ ሥራቸው ፦ ከኔ ሂዱ ብሎ ወደ ገሃነም ይልካቸዋል፡፡

– ጻድቃን ደስ ይላቸዋል ኃጥአን ግን ያዝናሉ ዋይ ዋይ እያሉ ደረት ይደቃሉ እንባቸውን ያፈሳሉ፡፡ የማይጠቅም ልቅሶ የማይረባ ኃዘን ነው ሰቅለው የገደሉትም አይሁድ ክብሩን አይተው ላይጠቀሙ ይጸጸታሉ፡፡
– እግዚአብሔር በዳግም ምጽአቱ ከሚያዝኑት ጋር ሳይሆን ከሚደሰቱት ፤ ከሚያለቅሱት ጋር ሳይሆን ከሚዘምሩት ከሚያመሰግኑት ጋር እድል ፈንታችንን ያድርግልን ከቅዱሳኑና ከሰማዕታቱ ጋር ለመቆም ያብቃን፡፡

አሜን ይቆየን ፣

መጻጉዕ

መጻጉዕ

የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ የሚዘመረው ዝማሬ የሚነበበው ምንባብ ፣ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚገልጥ በመሆኑ ነው፡፡

«ሠላሳ ስምንት ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው “ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም” አለው። “ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ” ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ “የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ” እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ “በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና “በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ” እያለ ሠላሳ ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ይናገራል

የሕሙማን መታሰቢያ ሳምንት ማለት ነው።
የስያሜው ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
➾ 1ኛ.ለአምስተ ሺህ አምስት መቶ ዘመን በዚህ ዓለም በሥጋ በአካለ ነፍስም በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት እየተረገጡ ይኖሩ የነበሩት ሕሙማነ ሥጋን እና ሕሙማነ ነፍስን የምናስብበት ሰሙን ማለት ነው።
➾ 2ኛ.መድኅን ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ የሆኑትን በማዳን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ያስተማረበትን ዘመን የምናስብበት ነው።
“ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።”ማቴ. 4 ፥ 23 እንዲል።
➾ 3ኛ.ሥግው መለኮት ሕማማችንን ሕማም አድርጎ በዕለተ ዓርብ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን፤በአካለ ነፍስ ወደ ሢኦል ወርዶ ዕዳ በደልን ያጠፋበትን የምናስብበት ነው።በዚህ ዓለም ያለው ደዌ ሥጋ የዚህ ዓለም ምሳሌ ነው።ፈውሰ ሥጋ የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው።
“በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል።”ኢሳ 53 ፥ 4 እንዲል።
➾ 4ኛ.እስከ ዕለተ ምጽአት እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ሕሙማንን ብንችል እየፈወስን ካልቻልን እየጠየቅን የወንጌልን ሕግ እንፈጽም ዘንድ መታዘዛችንን የምናስብበት ሳምንት ነው።”ታምሜ ጠይቃችሁኛልና።”ማቴ. 25 ፥ 36 እንዲል።
5ኛ.ኃጢአትን በንስሐ እያስወገድን ከደዌ ነፍስ እየተላቀቅን እንኖር ዘንድ የምናስብበት ሰሙን ነው።
➢ በኃጢያት መያዝ የደዌ ፦ በንስሐ መታጠብ የፈውስ ምሳሌ ነውና።..
“ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ።”ማቴ. 8 ፥ 4 እንዲል።

ይኸ ሁሉ የክርስቶስ ሥራው፣ መግቦቱ ፣ ቸርነቱ የተቋረጠ አይደለምና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስናስበው ስንፈጽመው እንኖራለን።
“አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ።”ዮሐ. 5 ፥ 17
ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰን አሜን ።

ይቆየን፤

ምኵራብ

ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ፤
ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ፤ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት፤ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት፤አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት፤እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው፤ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ፤ቦአ ምኲራቦሙ ወገሠጾሙ ያርምሙ፤አንከሩ ምሕሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዐ አፉሁ።

ትርጉም
ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ፤የሃማኖት ትምህርትን አስተማረ፤ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው፤የሰንበት ጌታ የይቅርታ አባት እኔ ነኝ፤የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው፤የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት፤ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ወደምኵራባቸው ገባ፤ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው፤ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ የነገሩን ጣዕም የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።
(ቅዱስ ያሬድ)

➾ ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት ፣
ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው

➣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ወደምኵራብ ገባ ነገር ግን በምኵራብ ወርቅና ብር የሚለውጡትን በጉን በሬውን ርግቡን የሚሸጡትን አየ እሱም የአባቴን ቤት ወይም ቤቴ የጸሎት ቤት ነው የጸሎት ቤት ይባላል እናንተ ግን የገበያ አዳራሽ የሌቦች ዋሻ የቀማኞች መሸሻ አደረጋችሁት ብሎ
እየገረፈ አስወጣቸው እና ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው ይላል ለምን እንዲህ አለ ብንል ለመሥዋዕት የሚያቀርቡ ከዚህ እየገዙ ነበር ፣
➢ ለበዓል የሚወጡ ሰዎች ከሩቅ ቦታ የሁለት ቀን የሶስት ቀን የሳምንት ጎዳና እየነዱ መጥተው ሲደርሱ በዚያ ያሉ የጊዜው ነጋዴዎች ይኸማ ከስቷል ቀጥኗል ደክሟል ለመሥዋዕት አይሆንም ይሏቸዋል፣
➣ አና ምን ይሻላል ሲሏቸው እኛጋ የሰባ የወፈረ ያማረ ለመሥዋዕት የሚሆን አለን በሁለት አንድ ለውጣችሁ ወሰዱና ሠው እያሉ ምክንያት እየፈጠሩ ያጭበረብሩ ነበር ጌታ ይህን አይቶ ከመሥዋዕት ይልቅ ለሰዎች ማሰብን ለሰዎች መስጠትን ለሌሎች መራራትን ለሌለው ማካፈልን እወዳለሁ እንጅ እናንተ በማጭበርበር የምትነገዱበትን አይደለም ብሎ እየገረፈ አስወጣቸው ይላል ፣
➾ ስለዚህ ዛሬ ቤተ መቅደሱን ጌታችን ኢየሱስ ያጸዳበት ቀን ነው።
➢ አዎ ቤተ መቅደሱ በነጋዴዎች ተሞልቷል መቅደሱ በሌቦች በአጭበርባሪዎች በአስመሳዮች በግብዞች በውሸታሞች ተሞልቷል መጽዳት ይገባዋል።
መቅደሱ ለታለመለት አላማ ለምስጋና ለጸሎት የተገባ ሊሆን ያስፈልጋል ፣፣
➢ አንድም መቅደስ ሰውነታችን የተለያዩ ችግሮች ነግሠውበታል ውሸት ሐሜት ስርቆት ክፋት ተንኮል ምቀኝነት ዘረኝነት ሌብነት ዝሙት ሱሰኝነት በአጠቃላይ ምልዓተ ኃጢአት ሞልቶታል መጽዳት አለበት ።
➣ አሁን አሁን አብዛኛዎቻችን ሀሳባችን እግዚአብሔር በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ አገልጋዮችን ስለእኛ ሕይወት መጥፋትም ሆነ ለሚሰራው ጥፋት ተጠያቂ በማድረግ እነርሱን እንደ አይሁድ በጅራፍም ሆነ በሥልጣኑ እንዲገሥፃቸው እንፈልጋለን ነገር ግን በሰውነታችን ፣በልቡናችን ላቆምነው ጣኦት፣ሕዋሳቶቻችን ጽድቅን በርኩሰት፣ጾምን በሆዳምነት፣ዕውቀትን በድንቁርና እየለዋወጥን ላለን ሰዎችምኮ ተግሣጽ አለብን ።
ሕዋሳቶቻችንን በምጽዋት ፣ በፆም ፣ በጸሎት፣ በስግደት ያነጻን እንደሆነ እግዚአብሔር ደግሞ ወደ ሕይወታችን የሚገባው በጅራፍ፣በተግሣጽ ሳይሆን በምሕረት በጸጋ ይሆናል እንዲሁም የሚፈታተኑንን ኀጣውእን ፣ ርኩሳትን አጋንንትን ከሰውነታችን ከቤቴ፣ከማደሪያዬ ምዕመን ውጣ በማለት ጠላታችን ኀጢአትን፣ዲያብሎስን ይገሥጽልናል። ሰውነታችን የልዩ ልዩ ክፉ ነገሮች መገበያያ ሆኗልና አምላካችን በመምህራን ትምህርት ፣በካህናት ሥልጣነ ክህነት ፤በምሕረቱ በቸርነቱ ያንጻን፣
እግዚአብሔር መቅደሱን ያጽዳልን ። አሜን

ይቆየን

ቅድስት

“እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ኤፌሶን 5 ÷ 27

የአብይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት የሚከተሉት ናቸው።

  • የቅድስና ትርጉም፡ “ቅድስት” ማለት “የተቀደሰች፣ የተለየች” የከበረች ” ማለት ነው። ይህ ሳምንት በልዩ መንፈሳዊ ትኩረት እና በጸሎት፣ በጾም እና በንስሃ ስለሚታለፍ ቅድስት ተብሎ ይጠራል።
  • በዚ ሳምንት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ የጀመረው የ40 ቀን እና ሌሊት ጾም የሚታሰብበት በመሆኑ ቅድስት ይባላል።
  • ስያሜው ከኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ አስተምህሮ ነው፡፡

ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርት፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ እና ወንጌላቱም ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ፣ የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራው በውስጡ ባለው መንፈሳዊ ትኩረት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ትውስታ እና በቤተክርስቲያን ትምህርት ነው።

ስለዚህ ቅድስት ሲባል የሚጠቁመን እራሳችንን ቁዱስና እና ንጹህ አድርገን በንስሐ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበልን እኔ ቅዱስ ነኘና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዳለ ከሐጢአት ከበደል ከክፋት ከተንኮል ከቂም ከበቀል ከሐሜት ከሐሰት ከምቀኝነት ከዘረኝነት ወጥተን በጎ በጎውን በማሰብ መልካም ሥራ በመሥራት መንፈሳዊ ሰው በመሆን ልንኖር ይገባል ፣አምላካችን መልካሙን ሁሉ እንድናደርግ ይርዳን አሜን ፣

ይቆየን ።

ዘወረደ

“ወአልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ዘውእቱ ይነብር ውስተ ሰማይ።
ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” ዮሐንስ 3 ÷ 13

ዘወረደ ፦ ማለት! ከክብር አንድም ከከፍታ አንድም ከንጽሕና አንድም ከጽድቅ የወረደ የተለየ ማለት ነው ፣ለጌታ ሲሆን ከሰማየ ሰማያት ከልዕልና ከመስቀል የወረደ ማለት ነው ።

እግዚአብሔር አዳምን በጥንተ ተፈጥሮ በልጅነት አክብሮ በቦታ አልቆ በገነት አኑሮት ነበር ነገር ግን ሕግ ባለማክበሩ ከክብሩ ተዋርዷል ፣

  • ከንጽሕና ፦ አዳም በክብር በልጅነት ከብሮ ከሚኖርባት ገነት በኃጢአት ቆሽሾ መውጣቱን ፣ የሰው ልጅ ሰማያዊ መንግሥትን እንዳይወርስ በምድራዊ በኃላፊው በሚጠፋው በሚቀረው ቁሳዊ ዓለም ተጠምዶ በኃጢአት ተውጦ መኖሩን መናገር ነው ፣
  • ከሰማይ፦ በዚህ ሁሉ ምክንያት የተዋረደ አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ የተዋረደውን የአዳምን ሥጋ ለብሶ ሰው መሆኑን አንድም ከልዕልና መውረዱን መናገር ነው ፣

ስለዚህ ወንጌላዊ ከወረደው በቀር የወጣ የለም ሲል ወደ ሲኦል የወረደ አዳም ወደ ገነት ተመልሶ ርስቱን መውረሱን በኃጢአት በበደል የወረደው ወደ ጽድቅ ፣ በውርደት የተሰደደው ወደክብር ፣ በሞት የተቀጣው ወደ ሕይወት ፣ በኀዘን የተዋጠው ወደ ደስታ ፣ በጭንቀት የተያዘው ወደ ሰላም ፣ በፍዳ በመከራ የወደቀው አዳም ወደ ነጻነት ተመለሰ ማለት ነው ።

አንድም ከአደባባይ ወደ መስቀል ፣ ከግዘፍ ወደ ርቀት ከትሕትና ወደ ልዕልና ከከመቃብር ወደ ትንሣኤ ከምድር ወደ ሰማይ የወጣ እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረው በማዕከለ ዓለም የተገለጠው ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው መንግሥቱ ዘለዐለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየሰማያት የወረደው ዝቅ ያለው ከድሆች ጋር የተመላለሰው ከኃጢአተኞች ጋር የተቆጠረው ተዋርዶ የነበረውን ሰው ወደላይ ከፍ ያደረገው በትህትና ውስጥ እየተመላለሰ ነው ፣
የክብር ባለቤ ኢየሱስ ክስቶስ በኃጢአት የተዋረድነውን ሁሉ በመሐሪነቱ በንስሐ ይመልሰን ፣ አሜን ።

ይቆየን