የጥምቀት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በትሮንዳሔም በድምቀት ተከበረ
ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አዘጋጅነት በተካሄደው የጥምቀት በዓል ላይ ከበርገን የመንበረ ልዑል ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከስታቫንገር የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ ከክርስቲያንሳንድ የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ በተጨማሪም ከትሮንዳሔም ቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምእመናን ተገኝተው በዓሉን በጋራ አክብረዋል። በዓሉን ለማክበር ከኦስሎ፣ ከላቫንጋርና ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች፤ ከኖርዌይ ውጭ ደግሞ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከስዊድን፣ ከዴንማርክና ከስዊዘርላንድ ጥሪ የተደረገላቸው አባቶች ካህናት፣ ዲያቆናት እንዲሁም ምዕመናን በበዓሉ ላይ ተካፍለዋል።
በዓሉ ቅዳሜ ከረፋዱ 10፡30 ላይ ሁሉም ካህናትና ዲያቆናት በተገኙበት በጸሎት ተጀምሮ «ዝክረ ተዋሕዶ» በሚል ርእስ በተሰየመ አውደ ርእይ ተክፍቷል። ዝክረ ተዋህዶ አውደ ርእይ አራት ትዕይንቶችን የያዘ ሲሆን በትዕይንቶቹም ውስጥ የቤተክርስቲያን ጉዞ ከሐዋርያት ዘመን እስከ አሁን፣ የሃይማኖት ጸሎትና ታሪካዊነት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዞ በሕገ ልቦና ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል /ከ ፴፬ ዓ.ም እስከ አሁን/፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶችና ሃብቶች እንዲሁም ያበረከተቻቸው አስተዋጽዖዎች፣ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዊ አስተምህሮ፣ አስተዳደራዊ መዋቅር፣ መንፈሳዊ ሥልጣናት፣ ተደራሽነትና ሀብቶቿ፣ የጥምቀት በዓል በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን እና የበዓሉ አከባበር በሃገረ ኖርዌይ፣ ስደትና ክርስትና፣ የስደት መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በአውሮፓ፣ የልጆች አስተዳደግ በአውሮፓ የሚሉ ርእሶችን አካቷል። አውደ ርእዩን ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን አዋቂዎችና ሕጻናት እንዲሁም አንዳንድ ተጋብዘው የመጡ የውጭ ሃገር ዜጎች ያዩት ሲሆን በመጨረሻም አስተያየቶች ጥያቄና መልሶች ተስተናግደው፣ አውደ ርእዮን በማስመልከት ጠለቅ ላለ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ዝክረ ተዋሕዶ በሚል የተዘጋጀው መጽሔት ለአባቶችና ለምእመናን ደርሷል።
ከዚያ በማስቀጠል ከ 15፡00 ሰዓት ጀምሮ የከተራ በዓል በካህናት፣ በዲያቆናትና በምእመኑ የተከበረ ሲሆን በዓሉን የሚያወድስ ወረብ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እንዲሁም የደብሩና የአጎራባች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን በኅብረት ቀርቧል። በመጨረሻም የከተራ በዓልን በተመለከተ አጠር ያለ ትምህርት በመላከ ጽዮን ቆሞስ አባ ሙሴ ተሰጥቶ በቡራኬ ተፈጽሟል።
እኩለ ሌሊት ጀምሮ ማህሌት በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እና በመምህር ኢሳያስ መሪነት በአባቶች፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በሁሉም ደብሮች የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማሕሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። በመቀጠልም የነግህ ኪዳንና የቅዳሴው ስርዓት ተጠናቆ ስርዓተ ጥምቀት ተፈጽሟል። በአጥቢያው መዘምራን ወረብና ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በመጋቤ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴድሮስ ተሰጧል። ከዚህ በመቀጠል ደብሩ ያዘጋጀውን ለጨረታ የቀረበ ባለ አስር አውታር በገና የትሮንዳሔም ቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ጨረታውን ከ፸፬ሺ ክሮነር በላይ በሆነ ዋጋ አሸንፈው ወስደዋል። ከጨረታው በተጨማሪ ሶስት ሽልማቶች ያሉት ዕጣም ወጥቶ ለባለ እድለኞች ተሰጥቷል። ቀጥሎም የሁሉም ደብራት ታቦታት የአዘጋጁን ደብር የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት በየተራ ተሰናብተው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል። በመጨረሻም በአባቶች የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል፤ ካህናቱና ምእመናኑም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።