የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ተከበረ
 
ክርስቶስ ተንስአ እሙታን…….በዐቢይ ኃይል ወስልጣን
አሰሮ ለሰይጣን ………….አግአዞ ለአዳም
ሰላም…………እምይእዜሰ
ኮነ …………….ፍስሀ ወሰላም
 
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ተከበረ።
“እም ሐና ወኢያቄም ተወለድኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ – በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ” – አባ ሕርያቆስ
ሰማይና ምድርን የፈጠረ፣ ፈጥሮም የሚመግብ ንጉሠ ሰማይ ወምድር የሆነን የእግዚአብሔር ቃል ለመቀበል የተገባት ሆና የተገኘች፣ አምላክን የወለደች የባህርያችን(ሰውነት) መመኪያ የሆነች የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ንጽኅተ ንጹኃን ድንግል ማርያም የልደት በዓል ግንቦት ፩፣ ፳፻፰ዓ.ም. (ሜይ 09፥2016) በአጥቢያችን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። መርሐ ግብሩ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ በተዓምረ ማርያም “ሰላም ለኪ ኦ ሐና እማ ለጸሐየ ጽድቅ ወላዲቱ ወምሕየውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ – ጸሐየ ጽድቅ የተባለ ክርስቶስ የምትወልድ እናት እና የጽድቁ ጸሐይ አያት የምትሆኝ ሐና ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ” ተብሎ እንደተመዘገበ የተስፋችን ሁሉ መፈፀሚያ የሆነች እመቤታችንን እና ወላጆቿን ክብር የሚያወሳ ሰፋ ያለ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ መምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማንአየ ተሰጥቷል፤ እመቤታችንን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎችም ተዘምረዋል።
ከመርሐ ግብሩ ፍጻሜ በኋላ ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ደጅ ላይ በመሰባሰብ የተዘጋጀው ጸበል ጸዲቅ ከተቀመሰ በኋላ ዝማሬዎች በማኅበር ተዘምረው ምዕመናን ወደየቤታቸው በሰላም ተሸኝተዋል።
“በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት፤ ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ። ስለሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን።” – ቅዱስ ኤፍሬም
ድንግል ሆይ የልደትሽ ቀን በእውነትም የልደታችን ቀን ነው!