አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

የተወደዳችሁ በዓለም ዙሪያ ያላችሁ ምእመናን ወምእመናት እንኳን ለጾመ ነቢያት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን !!

“ጾምሰ ተከልዖተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ እንዘ ይትኤዘዝ ለዘሐገጎ ለሥርየተ አበሳ ወብዝኀ ዕሤት ፈቃዶ ኪያሁ ከመ ያድክም ኃይለ ፍትወት ወትትአዘዝ ለነፍስ ነባቢት።” ይኽም ማለት ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው። በደሉን ለማስተስረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወድዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ። (ፍት. ነገ.ፍ.መ. አንቀጽ ፲ ወ ፭ቱ ቁጥ ፭፻፺፬)

የቤተ ክርስቲያናችን የሕግ መጽሐፍ እንደሚያስረዳን ጊዜ ወስኖ ወቅት ለይቶ አዋጅ አውጆ ቀኖና ሠርቶ ንስሐ ገበቶ መጾም እንደሚገባ በዚህም በረከት እንዳለው እንረዳለን። ነቢዩ ኢዩኤልም እንዲህ ይለናል፦

” አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቁጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቁርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ፣” ኢዩ ፪ ፥ ፲፪ – ፲፮

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንኑ የነቢያትንና የሐዋርያትን ቃል መሠረት በማድረግ በአዋጅ ከደነገገቻቸው አጽዋማት አንዱ ጾመ ነቢያት (ጾመ ስብከት) (ጾመ ልደት) ተብሎ የሚጠራው ጾም ነው። የዚህ ጾም መሠረት ነቢያት አስቀድመው ስለ ጌታ ወደዚህ ዓለም መምጣት፣ ትንቢት ተናግረው፣ ሱባኤ ቆጥረው ፣ አንስእ ኀይለከ፣ ፈኑ እዴከ፣ስልጣንህን ግለጥ ልጅንህንም ላክልን እያሉ ነገረ ልደቱን (ርደቱን) በመጠባበቅ የጾሙት ጾም ነው ቤተ ክርስቲያንም ቅዱሳን ነቢያትን አብነት በማድረግ ትጾማለች ።

በዚህም መሠረት ቅዱሳን ነቢያት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ሚልክያስና ሌሎችም የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት አስቀድመው በትንቢት ሲገልጹ በጾም፣ በጸሎትና በሱባኤ ነበር። በአጽዋማትና በበዓላት ቀኖናችን መሠረት እነርሱ ተስፋ አድርገው ድኅነቱን ለማየት፣ ቃሉን ለመስማት በትንቢት ተስፋ ያደረጉትን እኛ እንድናየው እንድንሰማው ስለፈቀደልን። ተስፋህን ለመፈጸም፣ ማዳንህን ለማየት፣ ቃልህን ለመስማት ያበቃኸን አምላካችን የልደትህ በረከት ተካፋዮች አድርገን፤ ደስም እናሰኝህ ዘንድ መላእክት በምድር ሰላም ለሰውም እርቅ ሆነ (ሉቃ ፪ ÷ ፲፬) ብለው እንዳመሰገኑህ እኛንም የሰላም ሰዎች አድርገን በኃጢአት የረከሰ ፣ሰውነታችንን፣ በክፋት የደነደነ ልቡናችንን በተንኮል የታጠረ ሕይወታችንን ከኃጢአት ከበደል አንጻን፣ በመሐሪነትህ፣ ማረን፣ ይቅር በለን፣ የቀደመ በደላችንን አታስብብን፣ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን፣ በማለት እንጾማለን።

አባቶቻችን በደነገጉት የበዓላትና የአጽዋማት ቀኖና መሠረት የነቢያት ጾም አርባ ቀን እንዲሆን ደንግገዋል። ፵ው ቀን ጾመ ነቢያት፤ ፫ቱ ቀናት ጾመ አብርሃም ሶርያዊ፤ ፩ ቀን ጾመ ገሐድ በመባል ለ፵፬ ቀናት ይጾማል፣ (እንጾማለን)። የገና ጾመ ገሐድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ ባለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች የገና ገሐድ የለውም ሲሉ ይሰማል ነገር ግን በፍትሕ መንፈሳዊ እንደተገለጠው እስከ የዓርብ ፀሐይ፣ (እስከ ይሠርቅ ኮከብ) በማለቱ ይታወቃል። ፍ.መን. አንድምታ አንቀጽ ፲፭ ÷ ፭፻ ፷፰

ስለዚህ « እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ሐዋርያት ወነቢያት እንዘ ክርስቶስ ርእሰ ማእዘንተ ሕንጻ። ዘቦቱ የኀድር ኵሉ ሕንጻ ወይጸንዕ ጽርሐ መቅደሱ ለእግዚአብሔር ፥ ወአንትሙሂ ቦቱ ተሐነጽክሙ ማኅደረ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ።
፦ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤  በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤ በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።  (ኤፌሶን ፪ ፥ ፳  ) ብሎ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ሁላችንም አባቶቻችን ነቢያትን እና ሐዋርያትን አብነት አድርገን በመጾም በመጸለይና በመስገድ በመመጽወት ለሌሎች በመራራት ራስን በመግዛት ልብንና ሕሊናን በማንጻት ያለኝ ይበቃኛል በማለት ቂም በቀልን በማራቅ፣ ከክፋትና ተንኮል፣ ምቀኝነት በመራቅ በንጹሕ ልብ ጾመን በረከት እንድናገኝ አምላካችን ይርዳን የአባቶቻችን በረከት አይለየን ለሀገር፣ ለወገን ፣ሰላሙን ይላክልን ፣

ሰላመ እግዚአብሔር አይለየን አሜን
ይቆየን
አባ ቀለመወርቅ