ቤተ ክርስቲያናችን መንበረ ፕትርክናው ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር በአስተዳደራዊ መዋቅር መታቀፏን ስለማሳዎቅ
ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅድመ ታሪኩ እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ትሮንዳሄም፣ ኖርዌይ በመጡ ቀናኢ የቤተክርስቲያን ልጆች አማካኝነት በሰንበት ትምህርት ቤትነት ደረጃ በመቋቋም ነበር። ሰንበት ት/ቤት በነበረበት ወቅት እ.ኤ.አ በ2010 ህጋዊ ሆኖ በኖርዌይ ሀገር በሃይማኖት ተቋምነት የተመዘገበ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመባል እ.ኤ.አ በ2012 በአቅራቢያው እየመጡ በሚያገለግሉን አባቶች ተሰይሟል። እ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ በአባቶች ተባርኮ መጥቶ ከሰንበት ትምህርት ቤትነት ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንነት በማደግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተመስርቷል። በዚህ ጉዞዋ ቤተ ክስቲያናችን በዚህ መዋቅር ነኝ ብላ ባታውጅም፤ ከአባቶቻችን እንደተማርነው ያለመዋቅርና ያለስርዓት መጓዝ ጥሩና አግባብ ባለመሆኑ /መዝ. ፻፲፰፥፻፲፰ ፡ ፩ኛ ተሰ. ፭፥፲፬ ፡ ፪ኛ ተሰ. ፫፥፮/ አጥቢያችን በአስተዳደራዊ መዋቅር ስር ገብታ ትተዳደር ዘንድ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያናዊና ሀይማኖታዊ ህግ መሆኑ ግልጽ ነው። ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ይህን ሃይማኖታዊ ስርዓት ሰፊ ጊዜ በመውሰድ የተወያየበት ሲሆን ከአባቶችም ጋር እንደዚሁ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ምዕመናን በጉዳዩ ዙርያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ይህን አጀንዳ በሃይማኖትና በእምነት መነጸር ብቻ እንዲመለከቱት የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እና ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን መተዳደርያ ህግ ይሆን ዘንድ ባወጣው ቃለ ዓዋዲ ላይ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ጥረት ተደርጓል።
ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ህግ አንፃር፣ እንዲሁም ይህች ቤተ ክርስቲያናችን ስትመሰረት ታቦተ ህጋችን በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ከሀገር ቤት እንደመምጣቱ መጠን፤ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ነገሮችን በእርጋታ ተመልክቶ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስር እንድትሆን አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባራውነቱ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም መሰረት በጉዳይ ላይ ከምዕመኑ ጋር ለመነጋገር ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ኅዳር ፳፭፥ ፳፻፰ ዓ.ም ልዩ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በትሮንዳሔም የቤተ ክርስትያን መዋቅርና የቤተ ክርስቲያኗን የበላይ ጠባቂ በግልጽ ስለ ማሳወቅ በሚል ርዕስ አባቶች በተገኙበት አወያይቷል። በዕለቱም ስለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት እንዲሁም ስለቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን በትሮንዳሔም የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ጉዳይ ገለፃ ተሰጥቶ ግልፅ ውይይት ተደርጓል። ጠቅላላ ጉባኤውም የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፕትርክናው ኢትዮጵያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ቤተ ክርስቲያናዊ መዋቅርን ጠብቃና አክብራ መተዳደር አለባት በማለት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል።