በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በትሮንዳሔም የሆሳዕና በዓል በድምቀት ተከበረ።
በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የሆሳዕና በዓል በጸሎት፣ በስብከተ ወንጌል እና በያሬዳዊ ዝማሬዎች እጅግ በርካታ የትሮንዳሔምና የአካባቢው ምዕመናን በተገኙበት በድምቀት ተከበረ።
በዕለቱ “እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ/ ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ” (መዝ. ፰፥፪) ተብሎ እንደተጻፈ የቤተ ክርስቲያን የነገ ተስፋ የሆኑት ሕፃናት እና ታዳጊዎች በጣፈጠ አንደበታቸው በዓሉን የሚያወሱ ዝማሬዎችን አቅርበዋል። በመቀጠልም እለቱን የተመለከተ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተደምድሟል።
በመጨረሻም መርሐ ግብሩን የተሳተፈው ማኅበረ ምእመን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ለበረከት እየቀመሰ በሰላም ወደ ቤቱ ተሸኝቷል።