ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት:- የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑና   ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት እየተባለ ይጠራል። (ማቴ.24÷ 3)

ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬሕይወት”

ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል። የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።” በማለት ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24  ላይ ያለውን ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው ከአሁን በፊት በመጣበት መንገድ  በትሕትና ሳይሆን በልዕልና በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ሳይሆን በምልዓት በስፋት በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ነው። በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል። ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ። ከእናቱ ጡትን እየለመነ ሳይሆን፣ ለፍጥረት ሁሉ  ዋጋ ለመስጠት ። ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ  የሚሸሹለት  ሆኖ  ይመጣል ። የጌታችን ዳግም ምጽአት ፡-

  1. የጸሎታችን መልስ ነው።
  2. የፍጥረት የምጥ ዕረፍት ነው።
  3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
  4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
  5. የእምነታችን ክብር ነው።
  6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
  7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡

1.  የጸሎታችን መልስ ነው:-

ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ። ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው። የምንፈራውና ይቅርብን የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥትህ ትምጣ” እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው። የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው። በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ.14÷17) ። የክርስቶስ መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው። ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው።

2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው:-

ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል። (ሮሜ.8÷19)ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል ቁ.22) ። በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው። እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው። ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግድ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል። የራሱም ዕረፍት ነውና። ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን። ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን። የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።

3.  የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው:-

“ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.22÷20)። ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት ጣር ካየበኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህም ማራናታ አለ። የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው። በመጀመሪያው  ምጽአቱ ሞት እንደ ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱም መከራ ገደብ ያገኛል።

4.  የተስፋችን ፍጻሜ ነው:-

የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡። የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም። ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እንዳያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ቀዱስ ጳውሎስ፡- “የተባረከው ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ.2÷12 13) ይላል። ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ። እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው። የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው። ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው።

5.  የእምነታችን ክብር ነው:-

ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን  እረኛችንን ተከትለን  ወደ ዘለዓለም  ደስታ  እንገባለን።

6.  የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው:-

በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ.21÷1) ። አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው። አሁን ፍጥረት አርጅቷል። በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨለመ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው። ይህን ሁሉ አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት ነው። ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል።

7.  የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው:-

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች። ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ። ገነት ጊዜያዊ የነፍሳት ማረፊያ ናትና። ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ። መንግሥተ ሰማያትና  ገሃነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41) ።
ዘለዓለማዊው  ርስትም  ይከፈታል። ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን።
የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው። ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው። ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል።

የእግዚአብሔር ፍቅርና  ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን
አሜን ።