የሊቀ ሰማዕታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በደመቀ መልኩ ተከበረ

በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፣ ፳፻፯ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ ምእመናን ዓርብ ሚያዚያ ፳፫ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፬ በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ዓርብ እለት ከሰዓት በኋላ በጸሎት የተጀመረ ሲሆን ስለ ቅዱስ ያሬድ በሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ፣ የወንጌል ትምህርት ደግሞ በዲያቆን ብሩክ አሸናፊ ከተሰጠ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ መዘምራን፣ በቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን እንዲሁም በዲያቆን ብሩክ በአሉን የሚያወድሱ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል። በመጨረሻም የማሳረጊያ ትምህርት በመጋቤ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ ተሰጥቶ የዓርብ ከሰአቱ ጉባኤ በጸሎት ተፈጽሟል።

በመቀጠልም ጉባኤው ዓርብ ለቅዳሜ ሌሊቱን በሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ ዲያቆናት፣ የሰ/ት/ ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማሕሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። እንዲሁም የነግህ ኪዳንና የቅዳሴው ስርዓት ሲጠናቀቅ በአጥቢያው መዘምራንና በዲያቆንብሩክ አሸናፊ ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በመልዓከ ጽዮን ቆሞስ አባ ሙሴተሰጥቷል። ከእለቱ ትምህርት በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግስ በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል።

በመጨረሻም በአባቶች በቅርቡ ስለእምነታቸው ሰማዕት ለሆኑ ክርስቲያኖች ጸሎት ካደረሱ እና ምዕመኑ ጧፍ በማብራት እንዲታሰቡ ከተደረገ በኋላ ታቦተ ህጉ ወደመንበረ ክብሩ ተመልሷል። ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት ላደረጋችሁት መንፈሳዊ አስትዋጾ ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓሉን ዝግጅት በፎቶ ይመልከቱ!