በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ  ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ  አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል”
(ቅዱስ ያሬድ)

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በዛሬው ዕለት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ የቅድስት ኢየሉጣ አመታዊ ክብረ በዓል ነው።
በዚህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸው  ታሪክ ይናገራል።

➾ በዘመነ ሰማእታት ከሐድያን ነገሥታትና አላውያን መኳንንት በክርስቲያኖች ላይ መከራ አጽንተውባቸው ነበር። በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሰማእትነትን ሲቀበሉ የተቀሩት ሀገር ጥለው ተሰደዱ።
➾ እየሉጣም የሦስት ዓመት ህፃን ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ይዛ ሸሸች በዚያም በሸሸችበት ሀገር የሸሸችውን መኮንን አገኘችው ሰዎችም ነገር  ሰሩባት ወደእርሱም አስቀረባት እና ስለ አምልኮ ጣዖት ጠየቃት እርሷም መኮንን ሆይ ዕድሜው ሦስት አመት የሆነው ህፃን አለ አማልክቶችህን ማምለክ መልካም እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ያስረዳን ዘንድ እሱን ጠይቅ አለችው።
➾ ከዚህ በኋላ ሕፃኑን አስመጥቶ ቢጠይቀው ነቢዩ ዳዊት የተናገረውን ኃይለ ቃል መንፈስ ቅዱስ ገልጾለት፤
‹‹የአሕዛብ ጣዖታት የወርቅና የብር የሰው እጅ ሥራዎች ናቸው አይን አላቸው ግን አያዩም ጆሮ አላቸው ግን አይሰሙም ………የሚታመኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ››
መዝ. ፻፴፬ ÷ ፲፭ (134 ÷ 15)

በማለት ሲዘልፏቸው  ሰምቶ ተቆጣና የብረት ጋን አስመጥቶ ውኃ አስሞልቶ ከዕቶን እሳት ላይ አስጥዶ ልዩ ልዩ ማገዶዎች  ፣ ጨው፣ ባሩድ፣ ሙጫ ፣ ሰም፣ የዶሮ ማር፣ እርሳስ፣ ብረት፣ ቅንጭብ፣ ቁልቋል ጨምራችሁ አንድዱትና  አፍሉት ብሎ ጭፍሮቹን አዘዛቸው።

«ድምጻ ለጽሕርት ከመ ነጎድጓደ ክረምት» ይላል

ነበልባሉ ከመጠን በላይ ሆነ።  ድምፁም እንደ ክረምት መብረቅና ነጎድጓድ እስኪያስፈራ ድረስ አስነድዶ ሕፃኑን እና እናቱን ወስዳችሁ ጨምሩአቸው ብሎ አዘዘ።
በዚህ ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ ከድምጹ የተነሳ በጣም ፈራች።
የእግዚአብሔር ኃይልና መንፈስ ግን በሕፃኑ ላይ  ስለነበረ ድንቅ ግሩም ረቂቅ በሆነ ተአምር ገና አፉን ያልፈታ የሦስት ዓመት ሕፃን።
«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ  ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ  አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል ”

እያለ ቢያበረታታትም እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ግን ፍርሃቱ ሊለቃት ባለመቻሉ፣ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፡፡
‹‹ጌታ ሆይ! የወይኑን ፍሬ ስትሻ ግንዱን ታጠፋለህን? እንደዚህስ ሁሉ እኔን አድነህ እናቴን ታጠፋታለህን?››

ብሎ በጸለየ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ አደረባትና መንግሥተ ሰማያትን በዓይነ ሥጋ እንድታይ አደረጋት።

ከዚህ በኋላ ፍርሃቱ ለቀቃትና ‹‹ልጄ ሆይ! ከዛሬ ጀምሮ መምህሬ፣ አባቴ፣ መካሪዬ እልሃለሁ እንጂ ልጄ አልልህም›› ብላ በጭካኔ ከልጅዋ ጋር ወደ ፈላው የብረት ጋን ገባች።
➾ በዚህ ጊዜ ሕፃኑ ቂርቆስ አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል እንዳለው ለወዳጆቹ ቅርብ የሆነና በመከራቸው የሚደርስ ጸሎታቸውን የሚሰማ ከመከራ የሚያድናቸው እግዚአብሔር አምላክ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው።
➾ መልአኩም በትእምርተ መስቀል እሳቱን ቢባርከው እንደ በረዶ ቀዘቀዘላቸው። መልካቸውም እንደ ፀሐይ አበራ።
የለበሱት ልብስ ስንኳን ምንም ሳይሆን አንድም ሳይጎዳቸው በደህና ወጡ። በመጨረሻም ሕፃኑ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ እንዲህ አለ።

‟ዘመጠነዝ ገድለ ተጋዲልየ ምንተኑ ተአስየኒ”

“ይህን ያህል ገድል ተጋድዬ ምን ዋጋ ትሰጠኛለህ ቢለው፣”
(ጌታም)  ‟አአስየከ ዘሀሎ ውስተ ልብከ ወአዲ ከመ ኢይማስን ስጋከ ዲበ ሠረገላ ኤልያስ ህየ አነብረከ”

በልብህ ያለውን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው፡፡ ዳግመኛም ሥጋህ በምድር ላይ እንዳይፈርስ እንዳይበሰብስ በኤልያስ ሠረገላ ላይ አኖርሃለሁ አለው።
እንግዲህ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች በዚህ ዕለት  መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእናታችን ለቅድስት ኢየሉጣ እና ለሕፃኑ ለቅዱስ ቂርቆስ ያደረገውን ይህን ታላቅ ተአምር ድንቅ ሥራ በማሰብ እኛንም ከዘመኑ ፈተና እና መከራ እንግልት እንዲጠብቀን ወገናችንን ሕዝባችንን ከስቃይ ከስደት ከሞት እንዲታደግልን ተግተን ልንጸልይ ይገባል።

የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል  ተራዳኢነት የሰማዕታቱ የቅ. ቂርቆስና ቅ. ኢየሉጣ የገድላቸው  በረከት ይደርብን የእግዚአብሔር ቸርነት ከሁላችን ጋር ይኑር አሜን።