እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ  ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ  አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል”
(ቅዱስ ያሬድ)

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በዛሬው ዕለት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ የቅድስት ኢየሉጣ አመታዊ ክብረ በዓል ነው።
በዚህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸው  ታሪክ ይናገራል።

የ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መልእክት

“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት” ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2ጢሞ 3÷1

+ + +

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለ2012 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ በሰላም በጤና አሸጋገረን አሸጋገራችሁ ።

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ሲቆጠር 7512 ዓ/ዓ ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ከወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ከተወለደ ደግሞ 2012 ዓ/ም ይሆናል ።

ማይክሮ – ሰከንዶች – ሰከንዶችን – ሰከንዶች ሰዓታትን – ሰዓታት – ቀናትን – ቀናት-ሳምንታትን – ሳምንታት – ወራትን- ወራት- ዓመታትን እየወለዱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር 64÷12 ላይ ” ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ,, ዓመታትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ (አንድም) የምሕረት አመታትን በቸርነትህ ለሰዎች ታድላለህ ብሎ እንደተናገረ እየተፈራረቁ ዘመናት በዘመናት እየተተኩ ዛሬ ካለንባት ጊዜና ዘመን ደርሰናል ።

ነገር ግን አባቶቻችን ዘመንን የሚቆጥሩት በሕይወት የኖሩበትን ዘመን ነበር እኛ ደግሞ ዛሬ ዘመን በሕይወት የምንኖርበት ሳይሆን በሥጋ የምንኖርበት ብቻ ሁኗል የሰዎች የክፋትም ሆነ የደግነት፣ የመልካም ሥራም ሆነ የክፉ ሥራ ውጤት በዘመን ይገለጣል ለዚህ ነው ሐዋርያው በመጨረሻው ዘመን ያለው እንደ እድል ሆኖ የኛ ዘመን ከመልካም ይልቅ ክፋት የበዛበት ከእውነት ይልቅ ውሸት የሚታመንበት ከፍቅር ይልቅ ጸብ የሚወደድበት ከሰላም ይልቅ ሁከት የሚፈለግበት ከምሕረት ይልቅ መዓት የሚሰማበት ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአት የነገሠበት ከመረዳዳት ይልቅ መገፋፋት የሚቀናበት ከመተሳሰብ ይልቅ መረሳሳት የተለመደበት ከማመስገን ይልቅ መካሰስ የበዛበት ከትእግሥት ይልቅ ቁጣ የፈጠነበት ከትሕትና ይልቅ ትእቢት ከሥራ ይልቅ ስርቆት የሞላበት የመከራው ዘመን ነው ።

ዓለም እንደፈለገ የሚጋልብበት የውድድር ሜዳ አጥር ቅጥሩ የፈረሰበት ዘመን እየሆነ መጥቷል እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ለተፈጠርንለት አላማ ሳይሆን በራሳችን አዙሪት እየተሽከረከርን መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል ጥንቱን ሰው የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነበር እሱም እንደ መላእክት ያለዕረፍታና ያለመታከት ያለድካም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ዓለም ግን መሥመር እየሳተ አቅጣጫ እየቀየረ መንገድ እየለቀቀ ነው ።

ይህንን ነበር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “የሚአስጨንቅ ዘመን እንዲመጣይህንን እወቅ ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ” ብሎ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን በዝርዝ የነገረው ።  ቅዱስ ጳውሎስ ወረድ ብሎ ከቁጥር 14 ላይ እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ቃል መሠረት በማድረግ እንደ ደቀ መዝሙሩ እንደ ጢሞቴዎስ ታዛዦች በመሆን አዲሱና የሚመጣው ዓመት እኛ ተለውጠን ሌሎችን የምንለውጥበት እኛ ከብረን የምናከብርበት ሰርተን ዋጋ የምናገኝበት ያለፈውን ድክመታችንን የምናስተካክልበት ባለፈው ያባከነውን ጊዜ ሐዋርያው ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ እንዳለ በቁጭት የምናስብበት ያስቀየምነውን ይቅርታ የምንጠይቅበት የቀማነውን የምንመልስበት ያጣነውን ሕይወታችንን ፈልገን የምናገኝበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የምንመለስበት ንስሐ ገብተን ባጠፋነው ክሰን የምንችል ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት የማንችል ሁሉን ወደሚችል አምላክ እንዲያስችለንና ለሥጋው ለደሙ እንዲያበቃን በጽኑ እምነት በቁርጥ ኅሊና በጠነከረ ልብ በበረታ ጉልበት ለጾም ለጸሎት የምንዘጋጅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ እንዲአደርግልንም ተግቸ እጸልያለሁ ።

እናንተም እንደ ጢሞቴዎስ በተማራችሁበትና በተረዳችሁበት ነገር ጸንታችሁ እንድትኖሩ አደራ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።

መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመወርቅ

ሊቀ-ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ

በወንድም ይበልጣል ጋሹ

St.George የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት አንስጣስዮስ ከሮም ወደ ፍልስጤም በፈቃደ እግዚአብሔር ሄደ።በዚያም ከክቡራን መኳንንት፣ ከታላላቆች መሳፍንት መካከል አንዱ ነበር። ከፍልስጤም ዕጻ ከምትሆን ድያስ ከተባለች አገር ቴዎብስታ (አቅሌስያ) የምትባል ደግ ሚስት አገባ። የቴዎብስታ የስሟ ትርጓሜ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው። አቅሌስያም እንደ ስሟ የተቀደሰች፣ የተመሰገነች፣ የተባረከች፣ የተመረጠች በብርሃኑ ዓለምን ሁሉ ያበራውን የሰማዕታትን ኮከብ ይሸከም ዘንድ እግዚአብሔር ማህጸኗን የባረከላት ሴት ነበረች።እነዚህ ሁለት ደጋግ የእግዚአብሔር ሰዎችም ዘሮንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ቴዎብስታ (አቅሌሲያ) በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ተጋብተው በህይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ይፈጽሙ ነበር። ጥር 20 ቀን 277 ዓ.ም በሀገረ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ በተባለ ስፍራ ደም ግባቱ ያማረ፣ መልከ መልካም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ወለዱ። በተጨማሪም ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴቶች ልጆችን አፈሩ።

Read more

ያግኙን

እናመሰግናለን

ለሰጡን አስተያየት እናመሰግናለን። አስተያየትዎት ምላሽ የሚያሻ ከሆነ በተቻለን መጠን ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን።

ቅዱስ እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ይባርክ!!!

ስለ እኛ

ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  የትሮንዳሔም ሰንበት ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ኖርዌይ ትሮንዳሔም በመጡ የቤተክርስቲያን ፍቅር ባላቸው ተማሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ ነው። ሰንበት ት/ቤቱ በምስረታው ወቅት ሞሆልት ተብሎ በሚጠራው የተማሪዎች የመኖሪያ  ሰፈር በመጀመሪያ የተማሪዎችን መኖርያ ቤት ቆይቶ ደግሞ ተማሪዎች ለመዝናኛነት ይጠቀሙበት የነበረው የምድር ቤት ለሰንበት መርሐግብር  መሰብሰቢያ ይጠቀም  ነበር።

እ.ኤ.አ  ከ1998 አጋማሽ ጀምሮ የነበረው ጉባኤ የበለጠ እየጠነከረ ቢሄድም  የተማሪዎች የመኖሪያ ህንፃ ውስጥ  መርሐግብሮቹን እስከ ጥር 2007  /እ.ኤ.አ/  ሲያካሄድ ቆይቷል። ይህም ቦታ በመጥበቡ ምክንያት የሰንበት ት/ቤቱ መርሐግብሮች ሞሆልት ሜንገሄስሁስ / Moholt Menighetshus/  ወደሚባል ስፍራ ተዛውሯል። እስከ አሁን ድረስ ይህን ቦታ ለጉባዔ መሰብሰቢያ ይጠቀማል።

ከጉባኤው መስፋት ጋር ተያይዞ ሰንበት ት/ቤቱ በአካባቢው እንዲሁም በስዊድን ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመስረት ችሏል። ይሄም ሰንበት ት/ቤቱ በተለይ በአበይት በዓላት ጊዜ የቅዳሴ አገልግሎት እንዲጀምር አስችሎታል።  የመጀመሪያውን ቅዳሴም ኒዳሮስ ካቴድራል በግንቦት 2001 እ.ኤ.አ አድርጓል። ሰንበት ት/ቤቱ በየአመቱ በሚመረጡ የስራአስፈፃሚ ኮሚቴዎች የሚመራ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2010 በኖርዌይ ሀገር በሐይማኖት ተቋምነት ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት አግኝቷል። 

በአሁኑ ወቅት ሰንበት ትቤቱ በተለያዩ መዋቅሮች ተደራጅቶ አገልግሎቱን አጠናክሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትሮንዳሔም ለመጡ የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎቱን  እየሰጠ ሲሆን ከ 60 የማያንሱ አባላት አሉት።

ሰንበት ት/ቤቱ ከተቋቋመበት  ዋነኛ አላማዎች ውስጥ አንዱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱን እምነትና ስርዓት ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በቤተክርስቲያኒቷ ዕምነትና ስርዓት መሰረት ትምህርተ ወንጌልን ማስተማር፣ ሲሆን ለዚህ አላማ መሳካት በኖርዌይ ሀገር ከሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።

የዘወትር አገልግሎት

ሰንበት ት/ቤቱ ዘወትር እሁድ ከ 10:00 – 12:00 ሰዓት የሚከተሉትን የሰንበት መርሐግብራት ያከናውናል።

  • የማህበር ጸሎት
  • ስብከተ ወንጌል
  • ያሬዳዊ መዝሙርና
  • የተለያዩ ስነ ጽሑፎች

በዓላት

ሰንበት ት/ቤቱ በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ  የዘመን መለወጫ፤ መስቀል፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ስቅለትና ትንሣኤ በዓላት፣ እንዲሁም ደብረዘይት እና ፍልሰታ ማርያምን ያከብራል።  እነዚህን በዓላት ምክንያት በማድረግ በዓመት ቢያንስ አምስት ጊዜ ቅዳሴ ሲኖር በአካባቢዉ ለተወለዱ ህጻናት ጥምቀትና ሌሎች ሚስጢራተ ቤተክርስቲያንን ያከናውናል።