መስቀል – ፳፻፲፰ ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ አደረሰን ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብር የምትሰጠው?
” መስቀል ኃይላችን ነው ፣ ኃይላችን መስቀል ነው ፣ የሚያፀናን መስቀል ነው ፣ መስቀል ቤዛችን ነው ፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው ፣ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነው እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።” /የዘወትር ጸሎት/
“በብሉይ ኪዳን መስቀል የእርግማን ምልክት ና የወንጀለኞች መቀጫ ነበር::” (ዘዳ 21:23) ክርስቶስ በደሙ ስለቀደሰው ግን ቅዱስ መስቀል ተብሏል።
“በመስቀል ድህነትን አግኝተናል። ” (1ኛ. ጴጥ 2: 24-25) ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን በቀራኒዮ የተሰቀለበት ቤዛችን ነው። መስቀል የነጻነታችን ግርማ: የድህነታችን መገኛ: ጠላትን ድል የምንነሣበት መሳሪያችን ነው። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው በጥንቱ ፋርስ (በዛሬዋ ኢራን) ከክርስቶስ ልደት በፊት
(339 – 33) ዓመት ነው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብርን የምትሰጠው?
  1. ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ ራሱን የሠዋበት እውነተኛ መንበር በመሆኑ ፤
  2. የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት: እኛ የዳንበት የነጻነት አርማችን በመሆኑ ፤
  3. የአምላካችን መለኮታዊ ፍቅር የተገለጠበት መሳሪያ በመሆኑ ፤
የመስቀል ዓይነቶች :-
  1. የመጾር መስቀል:- በቅዳሴ እና በማዕጠንት ጊዜ ሠራዒው ዲያቆን የሚይዘው ነው።
  2. የእጅ መስቀል:- ካህናት ምእመናንን የሚባርኩበት በእጅ የምትያዝ የመስቀል ዓይነት ናት።
  3. የአንገት መስቀል:- ምእመናን ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ከማዕተባቸው ጋር በአንገታቸው የሚያደርጉት ነው።
  4. እርፈ መስቀል:- በማንኪያ ቅርጽ ተሠርቶ በእጅታው ላይ የመስቀል ምልክት ያለበት ነው። ሠራዒው ዲያቆን በቅዳሴ ጊዜ የአምላካችንን ክቡር ደሙን ለምእመናን የሚያቀብልበት ነው። እንዲሁም ጌታችን በእለተ አርብ የተወጋበት ጦር ምሳሌ ነው።
መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ይሰራል ። መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ሊሰራ ይችላል። መስቀሉ የሚሰራባቸው ማዕድናት የራሳቸውን ባህርያት እንዳላቸው ሁሉ ምሳሌውን ለመግለጽ ብቁ ናቸው ብለው አባቶች ያስቀመጡትን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
  1. የእንጨት መስቀል:- ጌታችን የተሰቀለው በዕጽ በእንጨት ላይ መሆኑን ለማመልከት ነው።
    ለምን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት ተሰቀለ? አዳም ዕጽ/ እንጨትን በልቶ ሞትን በማምጣቱ ክርስቶስም በእንጨት ተሰቀሎ ህይወትን ሊሰጠን በእንጨት መስቀል ተሰቀለ።
  2. የብረት መስቀል:- ጌታችን በአምስቱ ቅንዋተ ለመቸንከሩ ምሳሌ ነው።
  3. የብር መስቀል:- ይሁዳ በሠላሳ ብር አሳልፎ ስለመስጠቱ። በተጨማሪም ከብር ቢሰራ ተስፋን: ዕድልን ያመለክታል። ይኸውም እርሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ ሊሆን በደሙ ዋጋ ከፍሏልና ከእርሱ ተስፋ እንድናደርግ ያመለክተናል።
  4. የወርቅ መስቀል፦ ከወርቅ ቢሰራ ወርቅ ንጹህ እንደሆነ ንጹሀ ባህርይ እድፈት የሌለው ጽኑ አንተ ነህ ብሎ ለመመስከር ነው።
  5. የመዳብ መስቀል:- መዳብ ቀለሙ ቀይ ይመስላል: ጌታችን ለእኛ ብሎ ያፈሰሰው ደም ምሳሌ ነው።
ብዙዎች የመስቀል ጠላት ሆነው መስቀልን ጣኦት ነው ይላሉ ጣኦት ማለት ግን የሠይጣን ስም የሚጠራበት ፣የሚመለክበት ነው።መስቀል ደግሞ የመድኃኒዓለም ስም የሚጠራበት ህማሙን የሚድኑበት አርማችን፣ ኃይላችን ነው እንጂ መስቀል አምላክ አይደለም። በመስቀል የተሠቀለው ግን አምላክ ነው። ምሳሌ:- ሰው አልጋ ላይ ሲተኛ አልጋ ላይ ተኛ ይባላል እንጂ እንጨቱ ላይ ተኛ አይባልም: ሰው የቤቱን በር ሲዘጋ እጨቴን ልዝጋ አይልም በሩን ልዝጋ ይላል እንጂ: አልጋ አልጋ ይባላል የተሰራው ከእንጨት ሊሆን ይችላል ነገር ግን እንጨት ተብሎ አይጠራም: በርም በር ይባላል እንጂ እንጨት ተብሎ አይጠራም። እንዲሁም ጌታ የተሰቀለበትን መስቀል መስቀል ይባላል ፤እንጂ እንጨት አይባልም።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵ 3÷18-19)
“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” ( ገላ 6:14)
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ” ተብሎ ተጽፎአልና። (1ኛ ቆሮ 1÷18-19)
ልዑል እግዚአብሔር ከመስቀሉ በረከት ያድለን ።
በትሮንድሃይም ከተማ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን የደመራ በዓል እንዲህ ከታች በፎቶ እንደሚታየው በአማረ በደመቀ ሁኔታ አክብረናል እግዚአብሔር ይመስገን ፣፣

አዲስ አመት – ፳፻፲፰ ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
” አሮጌውን ሰው አስወግዱ አዲሱን ሰው ልበሱ ” ኤፌ 4-22
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን አላችሁ? እንኳን ለ2018 ዓ/ም ዘመነ ማርቆስ በሰላም በጤና አደረሳችሁ አደረሰን ።
አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ተተካ ስንል ዓመተ ምሕረቱ አራቱ ወንጌላውያን በየ አራት አመቱ እየተፈራረቁ ዘመናትን ሲመግቡ ይኖራሉ ፣ ስለዚህም ማቴዎስ ሲወጣ ማርቆስ ተተክቶ ዓመቱን ሙሉ ያሳልፋል ማለት ነው ። በዘመነ ማቴዎስ የነበረን ሕይወት ሁሉ ተቀይሮ የቆሸሸው ጸድቶ ያደፈው ታጥቦ የከፋው ቀንቶ የወደቀው ተነስቶ አዲስ ሕይወት እንዲኖረን ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱን ሰው ልበሱ እያለ ይነግረናል ።
ጌታችን መድኃኒታችን እኢየሱስ ክርስቶስም በዮሐንስ ወንጌል 6 ÷ 53 ላይ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ።”
  • ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ ።
  • ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ።
  • ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ ።
በማለት የአዳም ልጅ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶ ሥጋውን ደሙን ተቀብሎ አዲስ ሕይወት እንዲኖረው ያስፈልጋል። አብዛኛው ማኅበረሰባችን የወንጌሉን ቃል በተግባር እየተረጎመው አይደለውም እና ከዛሬ ነገ በማለት በቀጠሮ ጊዜውን ያሳልፋል ፣ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ሳይቀበል መልአከ ሞት በድንገት እንደ ሌባ ደርሶ ሳያስበው ነጥቆ ይወስደዋል ስለዚህ እንደ ቃሉ ልንኖር ያስፈልጋል።
በቀጠሮ ዘመናችን ሳያልቅ ፣ የጭንቅ ቀን ሳይመጣ ፣ ልንመለስ ፣ ልንስተካከል ፣ ልንታረቅ ፣ ልንታጠብ ፣ ልንቀደስ ፣ አዲስ ሕይወት ልንይዝ ይገባል ።
እግዚአብሔር ዘመኑን የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የቅድስና ፣ የለውጥ ፣ የንስሐ ፣ የደስታ ፣ የምስጋና ፣ ዘመን ያድርግልን አሜን ።
መልካም አዲስ አመት !

የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሚያዚያ ፳፭ እና ፳፮ ፥ ፳፻፲፯ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የትሮንድሄም ምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፲፯ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የኢጣልያና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በተገኙበት እንዲሁም በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፭ እና እሁድ ሚያዚያ ፳፮ ፥፳፻፲፯ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

በዓሉ ቅዳሜ ከሰዓት በኃላ የተጀመረ ሲሆን በአባቶች ዋዜማ እንዲሁም በአጥቢያው አዋቂ እና ታዳጊ መዘምራን የተለያዩ ያሬዳዊ ዝማሬዎች የቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የቅዳሜው ጉባዔ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ማሳረጊያና ቡራኬ ተፈጽሟል። ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በአባቶች ካህናት ፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማኅሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። የማኅሌቱ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ የነግህ ኪዳንና የቅዳሴ ስርዓት ተከናውኗል። በመቀጠልም የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ፡ንግሥ በዝማሬና በምስጋና በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ፤ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በብፁዕነታቸው የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉ ላይ የተገኙት ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት እና በረከት አይለያችሁ።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!

ትንሣኤ

“እንደተናገረ ተነስቷል።” ማቴ  28 ፥ 6
ትንሣኤ ማለት ቀጥታ የቃሉ ትርጉም መነሣት ማለት ነው።

ብዙዎቻችንም እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን አደረሳችሁ እያልን እና እየተባባልን  ነው። ፖለቲከኛውም፣ ሰባኪውም፣ ጳጳሱም፣ ዘማሪውም  ዘፋኙም፣  አርቲስቱም፣ አክቲቪስቱም ሁሉም እንኳን አደረሳችሁ እያለ ነው። ጥሩ ነው ፥ ለምን ይባላል ማለት አይገባም ፥ ደስ ይላል ፥ መጠያየቁ  መተሳሰቡ ከልብ ከሆነ !! በሌላ መልኩ መድረስ የሚለው ቃል ናፋቂ ሆኗል ፥ ውሎ መግባት ፣ አድሮ  መገኘት ፣ ተኝቶ መነሳት ፣ ቁሞ መሔድ  ብርቅ የሆነበት ዘመን ላይ ደርሰናል።

➾  ጌታ ተነሣ ስንል እኛም መነሣት አለብን።  ከከፋፋይነት መቃብር ወጥተን  አንድ የሚያደርገን  ሐሳብ  መኖር  አለበት ።

  • በቂም በቀል እና በሴራ መቃብር ውስጥ ሆነን እንኳን አደረሳችሁ ብንባባል  የውሸት የይሁዳ ሰላምታ ይሆናል ።
  • እንደ ይሁዳ በልባችን ፥ ጥላቻ ፥ ፍቅረ  ነዋይ ፥ ቂምና በቀል ፥ ተንኮል ፥ ውሸት ፥ ሐሜት ፥ ሐሰት ፥ ትውዝፍት ፥ ሱሰኝነት ፥ ጣዖትን ፥ ማምለክ ፥  ምዋርት ፥ ጥል ፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት ፥  እያለ  በምንም አይነት መንገድ  የእውነት ሰላምታ ሊሆን አይችልም ስለዚህ  ከመቃብር እንውጣ ።  ያንጊዜ ትንሣኤያችን  በግልጥ  ቅዱሳት አንስት የሚያዩት ሐዋርያት የሚመልከቱት ይሆናል። በመቃብር ሆነን ስለ ትንሣኤ ብናወራ  እውነት አይሆንም  አያምርብንም።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተነሣ እኛም  በትንሣኤ ልቡና እንነሣ። የዘረኝነት፣ የውሸት፣ የጥላቻ፥ የበቀል፣ የሐሜት፣ የከንቱ ውዳሴ፣ የትዕቢት፣ የራስ ወዳድነት መቃብርን ፈንቅለን እንውጣ  ፣ በአፋችን እንኳን አደረሳችሁ እየተባባልን በልባችን ግን ቀጣይ ዓመት እንዳንደርስ እየተገዳደን ከሆነ ግን ይሁዳነት ነው። ይሁዳ ጌታን የሸጠው በአፉ ሰላም እያለ ነው ። ሁሉም ከተንኮል፣ ከሽንገላ መቃብር ይውጣ እና የፍቅር ትንሣኤን ይነሣ። እግዚአብሔር  የፍቅር  ትንሣኤ እንድናከብር አምላካችን ያድለን።

«እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና፡— ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ፥ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው።»  የማቴዎስ ወንጌል 28:6-7

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም በጤና አደረሳችሁ!  አሜን ።

ይቆየን።

ጸሎተ ሐሙስ

ጸሎተ ሐሙስ ክርስቶስ አምላካችን ራሱን ዝቅ አድርጎ የሐዋርያትን እግር ያጠበበት ዕለት ነው፡፡

በሕማማት ውስጥ ያለው ይህ ሐሙስ በተለያዩ ስያሜዎች ይጠራል፡፡

አንደኛ፦ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኀብስቱን በባረከ ጊዜ ስለጸለየ፤  እና  ከመያዙ አስቀድሞ በጌቴሴማኒ  ደቀ መዛሙርቱ ተኝተው እርሱ ግን  ተንበርክኮ  አባት ሆይ ብትወድስ ይች ጽዋ ከእኔ ትለፍ እያለ በሰው ልጆች  (በአዳም ልጆች) ተገብት ጸልዮልናል ፡፡
ሁለተኛው፦ትዕዛዝ ሐሙስ ይባላል ፡ ምክንያቱም ከኀጽበተ እግር በኋላ ጌታ እናንተም እንዲሁ አድርጉ ብሎ  አዝዟቸዋልና ነው ከዚያም ቀጥሎ በጌቴሴማኒም  ጌታ ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ ብሎ አዝዟቸዋል፤
ሦስተኛ፦ የምሥጢር ቀን ይባላል ፡ ሥርዓተ ቁርባንን ከሠራ በኋላ /ከመዝ ግብሩ ተዝካርየ/ ብሎ አዝዟል  እንዲሁም በዚህ ዕለት የተሰጡትን ሌሎችንም ትዕዛዛት ለማስታወስ ነው፡፡
አራተኛ፦ ኀጽበተ እግር  ሐሙስ ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ቀን ጌታ የደቀመዛሙርቱን እግር ስላጠበ ባዘዘንም መሠረት ዛሬ በቤተክርስቲያን መታሰቢያውን እናደርጋለን ፡፡
አምስተኛ፦የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡ በዚሁ ቀን ምሽት ጌታችን ‹‹ ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፡— እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው» አለ። ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ፡— ‹‹ ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።» (ማቴ.26:28) በማለት የሰጠንን ዘለዓለማዊ ኪዳን የሚያስታውስ ስያሜ ነው፡፡

ጌታችን ተጠምቆ ተጠመቁ ፣ ጾሞም ጹሙ እንዳለን ፣ ጸልዮ ጸልዩ፤ ሰግዶም ስገዱ ሲለን እንደዚሁም የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ አርአያነቱን ሲያሳየን መምህረ ትሕትናነቱን ሲገልጥልን ነው፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱና ካህናቱ ሁሉም በየመዓርጋቸው የምእመናኑን እግር ዝቅ ብለው የሚያጥቡት የጌታን የትሕትና ሥራ ለማሰብ ነው፡፡

በዚህም መሠረት ይህንን ሥርዓቱን አብነት በማድረግ በዚች ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የሕፅበተ እግር ሥርዓቱ በሚከናወንበት ጊዜ ዲያቆኑ ውኃን ያቀርባል፤ በቀረበውም ውኃ ላይ ጸሎተ አኰቴት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነብቦ ውኃው በካህኑ ወይም በሊቀ ጳጳሱ እጅ ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓቱ ከካህናት እስከ አናጕንስጢስ እንደዚሁም ከወንዶች እስከ ሴቶች ላሉት ምእመናን ሁሉ በካህናቱ እጅ ይከናወናል፡፡

ከበዓሉ በረከት  ያድለን አሜን፡፡

ሆሣዕና

ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሣዕና”  ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ክንፋቸው ትእምርተ መስቀል የሚሠራው ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዓድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት ጌታ በትሕትና ኾኖ  በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡

ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲሆን  በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡

ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ሁሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡ አህያዋ የሕዝቡ  ውርንጫዋ የአሕዛቡ ምሳሌ ናቸው፡፡

ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋል።

አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ። ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ በማለት መተርጉማን ይተነትናሉ፡፡ በተጨማሪም ልብስ በልጅነት ይመሰላልና የተገፈፍነውን የጸጋ ልብሳችን (ልጅነትን) ትመልስልናለህ ሲሉ ነው፡፡

ዛሬም  በኃጢአት  ክፋት በተንኮል በምቀኝነት በዘረኝነት  የተገፈፈ  ጸጋችንን በጽድቅ  በምሕረት በደግነት  በፍቅር  ይመልስልን አሜን ፡፡

ኒቆዲሞስ

ኒቆዲሞስ የዓቢይ ጾም  ሰባተኛ ሳምንት  ሲሆን ስያሜው  ኒቆዲሞስ በተባለ የአይሁድ አለቃ በነበረ ሰው ስም ተሰይሟል፡፡

“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤” ዮሐ 3-1

በዕለቱ በሚነበበው በዚህ  የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ ጥያቄና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ይገልጽልናል።

“ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው” ዮሐ 7-51
ቀን ቀን ከአይሁዳውያን ጋር ሲያስተምር ይውላል  ማታ ማታ  ዕውቀቱን ለማስፋት ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ሲማር ያድራል  አለቅነትን ከመምህርነት  ዕውቀትን ከትህትና   አስተባብሮ የያዘ ሰው ነበር ፣

“የምስጢረ ጥምቀት መገለጥም  ምክንያት የሆነ  እና  ምስጢረ ጥምቀትን  ከባለቤቱ ጠይቆ የተረዳ  ሰው ነው ”  ዮሐ 3  ÷ 1-21
አንዳንዴ ሳያውቁ አዋቂ ነን  ሳይማሩ መምህር ነን እናስተምር ለሚሉ ደፋር  መምህራን  ኒቆዲሞስ  ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል፣ የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡ በዚህ ሰዓት ኒቆዲሞስ ጊዜ አላጠፋም ክብሩም አላስጨነቀውም መምህርነቱም  አልገደበውም በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ ፤ በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን ።» ብሎ  እራሱ  ዝቅ አድርጎ በትህትና  ቀረበ።

ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደ ሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን  አላወቁም የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡

ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ድረስ ከአንተ አንለይም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር፣ በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን  ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ  ነበር፡፡

ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?
ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ  ራሳችንን ጠምደን  የመማር አቅም አጥተናል፡፡  ቁጭ ብሎ መማር  ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ  ስንቶች እንሆን?

አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ፣ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ  እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን በመጽሐፍ ተጽፎ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ እኛስ ያወቅነውን እያሳወቅን ያላወቅነውን ብንማር  ምን ችግር አለው?  ይኸ አልሳካ ያለን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን?  ትሑት የሚያሰኘው  ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ  ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡   ኒቆዲሞስ ግን  ፈሪሳዊ ፣ የአይሁድ አለቃ ፣ መምህር ፣ ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ከመምህራን ስር ቁጭ  ብሎ መማር መታደል ነው
እኛም በምሕረቱ አደባባይ ተገኝተን በጌታ ፊት ቁጭ  ብለን  ቃሉን ለመስማት ያብቃን አሜን ።

ይቆየን፤

ገብር ኄር (መልካም አገልጋይ)

ከደብረ ዘይት ቀጥሎ ያለው ስድስተኛው የዓቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ገብር ኄር ይባላል። መልካም አገልጋይ ቸር ርኅሩኅ ማለት ነው። ይህ ዕለት መልካም አገልጋዮች በትጋታቸው የሚወደሱበት ሰነፍ አገልጋዮች ደግሞ በስንፍናቸው የሚወቀሱበት ዕለት ነው።

ስያሜውን ያገኘው፦
አንደኛ፦በብሉይ ዘመናት የነበሩ መልካም አገልጋዮቹ ነቢያትና እና ካህናት በአጠቃላይ ምእመናነ ብሉይ የአገልግሎት እና የመልካም አገልጋይነት ዋጋቸውን አግኝተው እንደምን እንደ ተመሰገኑ እነሱንና መልካም ስራቸውን የምናስብበት ዕለት ነው።

ሁለተኛው፦የትሩፋተ ሥጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪው መድኅን ክርስቶስ በተገዥ ሰውነት ተገልጦ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተመላልሶ በሕጻንነቱ ለእናቱ ለዘመዶቹ ኋላም ለሁሉም ሰው አርአያ በመሆን በሰውነቱ ማገልገሉን የምናስብበት ነው።”

የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ማቴ.20 ፥ 28 ። አርአያነት ማለት!! የትህትና ሥራውን በገለጸበት በምሴተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡም ከዚህ የተነሣ ነውና።
ስለዚህ ይኸ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነት ተልእኮ የምናስብበት ሳምንት ነው።

ሦስተኛ፦ቅዱሳን ሐዋርያት እና ተከታዮቻቸው በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው በሠሩት መልካም የወንጌል አገልግሎት የተልእኮ ሥራቸው “ቸር አገልጋዮች ተብለው ታማኝነታቸው ፣ ትሩፋታቸው፣ ክብራቸው የሚነገርበት ሳምንት ነው።

አራተኛ፦አጠቃላይ ምእመናን በተሰጣቸው የተፈጥሮ ጸጋ እና የእምነት ጸጋ፣የትሩፋተ ሥጋ፣የትሩፋተ ነፍስ ጸጋ፦ሥራ ሠርተው የጸጋ መክሊታቸውን አብዝተው አትርፈው ቢገኙ የሚመሰገኑበት ሳምንት ነው።

አምስተኛ፦በተፈጥሮ በተሰጣቸው ጸጋ እና በሃይማኖት በሹመት በተሰጣቸው ጸጋ ምግባር ትሩፋት መሥራት ሲገባቸው በስንፍና፣በፍርሀት ተሸብበው የኖሩ ሰነፍ ሰዎችም የሚወቀሱበት ሳምንት እና ክፍለ ጊዜ ነው።

ስድስተኛ፦አጠቃላይ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ የተሰጡን ነገሮች በሙሉ የሚያስጠይቁ ሀብቶች እንደሆኑ የምንማርበት ጊዜ በመሆኑ ሁሉም የሥነ ፍጥረት እና የሃይማኖት ጸጋዎች ሁሉም ሥጦታዎቻችንን
በትክክል ተቀብለን በሕይወታችን ዘመን ሙሉ ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ ልናስረክባቸው ግድ ነው። ይህንን ባናደርግ ግን መክሊት ቀባሪዎች ተብለን እንደምንወቀስ የምንማርበት ነው።

ስለዚህ መክሊቱን የሰጠን አምላክ ተመልሶ መጥቶ ሲጠይቀን ምላሽ እንዳናጣ መክሊትችንን አውጥተን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን አትራፊዎች ልንሆን ይገባል ። “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።”ማቴ.25 ፥ 15

በመጨረሻም የጸጋው ባለቤት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በመጣ እንደየ መክሊታችን አትርፈን እንድንገኝ ይርዳን አሜን

ይቆየን ፣

በዓለ ደብረ ዘይት

ደበረ ዘይት ትርጉሙ ፣ «ደብር » ማለት «ተራራ» ማለት ሲሆን «ዘይት» ማለት ደግሞ «የወይራ ዛፍ » ማለት ነው። ሲገናኝ «ደብረ ዘይት» ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ ወይም በወይራ ደን የተሸፈነ ተራራ ማለት ነው። « የወይራ ተራራ ማለት ይሆናል።

– ደብረ ዘይት ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኝ ተራራ ሲሆን የጸሎተ ሐሙስ ማታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጸለየበት ቦታና በኋላም የተያዘበት ቦተ ነው ፣
– ይህ ተራራ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኙ ብዙ ሥራወቹ የተገለጡበት ቦታ ነው።
– ጌታችን ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ ዓለም ፍጻሜና ስለ ዳግም ምጽአት በዚህ ተራራ ላይ በግልጥ አስተምሯል (ማቴ.24፥3)።
– ከትንሣኤውም በኋላ በዓርባኛው ቀን በዚሁ ተራራ ላይ ወደ ሰማይ ዓርጓል (ሉቃ.24፥50)።
– ቀን በከታማና በገጠር ሲያስተምር ውሎ ሌሊት በዚሁ ተራራ ላይ ያድር ነበር ። በኋለኛው ዘመን በፍጻሜ ዘመን ነገረ ምጽአቱ ወይም በዚሁ ቦታ እንደሚገለጥ ትንቢት ተነግሯል።(ዘካ. 14፥3-5)።

– በዚህ ተራራ ላይ «እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት» (ማቴ.24፥3)። ተብሎ ተእንደተጻፈ፣

– ለደቀ መዛሙርቱ የዳግም ምጽአቱን፣ የዓለምን ፈጻሜ፣ የትንሣኤ ሙታንን፣ ትምህርት በሰፊው በዚሁ ተራራ ላይ አስተምሯል ።

– ጌታ ይህንን ዓለም ለማሳለፍ ለሁሉም እንደ ሥራው ለመክፈል በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ይመጣል፡፡
– ጊዜው ፦ ዘመነ ዮሐንስ፣ ወሩ ወርኃ መጋቢት፣ ዕለቱ ዕለተ እሑድ፣ ሰአቱ መንፈቀ ሌሊት፣ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
– ምነው ‹‹ የሚያውቀው የለም ይል የለምን? ቢሉ! ማቴ 24 ÷ 42 እንዲህ ማለቱ ብዙ ፤ የዮሓንስ ዘመን ፤ ብዙ የመጋቢት ወር ፤ ብዙ ዕለተ እሑድ ፤ በዙ ሌሊቶች አሉና በዚህ ቀን ነው ብሎ ለይቶ የሚያውቅ የለም ለማለት ነው፡፡
– ንቃሕ መዋቲ ዘትነውም ባለ ጊዜ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ደጉ ደግነቱን ክፉውም ክፋቱን ይዞ ይነሳል፡፡
– እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ሊሸከም ነውና። ገላትያ 6 ÷ 5

– ወንዱ የ30 ዓመት ሴቲቱ የ15 ዓመት ሆነው ጻድቃን ብርሃን ለብሰው ብርሃን ተጎናጽፈው ከፀሐይ 7 እጅ አብርተው ይነሳሉ ማቴ 13፡43 ኃጥአን ጨለማ ለብሰው ፍጹም ዲያብሎስን መስለው ይነሳሉ፡፡ ጻድቃን ስለሠሩት መልካም ሥራ ፦ ኑ የአባቴ ቡሩካን ብሎ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል፡፡ኃጥአንን ስለክፉ ሥራቸው ፦ ከኔ ሂዱ ብሎ ወደ ገሃነም ይልካቸዋል፡፡

– ጻድቃን ደስ ይላቸዋል ኃጥአን ግን ያዝናሉ ዋይ ዋይ እያሉ ደረት ይደቃሉ እንባቸውን ያፈሳሉ፡፡ የማይጠቅም ልቅሶ የማይረባ ኃዘን ነው ሰቅለው የገደሉትም አይሁድ ክብሩን አይተው ላይጠቀሙ ይጸጸታሉ፡፡
– እግዚአብሔር በዳግም ምጽአቱ ከሚያዝኑት ጋር ሳይሆን ከሚደሰቱት ፤ ከሚያለቅሱት ጋር ሳይሆን ከሚዘምሩት ከሚያመሰግኑት ጋር እድል ፈንታችንን ያድርግልን ከቅዱሳኑና ከሰማዕታቱ ጋር ለመቆም ያብቃን፡፡

አሜን ይቆየን ፣

መጻጉዕ

መጻጉዕ

የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ የሚዘመረው ዝማሬ የሚነበበው ምንባብ ፣ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚገልጥ በመሆኑ ነው፡፡

«ሠላሳ ስምንት ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው “ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም” አለው። “ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ” ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ “የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ” እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ “በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና “በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ” እያለ ሠላሳ ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ይናገራል

የሕሙማን መታሰቢያ ሳምንት ማለት ነው።
የስያሜው ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
➾ 1ኛ.ለአምስተ ሺህ አምስት መቶ ዘመን በዚህ ዓለም በሥጋ በአካለ ነፍስም በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት እየተረገጡ ይኖሩ የነበሩት ሕሙማነ ሥጋን እና ሕሙማነ ነፍስን የምናስብበት ሰሙን ማለት ነው።
➾ 2ኛ.መድኅን ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ የሆኑትን በማዳን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ያስተማረበትን ዘመን የምናስብበት ነው።
“ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።”ማቴ. 4 ፥ 23 እንዲል።
➾ 3ኛ.ሥግው መለኮት ሕማማችንን ሕማም አድርጎ በዕለተ ዓርብ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን፤በአካለ ነፍስ ወደ ሢኦል ወርዶ ዕዳ በደልን ያጠፋበትን የምናስብበት ነው።በዚህ ዓለም ያለው ደዌ ሥጋ የዚህ ዓለም ምሳሌ ነው።ፈውሰ ሥጋ የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው።
“በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል።”ኢሳ 53 ፥ 4 እንዲል።
➾ 4ኛ.እስከ ዕለተ ምጽአት እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ሕሙማንን ብንችል እየፈወስን ካልቻልን እየጠየቅን የወንጌልን ሕግ እንፈጽም ዘንድ መታዘዛችንን የምናስብበት ሳምንት ነው።”ታምሜ ጠይቃችሁኛልና።”ማቴ. 25 ፥ 36 እንዲል።
5ኛ.ኃጢአትን በንስሐ እያስወገድን ከደዌ ነፍስ እየተላቀቅን እንኖር ዘንድ የምናስብበት ሰሙን ነው።
➢ በኃጢያት መያዝ የደዌ ፦ በንስሐ መታጠብ የፈውስ ምሳሌ ነውና።..
“ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ።”ማቴ. 8 ፥ 4 እንዲል።

ይኸ ሁሉ የክርስቶስ ሥራው፣ መግቦቱ ፣ ቸርነቱ የተቋረጠ አይደለምና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስናስበው ስንፈጽመው እንኖራለን።
“አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ።”ዮሐ. 5 ፥ 17
ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰን አሜን ።

ይቆየን፤