የ ፳፻፱ ዓ.ም መስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ተከበረ፤ የ፫ ቀናት መንፈሳዊ ጉባዔም ተካሄደ
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሃገረ ስብከት የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ከኢትዮጵያ ወደ አውሮጳ በመጡትና ወደ አጥቢያችን የመስቀልን በዓል ለማክበር በተጋበዙት መምህር ፍቃዱ ሳህሌ የ፫ ቀናት ጉባዔ ተካሄደ። ቅዳሜ፣ እሁድ እንዲሁም ማክሰኞ (ከመስከረም ፲፬ – ፲፯) በተካሄደው ጉባዔ ላይ በተለያዩ ርዕሶች መንፈሳዊ ትምህርት ለትሮንዳሔምና አካባቢው ምዕመናን የተሰጠ ሲሆን ከምዕመናን በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ምክረ አበው በማክሰኞው ጉባዔ ተሰጥቷል።
በተያያዥነትም ሰኞ፣ መስከረም ፲፮፥፳፻፱ ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል መምህር ፍቃዱ ሳህሌ፣ የአጥቢያው የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና ምዕመናን እንዲሁም ከኤርትራ ቅዱስ ሚካኤል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመጡ ካህናትና ዲያቆናት፣ መዘምራንና ምዕመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በዓሉ ሰኞ እለት ከሰዓት በኋላ 17:30 ላይ በካህናት አባቶች ጸሎት እንዲሁም ወረብ የተጀመረ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በዓሉን የተመለከቱ መዝሙራትን አቅርበዋል። በመቀጠልም በዓሉን የተመለከተ የወንጌል ትምህርት በመምህር ፍቃዱ ሳህሌ ከተሰጠ በኋላ ደመራው በቀሲስ ተስፋዬ ተባርኮ ተለኩሷል። መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል። በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።
በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽኦ ላበረከታችሁ ምዕመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።