ሆሣዕና
ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ነው፤ “ሆሣዕና” ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ክንፋቸው ትእምርተ መስቀል የሚሠራው ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዓድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት ጌታ በትሕትና ኾኖ በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕፃናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ የተጻፈ ሲሆን በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል፡፡
ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ናት፤ ሁሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታም ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” በማለት እንደ ማዕምረ ኅቡአትነቱ (የተሰወረውን ዐዋቂነቱ) በመንደሯ ውስጥ ስለታሰሩት አህያና ውርንጫ አስቀድሞ ነግሯቸዋል፡፡ አህያዋ የሕዝቡ ውርንጫዋ የአሕዛቡ ምሳሌ ናቸው፡፡
ከዚያም “ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ጌታ ርሱ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም እንዲያመጡ አዟቸዋል።
አምጥተው “ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”፤ በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ። ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ በማለት መተርጉማን ይተነትናሉ፡፡ በተጨማሪም ልብስ በልጅነት ይመሰላልና የተገፈፍነውን የጸጋ ልብሳችን (ልጅነትን) ትመልስልናለህ ሲሉ ነው፡፡
ዛሬም በኃጢአት ክፋት በተንኮል በምቀኝነት በዘረኝነት የተገፈፈ ጸጋችንን በጽድቅ በምሕረት በደግነት በፍቅር ይመልስልን አሜን ፡፡