ብርሃን

የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ብርሃን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት የነበሩበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው። በዚህ ሳምንት ከዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ዘመን ( 14 ትውልድ) ይታሰብበታል፡፡

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከአስተማሩባቸውና፣ ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣ “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ 42፡3) በማለት ይጸልይ ነበር፡፡ ይህም ማለት ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድን) ላክልን፤ እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው (ኢሳ 49)፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ እውነተኛ ብርሃን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት አስረግጦ ይነግረናል፣ (ዮሐ 1፡1-11)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ 8:12) ብሎ ስለ እርሱ እውነተኛ ብርሃንነትና አምላክነት በሚገባ አስተምሯል፡፡

በዚህ ዕለት ‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን›› እንዲሁም ‹‹የማይነገር ብርሃን›› የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ አስረግጦልናል፡፡ ‹‹ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ እንዳስተማረን። ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ‹‹በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ፤ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና። የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን፤ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን የሕይወታችን ብርሃን የሆነውን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ረድኤቱን ይላክልን ፣ አሜን ፣