የጌታችን ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

&nbsp

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

ሞተ ወኬዶ ለሞት

ለእለ ውስተ መቃብር

ወሀበ ሕይወተ ዘለዓለመ ዕረፍተ።

&nbsp

&nbsp

የ፳፻፰ ዓ.ም የጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም በድምቀት ተከበረ። በዓላቱ በአባታችን አባ ገብረ ማርያም ቢምረው እና መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ማንአየ መሪነት እና በርካታ ቁጥር ባለው ምእመን ሱታፌ በተለያዩ አገልግሎቶች ተከብረዋል።

ዕለተ አርብ ሚያዝያ ፳፩፥፳፻፰ ዓ.ም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታችንን ስቅለት በሚያወሱ ምንባባት፣ ሕማሙን በሚዘክሩ ጸሎቶች እንዲሁም በስግደት ያለፈ ሲሆን፤ “አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ይልቅ ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል” እንደተባለ የጌታችንን ረቂቅ የማዳን ሥራ እና ነገረ-መስቀሉን በተመለከተ በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ትምህርት ተሰጥቷል።

ቅዳሜ ማለዳ ለቀዳም ስዑር እለት የሚደረጉት ጸሎትና ምንባባት ከተከናወኑ በኋላ ቀኑን የተመለከተ አጠር ያለ ትምህርት በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረሥላሴ ተሰጥቶ የማለዳው መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።

ቅዳሜ ምሽት ከ 22:00 ሰዓት ጀምሮ የጌታችንን ትንሳዔ የሚያወድስ ሥርዓት ከምንባባትና ወረቦች ጋር ከተከናወነ በኋላ በኪዳንና በሥርዓተ ቅዳሴ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን የጾም መፈሰኪያ ጸበል ጸዲቅ እየቀመሰ ወደየቤቱ በሰላም ተመልሷል።

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ!