ኖላዊ

የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ‹‹ኖላዊ›› ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት ‹‹እረኛ›› ወይም ‹‹ጠባቂ›› ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ቅዱሳን ነቢያት አምላክ ወልደ አምላክ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው ትንቢት መናገራቸው እና ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ኖላዊ ዘበአማን እውነተኛ ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቤተክርስቲያናችን የምታስተምርበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ፤ ብሎም ዓለምን ፤ እንደ በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ ይታሰባል። ቤተክርስቲያን ፦

“ ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አፅምእ፤
ዘይርዕዮሙ ከመ አባግዕ ለዮሴፍ፤
ዘይነብር ላዕለ ኪሩቤል አስተርአየ።
በቅድመ ኤፍሬም ወብንያም ወምናሴ፤
አንሥእ ኀይለከ ፥ ወነዐ አድኅነነ።

እረኛ የሌለው የበግ መንጋ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ 79፡1) በማለት ይማፀኑ እንደ ነበር ታስተምራለች።

ቸር ጠባቂ: የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል›› ዮሐ፣ 10፥11 በማለት እውነተኛ አእረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል። ስለራሱም ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።›› ዮሐ 10፡15 በማለት አስተምሯል፡፡

በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ (22፡1) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተበትነናልና ሰብስበን ጠፍተናልና ፈልገን አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ሁሉን ወደ ሚችል ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

ከተኩላዎች ተጠበቁ: ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› ብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛና ምንደኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ ስለበጎቹም ይገደዋል ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። (ማቴ 7፡15)፡ ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው እየታገሉ ነው ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል ከቅዱሳን ነቢያት በረከት ያድለን አሜን፣

ወስብሐት ለእግዚአብሔር