ስለ እኛ

ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  የትሮንዳሔም ሰንበት ትምህርት ቤት እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ኖርዌይ ትሮንዳሔም በመጡ የቤተክርስቲያን ፍቅር ባላቸው ተማሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ ነው። ሰንበት ት/ቤቱ በምስረታው ወቅት ሞሆልት ተብሎ በሚጠራው የተማሪዎች የመኖሪያ  ሰፈር በመጀመሪያ የተማሪዎችን መኖርያ ቤት ቆይቶ ደግሞ ተማሪዎች ለመዝናኛነት ይጠቀሙበት የነበረው የምድር ቤት ለሰንበት መርሐግብር  መሰብሰቢያ ይጠቀም  ነበር።

እ.ኤ.አ  ከ1998 አጋማሽ ጀምሮ የነበረው ጉባኤ የበለጠ እየጠነከረ ቢሄድም  የተማሪዎች የመኖሪያ ህንፃ ውስጥ  መርሐግብሮቹን እስከ ጥር 2007  /እ.ኤ.አ/  ሲያካሄድ ቆይቷል። ይህም ቦታ በመጥበቡ ምክንያት የሰንበት ት/ቤቱ መርሐግብሮች ሞሆልት ሜንገሄስሁስ / Moholt Menighetshus/  ወደሚባል ስፍራ ተዛውሯል። እስከ አሁን ድረስ ይህን ቦታ ለጉባዔ መሰብሰቢያ ይጠቀማል።

ከጉባኤው መስፋት ጋር ተያይዞ ሰንበት ት/ቤቱ በአካባቢው እንዲሁም በስዊድን ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመመስረት ችሏል። ይሄም ሰንበት ት/ቤቱ በተለይ በአበይት በዓላት ጊዜ የቅዳሴ አገልግሎት እንዲጀምር አስችሎታል።  የመጀመሪያውን ቅዳሴም ኒዳሮስ ካቴድራል በግንቦት 2001 እ.ኤ.አ አድርጓል። ሰንበት ት/ቤቱ በየአመቱ በሚመረጡ የስራአስፈፃሚ ኮሚቴዎች የሚመራ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2010 በኖርዌይ ሀገር በሐይማኖት ተቋምነት ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት አግኝቷል። 

በአሁኑ ወቅት ሰንበት ትቤቱ በተለያዩ መዋቅሮች ተደራጅቶ አገልግሎቱን አጠናክሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትሮንዳሔም ለመጡ የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎቱን  እየሰጠ ሲሆን ከ 60 የማያንሱ አባላት አሉት።

ሰንበት ት/ቤቱ ከተቋቋመበት  ዋነኛ አላማዎች ውስጥ አንዱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱን እምነትና ስርዓት ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በቤተክርስቲያኒቷ ዕምነትና ስርዓት መሰረት ትምህርተ ወንጌልን ማስተማር፣ ሲሆን ለዚህ አላማ መሳካት በኖርዌይ ሀገር ከሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።

የዘወትር አገልግሎት

ሰንበት ት/ቤቱ ዘወትር እሁድ ከ 10:00 – 12:00 ሰዓት የሚከተሉትን የሰንበት መርሐግብራት ያከናውናል።

  • የማህበር ጸሎት
  • ስብከተ ወንጌል
  • ያሬዳዊ መዝሙርና
  • የተለያዩ ስነ ጽሑፎች

በዓላት

ሰንበት ት/ቤቱ በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት መሠረት በየዓመቱ  የዘመን መለወጫ፤ መስቀል፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ስቅለትና ትንሣኤ በዓላት፣ እንዲሁም ደብረዘይት እና ፍልሰታ ማርያምን ያከብራል።  እነዚህን በዓላት ምክንያት በማድረግ በዓመት ቢያንስ አምስት ጊዜ ቅዳሴ ሲኖር በአካባቢዉ ለተወለዱ ህጻናት ጥምቀትና ሌሎች ሚስጢራተ ቤተክርስቲያንን ያከናውናል።