መስቀል – ፳፻፲፰ ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ አደረሰን ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብር የምትሰጠው?
” መስቀል ኃይላችን ነው ፣ ኃይላችን መስቀል ነው ፣ የሚያፀናን መስቀል ነው ፣ መስቀል ቤዛችን ነው ፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው ፣ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነው እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።” /የዘወትር ጸሎት/
“በብሉይ ኪዳን መስቀል የእርግማን ምልክት ና የወንጀለኞች መቀጫ ነበር::” (ዘዳ 21:23) ክርስቶስ በደሙ ስለቀደሰው ግን ቅዱስ መስቀል ተብሏል።
“በመስቀል ድህነትን አግኝተናል። ” (1ኛ. ጴጥ 2: 24-25) ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን በቀራኒዮ የተሰቀለበት ቤዛችን ነው። መስቀል የነጻነታችን ግርማ: የድህነታችን መገኛ: ጠላትን ድል የምንነሣበት መሳሪያችን ነው። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው በጥንቱ ፋርስ (በዛሬዋ ኢራን) ከክርስቶስ ልደት በፊት
(339 – 33) ዓመት ነው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብርን የምትሰጠው?
  1. ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ ራሱን የሠዋበት እውነተኛ መንበር በመሆኑ ፤
  2. የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት: እኛ የዳንበት የነጻነት አርማችን በመሆኑ ፤
  3. የአምላካችን መለኮታዊ ፍቅር የተገለጠበት መሳሪያ በመሆኑ ፤
የመስቀል ዓይነቶች :-
  1. የመጾር መስቀል:- በቅዳሴ እና በማዕጠንት ጊዜ ሠራዒው ዲያቆን የሚይዘው ነው።
  2. የእጅ መስቀል:- ካህናት ምእመናንን የሚባርኩበት በእጅ የምትያዝ የመስቀል ዓይነት ናት።
  3. የአንገት መስቀል:- ምእመናን ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ከማዕተባቸው ጋር በአንገታቸው የሚያደርጉት ነው።
  4. እርፈ መስቀል:- በማንኪያ ቅርጽ ተሠርቶ በእጅታው ላይ የመስቀል ምልክት ያለበት ነው። ሠራዒው ዲያቆን በቅዳሴ ጊዜ የአምላካችንን ክቡር ደሙን ለምእመናን የሚያቀብልበት ነው። እንዲሁም ጌታችን በእለተ አርብ የተወጋበት ጦር ምሳሌ ነው።
መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ይሰራል ። መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ሊሰራ ይችላል። መስቀሉ የሚሰራባቸው ማዕድናት የራሳቸውን ባህርያት እንዳላቸው ሁሉ ምሳሌውን ለመግለጽ ብቁ ናቸው ብለው አባቶች ያስቀመጡትን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
  1. የእንጨት መስቀል:- ጌታችን የተሰቀለው በዕጽ በእንጨት ላይ መሆኑን ለማመልከት ነው።
    ለምን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት ተሰቀለ? አዳም ዕጽ/ እንጨትን በልቶ ሞትን በማምጣቱ ክርስቶስም በእንጨት ተሰቀሎ ህይወትን ሊሰጠን በእንጨት መስቀል ተሰቀለ።
  2. የብረት መስቀል:- ጌታችን በአምስቱ ቅንዋተ ለመቸንከሩ ምሳሌ ነው።
  3. የብር መስቀል:- ይሁዳ በሠላሳ ብር አሳልፎ ስለመስጠቱ። በተጨማሪም ከብር ቢሰራ ተስፋን: ዕድልን ያመለክታል። ይኸውም እርሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ ሊሆን በደሙ ዋጋ ከፍሏልና ከእርሱ ተስፋ እንድናደርግ ያመለክተናል።
  4. የወርቅ መስቀል፦ ከወርቅ ቢሰራ ወርቅ ንጹህ እንደሆነ ንጹሀ ባህርይ እድፈት የሌለው ጽኑ አንተ ነህ ብሎ ለመመስከር ነው።
  5. የመዳብ መስቀል:- መዳብ ቀለሙ ቀይ ይመስላል: ጌታችን ለእኛ ብሎ ያፈሰሰው ደም ምሳሌ ነው።
ብዙዎች የመስቀል ጠላት ሆነው መስቀልን ጣኦት ነው ይላሉ ጣኦት ማለት ግን የሠይጣን ስም የሚጠራበት ፣የሚመለክበት ነው።መስቀል ደግሞ የመድኃኒዓለም ስም የሚጠራበት ህማሙን የሚድኑበት አርማችን፣ ኃይላችን ነው እንጂ መስቀል አምላክ አይደለም። በመስቀል የተሠቀለው ግን አምላክ ነው። ምሳሌ:- ሰው አልጋ ላይ ሲተኛ አልጋ ላይ ተኛ ይባላል እንጂ እንጨቱ ላይ ተኛ አይባልም: ሰው የቤቱን በር ሲዘጋ እጨቴን ልዝጋ አይልም በሩን ልዝጋ ይላል እንጂ: አልጋ አልጋ ይባላል የተሰራው ከእንጨት ሊሆን ይችላል ነገር ግን እንጨት ተብሎ አይጠራም: በርም በር ይባላል እንጂ እንጨት ተብሎ አይጠራም። እንዲሁም ጌታ የተሰቀለበትን መስቀል መስቀል ይባላል ፤እንጂ እንጨት አይባልም።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵ 3÷18-19)
“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” ( ገላ 6:14)
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ” ተብሎ ተጽፎአልና። (1ኛ ቆሮ 1÷18-19)
ልዑል እግዚአብሔር ከመስቀሉ በረከት ያድለን ።
በትሮንድሃይም ከተማ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን የደመራ በዓል እንዲህ ከታች በፎቶ እንደሚታየው በአማረ በደመቀ ሁኔታ አክብረናል እግዚአብሔር ይመስገን ፣፣

መስቀል – ፳፻፲፰ ዓ.ም. — ፎቶ

አዲስ አመት – ፳፻፲፰ ዓ.ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
” አሮጌውን ሰው አስወግዱ አዲሱን ሰው ልበሱ ” ኤፌ 4-22
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን አላችሁ? እንኳን ለ2018 ዓ/ም ዘመነ ማርቆስ በሰላም በጤና አደረሳችሁ አደረሰን ።
አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ተተካ ስንል ዓመተ ምሕረቱ አራቱ ወንጌላውያን በየ አራት አመቱ እየተፈራረቁ ዘመናትን ሲመግቡ ይኖራሉ ፣ ስለዚህም ማቴዎስ ሲወጣ ማርቆስ ተተክቶ ዓመቱን ሙሉ ያሳልፋል ማለት ነው ። በዘመነ ማቴዎስ የነበረን ሕይወት ሁሉ ተቀይሮ የቆሸሸው ጸድቶ ያደፈው ታጥቦ የከፋው ቀንቶ የወደቀው ተነስቶ አዲስ ሕይወት እንዲኖረን ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱን ሰው ልበሱ እያለ ይነግረናል ።
ጌታችን መድኃኒታችን እኢየሱስ ክርስቶስም በዮሐንስ ወንጌል 6 ÷ 53 ላይ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ።”
  • ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ ።
  • ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ።
  • ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ ።
በማለት የአዳም ልጅ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶ ሥጋውን ደሙን ተቀብሎ አዲስ ሕይወት እንዲኖረው ያስፈልጋል። አብዛኛው ማኅበረሰባችን የወንጌሉን ቃል በተግባር እየተረጎመው አይደለውም እና ከዛሬ ነገ በማለት በቀጠሮ ጊዜውን ያሳልፋል ፣ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ሳይቀበል መልአከ ሞት በድንገት እንደ ሌባ ደርሶ ሳያስበው ነጥቆ ይወስደዋል ስለዚህ እንደ ቃሉ ልንኖር ያስፈልጋል።
በቀጠሮ ዘመናችን ሳያልቅ ፣ የጭንቅ ቀን ሳይመጣ ፣ ልንመለስ ፣ ልንስተካከል ፣ ልንታረቅ ፣ ልንታጠብ ፣ ልንቀደስ ፣ አዲስ ሕይወት ልንይዝ ይገባል ።
እግዚአብሔር ዘመኑን የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የቅድስና ፣ የለውጥ ፣ የንስሐ ፣ የደስታ ፣ የምስጋና ፣ ዘመን ያድርግልን አሜን ።
መልካም አዲስ አመት !

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ  ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ  አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል”
(ቅዱስ ያሬድ)

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በዛሬው ዕለት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ የቅድስት ኢየሉጣ አመታዊ ክብረ በዓል ነው።
በዚህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸው  ታሪክ ይናገራል።

የ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መልእክት

“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት” ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2ጢሞ 3÷1

+ + +

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለ2012 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ በሰላም በጤና አሸጋገረን አሸጋገራችሁ ።

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ሲቆጠር 7512 ዓ/ዓ ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ከወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ከተወለደ ደግሞ 2012 ዓ/ም ይሆናል ።

ማይክሮ – ሰከንዶች – ሰከንዶችን – ሰከንዶች ሰዓታትን – ሰዓታት – ቀናትን – ቀናት-ሳምንታትን – ሳምንታት – ወራትን- ወራት- ዓመታትን እየወለዱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር 64÷12 ላይ ” ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ,, ዓመታትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ (አንድም) የምሕረት አመታትን በቸርነትህ ለሰዎች ታድላለህ ብሎ እንደተናገረ እየተፈራረቁ ዘመናት በዘመናት እየተተኩ ዛሬ ካለንባት ጊዜና ዘመን ደርሰናል ።

ነገር ግን አባቶቻችን ዘመንን የሚቆጥሩት በሕይወት የኖሩበትን ዘመን ነበር እኛ ደግሞ ዛሬ ዘመን በሕይወት የምንኖርበት ሳይሆን በሥጋ የምንኖርበት ብቻ ሁኗል የሰዎች የክፋትም ሆነ የደግነት፣ የመልካም ሥራም ሆነ የክፉ ሥራ ውጤት በዘመን ይገለጣል ለዚህ ነው ሐዋርያው በመጨረሻው ዘመን ያለው እንደ እድል ሆኖ የኛ ዘመን ከመልካም ይልቅ ክፋት የበዛበት ከእውነት ይልቅ ውሸት የሚታመንበት ከፍቅር ይልቅ ጸብ የሚወደድበት ከሰላም ይልቅ ሁከት የሚፈለግበት ከምሕረት ይልቅ መዓት የሚሰማበት ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአት የነገሠበት ከመረዳዳት ይልቅ መገፋፋት የሚቀናበት ከመተሳሰብ ይልቅ መረሳሳት የተለመደበት ከማመስገን ይልቅ መካሰስ የበዛበት ከትእግሥት ይልቅ ቁጣ የፈጠነበት ከትሕትና ይልቅ ትእቢት ከሥራ ይልቅ ስርቆት የሞላበት የመከራው ዘመን ነው ።

ዓለም እንደፈለገ የሚጋልብበት የውድድር ሜዳ አጥር ቅጥሩ የፈረሰበት ዘመን እየሆነ መጥቷል እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ለተፈጠርንለት አላማ ሳይሆን በራሳችን አዙሪት እየተሽከረከርን መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል ጥንቱን ሰው የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነበር እሱም እንደ መላእክት ያለዕረፍታና ያለመታከት ያለድካም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ዓለም ግን መሥመር እየሳተ አቅጣጫ እየቀየረ መንገድ እየለቀቀ ነው ።

ይህንን ነበር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “የሚአስጨንቅ ዘመን እንዲመጣይህንን እወቅ ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ” ብሎ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን በዝርዝ የነገረው ።  ቅዱስ ጳውሎስ ወረድ ብሎ ከቁጥር 14 ላይ እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ቃል መሠረት በማድረግ እንደ ደቀ መዝሙሩ እንደ ጢሞቴዎስ ታዛዦች በመሆን አዲሱና የሚመጣው ዓመት እኛ ተለውጠን ሌሎችን የምንለውጥበት እኛ ከብረን የምናከብርበት ሰርተን ዋጋ የምናገኝበት ያለፈውን ድክመታችንን የምናስተካክልበት ባለፈው ያባከነውን ጊዜ ሐዋርያው ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ እንዳለ በቁጭት የምናስብበት ያስቀየምነውን ይቅርታ የምንጠይቅበት የቀማነውን የምንመልስበት ያጣነውን ሕይወታችንን ፈልገን የምናገኝበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የምንመለስበት ንስሐ ገብተን ባጠፋነው ክሰን የምንችል ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት የማንችል ሁሉን ወደሚችል አምላክ እንዲያስችለንና ለሥጋው ለደሙ እንዲያበቃን በጽኑ እምነት በቁርጥ ኅሊና በጠነከረ ልብ በበረታ ጉልበት ለጾም ለጸሎት የምንዘጋጅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ እንዲአደርግልንም ተግቸ እጸልያለሁ ።

እናንተም እንደ ጢሞቴዎስ በተማራችሁበትና በተረዳችሁበት ነገር ጸንታችሁ እንድትኖሩ አደራ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።

መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመወርቅ

ሊቀ-ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ

በወንድም ይበልጣል ጋሹ

St.George የቅዱስ ጊዮርጊስ አባት አንስጣስዮስ ከሮም ወደ ፍልስጤም በፈቃደ እግዚአብሔር ሄደ።በዚያም ከክቡራን መኳንንት፣ ከታላላቆች መሳፍንት መካከል አንዱ ነበር። ከፍልስጤም ዕጻ ከምትሆን ድያስ ከተባለች አገር ቴዎብስታ (አቅሌስያ) የምትባል ደግ ሚስት አገባ። የቴዎብስታ የስሟ ትርጓሜ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው። አቅሌስያም እንደ ስሟ የተቀደሰች፣ የተመሰገነች፣ የተባረከች፣ የተመረጠች በብርሃኑ ዓለምን ሁሉ ያበራውን የሰማዕታትን ኮከብ ይሸከም ዘንድ እግዚአብሔር ማህጸኗን የባረከላት ሴት ነበረች።እነዚህ ሁለት ደጋግ የእግዚአብሔር ሰዎችም ዘሮንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ቴዎብስታ (አቅሌሲያ) በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ተጋብተው በህይወታቸው እግዚአብሔርን የሚያስደስት ተግባር ይፈጽሙ ነበር። ጥር 20 ቀን 277 ዓ.ም በሀገረ ፍልስጤም ልዩ ስሟ ልዳ በተባለ ስፍራ ደም ግባቱ ያማረ፣ መልከ መልካም ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ወለዱ። በተጨማሪም ማርታና እስያ የሚባሉ ሁለት ሴቶች ልጆችን አፈሩ።

Read more

ያግኙን

እናመሰግናለን

ለሰጡን አስተያየት እናመሰግናለን። አስተያየትዎት ምላሽ የሚያሻ ከሆነ በተቻለን መጠን ምላሽ ለመስጠት እንሞክራለን።

ቅዱስ እግዚአብሔር አገልግሎታችንን ይባርክ!!!

ስለ እኛ

ታሪክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  የትሮንዳሔም ምሥራቀ ፀሐይ ቅጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መነሻው እ.ኤ.አ በ1995 መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ ኖርዌይ ትሮንዳሔም በመጡ የቤተክርስቲያን ፍቅር ባላቸው ተማሪዎች አማካኝነት የተመሰረተ ሰንበት ትምህርት ቤት ነው። ሰንበት ት/ቤቱ በተለያዩ መዋቅሮች ተደራጅቶ አገልግሎቱን አጠናክሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትሮንዳሔም ለመጡ የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎት ዘወትር እሁድ የፀሎት መርሐግብር እንዲሁም በአበይት በዓላት ጊዜ የቅዳሴ አገልግሎት  እየሰጠ የቆየ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2010 በኖርዌይ ሀገር በሐይማኖት ተቋምነት ተመዝግቦ ህጋዊ ሰውነት አግኝቷል። በእ.ኤ.አ በ2013 ደግሞ ወደ አጥቢያነት በማደግ ቃለዓዋዲው መሰረት አድርጎ ሰበካ ጉባዔ በማደራጀት አገልግሎቱን አስፍቶ ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት አጥቢያችን ከሰበካ ጉባዔ ጀምሮ በተለያዩ መዋቅሮች ተደራጅቶ አገልግሎቱን አጠናክሮ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ትሮንዳሔም ለመጡ የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎቱን  እየሰጠ ሲሆን ከ 200 የማያንሱ አባላት አሉት።

ከአጥቢያችን ዋነኛ አላማዎች ውስጥ አንዱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም የቤተክርስቲያኒቱን እምነትና ስርዓት ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በቤተክርስቲያኒቷ ዕምነትና ስርዓት መሰረት ትምህርተ ወንጌልን ማስተማር፣ ሲሆን ለዚህ አላማ መሳካት በኖርዌይ ሀገር ከሚገኙ የኢ/ኦ/ተ/ ቤ/ክርስቲያናትና ሰንበት ት/ቤቶች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል።

የዘወትር አገልግሎት

ቅዳሴ፦ ዘወትር እሑድ እንዲሁም በበዓላት እና በንግሥ ቀን

ምህላ፦ በዐቢይ ጾም፣  እና እንደ አስፈላጊነቱ ሲታወጅ