ኒቆዲሞስ
ኒቆዲሞስ የዓቢይ ጾም ሰባተኛ ሳምንት ሲሆን ስያሜው ኒቆዲሞስ በተባለ የአይሁድ አለቃ በነበረ ሰው ስም ተሰይሟል፡፡
“ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤” ዮሐ 3-1
በዕለቱ በሚነበበው በዚህ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኒቆዲሞስ ለተባለ የአይሁድ አለቃ ያስተማረው ትምህርት እንዲሁም የኒቆዲሞስ ጥያቄና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው ትምህርት ይገልጽልናል።
“ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት ነው” ዮሐ 7-51
ቀን ቀን ከአይሁዳውያን ጋር ሲያስተምር ይውላል ማታ ማታ ዕውቀቱን ለማስፋት ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ሲማር ያድራል አለቅነትን ከመምህርነት ዕውቀትን ከትህትና አስተባብሮ የያዘ ሰው ነበር ፣
“የምስጢረ ጥምቀት መገለጥም ምክንያት የሆነ እና ምስጢረ ጥምቀትን ከባለቤቱ ጠይቆ የተረዳ ሰው ነው ” ዮሐ 3 ÷ 1-21
አንዳንዴ ሳያውቁ አዋቂ ነን ሳይማሩ መምህር ነን እናስተምር ለሚሉ ደፋር መምህራን ኒቆዲሞስ ጥሩ ግንዛቤ ይሰጣል፣ የአይሁድ የፋሲካ በዓል እየቀረበ ሲመጣ ክርስቶስ ቀኑ እንደደረሰ ለሐዋርያቱ ተናግሮ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፡ በዚህ ሰዓት ኒቆዲሞስ ጊዜ አላጠፋም ክብሩም አላስጨነቀውም መምህርነቱም አልገደበውም በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በፊቱ ቀርቦም «መምህር ሆይ ፤ በሌሊት ወደ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን ።» ብሎ እራሱ ዝቅ አድርጎ በትህትና ቀረበ።
ወቅቱ የአይሁድ የፋሲካ በዓል የቀረበበት ጻፎችና የካህናት አለቆች ጌታን ለመያዝ፣ እንደ ሙሴም ህግ ሊያስፈርዱበት የቋመጡበት ጊዜ ነበር፡፡ የሙሴ ፈጣሪ መሆኑን አላወቁም የካህናት አለቆች ተሰብስበው ክርስቶስን ለመያዝ በሚመካከሩበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍ ሕግ ጠቅሶ ሊቃውንተ ኦሪትን አፍ ያስያዛቸው እሱ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ሳይስማሙ ወደየቤታቸው እንዲበታተኑ ምክንያት የሆነ ታላቅ ሰው ነው፡፡
ጌታችን በቀራንዮ አደባባይ ራሱን ለዓለሙ ቤዛ አድርጎ ሲሰጥ እስከ ሞት ድረስ ከአንተ አንለይም ያሉት ደቀ መዛሙርቱ ሲበታተኑ ፣ከዮሐንስ በቀር፣ በዘጠኝ ሰዐት ቀራንዮ የነበረ ኒቆዲሞስ ነበር፡፡ ከዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ስጋ ከአለቆች ለምኖ፣ የገነዘ፣የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከርቤና የእሬት ቅልቅል ያርከፈከፈለት ወደ ሐዲስ መቃብር ያወረደውም ኒቆዲሞስ ነበር፡፡
ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?
ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ ደረጃ የዕውቀት ደረጃ የስልጣን ደረጃ ራሳችንን ጠምደን የመማር አቅም አጥተናል፡፡ ቁጭ ብሎ መማር ደረጃችንን የማይመጥን የሚመስለንስ ስንቶች እንሆን?
አንድ ወቅት አባ መቃርስ ከህጻናት እንቆቅልሽ ለመማር ቁጭ እንዳሉ፣ በእንቆቅልሹም ልባቸው ተነክቶ እያነቡ ወደ በዐታቸው መመለሳቸውን በመጽሐፍ ተጽፎ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ እኛስ ያወቅነውን እያሳወቅን ያላወቅነውን ብንማር ምን ችግር አለው? ይኸ አልሳካ ያለን የመማር አቅም ያጣን ስንቶች እንሆን? ትሑት የሚያሰኘው ሳያውቁ አላውቅም ማለት ሳይሆን እያወቁ አላውቅም ማለት ነው፡፡ ሳይማሩ ተምሬያለሁ ማለት ሳይሆን ተምረውም ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ለመማር ራስን ዝቅ ማድረግ ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ፈሪሳዊ ፣ የአይሁድ አለቃ ፣ መምህር ፣ ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ስር ቁጭ አለ፡፡ ከመምህራን ስር ቁጭ ብሎ መማር መታደል ነው
እኛም በምሕረቱ አደባባይ ተገኝተን በጌታ ፊት ቁጭ ብለን ቃሉን ለመስማት ያብቃን አሜን ።
ይቆየን፤