መጻጉዕ
መጻጉዕ
የዐቢይ ጾም አራተኛው እሑድ መጻጉዕ ይባላል፡፡ መጻጉዕ የተባለበት ምክንያት በዚሁ ሰንበት ከዋዜማው ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ የሚዘመረው ዝማሬ የሚነበበው ምንባብ ፣ ድውያንን መፈወሱን ዕውራንን ማብራቱን የሚገልጥ በመሆኑ ነው፡፡
«ሠላሳ ስምንት ዓመት የታመመውን መጻጉዕን ኢየሱስ አዳነው» እንዲሁም ልጁ የታመመበት የመቶ አለቃው “ጌታዬ በቃልህ እዘዝ ልጄ ይድናል፡፡ በቤቴ ጣርያ ሥር አንተ ልትገባ አይገባህም” አለው። “ጌታ በሚያልፍበት መንገድ አንድ ዕውር ፈውሰኝ” ብሎ ጮኸ የሚመሩት ሰዎች ዝም በል አሉት፡፡ ዕውሩ ግን እምቢ ብሎ “የዳዊት ልጅ ጌታ ይቅር በለኝ ዕርዳኝ” እያለ ጩኸቱን ቀጠለ፡፡ “በሰንበት ኢየሱስ መጻጉዕን ተነሥ አልጋህን ተሸከም ባለው ጊዜ ቀኑ ሰንበት ነበረ፡፡ መጻጉዕም አልጋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንበት ፈውሷልና “በሰንበት ድውያንን ፈወሰ የዕውራንንም ዓይኖች አበራ” እያለ ሠላሳ ዓመት በአልጋ ቁራኛ በደዌ ዳኛ ተይዞ ሲማቅቅ የኖረውን መጻጉዕንና ሌሎቹን በልዩ ልዩ ደዌ የተያዙትን ሕሙማን መፈወሱን በጠቅላላው ለምፅ ማንጻቱን፣ ዕውር ማብራቱን፣ አንካሶችን ማርታቱን፣ ልምሾዎችን ማዳኑን፣ አጋንንትን ማውጣቱን፣ ይናገራል
የሕሙማን መታሰቢያ ሳምንት ማለት ነው።
የስያሜው ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦
➾ 1ኛ.ለአምስተ ሺህ አምስት መቶ ዘመን በዚህ ዓለም በሥጋ በአካለ ነፍስም በመንጸፈ ደይን ወድቀው በእግረ አጋንንት እየተረገጡ ይኖሩ የነበሩት ሕሙማነ ሥጋን እና ሕሙማነ ነፍስን የምናስብበት ሰሙን ማለት ነው።
➾ 2ኛ.መድኅን ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የአልጋ ቁራኛ የደዌ ዳኛ የሆኑትን በማዳን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ ያስተማረበትን ዘመን የምናስብበት ነው።
“ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።”ማቴ. 4 ፥ 23 እንዲል።
➾ 3ኛ.ሥግው መለኮት ሕማማችንን ሕማም አድርጎ በዕለተ ዓርብ በአካለ ሥጋ ወደ መቃብር ወርዶ ሙስና መቃብርን፤በአካለ ነፍስ ወደ ሢኦል ወርዶ ዕዳ በደልን ያጠፋበትን የምናስብበት ነው።በዚህ ዓለም ያለው ደዌ ሥጋ የዚህ ዓለም ምሳሌ ነው።ፈውሰ ሥጋ የትንሣኤ ሙታን ምሳሌ ነው።
“በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል።”ኢሳ 53 ፥ 4 እንዲል።
➾ 4ኛ.እስከ ዕለተ ምጽአት እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ ሕሙማንን ብንችል እየፈወስን ካልቻልን እየጠየቅን የወንጌልን ሕግ እንፈጽም ዘንድ መታዘዛችንን የምናስብበት ሳምንት ነው።”ታምሜ ጠይቃችሁኛልና።”ማቴ. 25 ፥ 36 እንዲል።
5ኛ.ኃጢአትን በንስሐ እያስወገድን ከደዌ ነፍስ እየተላቀቅን እንኖር ዘንድ የምናስብበት ሰሙን ነው።
➢ በኃጢያት መያዝ የደዌ ፦ በንስሐ መታጠብ የፈውስ ምሳሌ ነውና።..
“ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ።”ማቴ. 8 ፥ 4 እንዲል።
ይኸ ሁሉ የክርስቶስ ሥራው፣ መግቦቱ ፣ ቸርነቱ የተቋረጠ አይደለምና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ስናስበው ስንፈጽመው እንኖራለን።
“አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ።”ዮሐ. 5 ፥ 17
ስለዚህም ይህ ሰንበት የሕሙማን ፈውስ መታሰቢያ ዕለት ነው ማለት ይቻላል፡፡
እግዚአብሔር ሁላችንንም ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ ይፈውሰን አሜን ።
ይቆየን፤