በዓለ መስቀል
በጎልጎታ ዘደፈኑ አይሁድ ዮም ተረክበ ዕፀ መስቀል
አይሁድ በምቀኝነት በጎልጎታ የቀበሩት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕፀ ምስቀል እነሆ ዛሬ ተገኘ
(ቅዱስ ያሬድ )
በዓለ መስቀል በክርስትና ኃይማኖት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮአደባባይ የተሰቀለበት መስቀል በአይሁድ ክፋትና ምቀኝነት ለ300 ዓመታት ከተቀበረበት ሥፍራ መገኘቱን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን በድምቀት ታከብራለች።
“መስከረም በአበባው ሠርግ በጭብጨባው ይታወቃል” እንዲሉ አበው። የመስከረም ወር ዓውደ ዓመት፣ የዘመን መለወጫ የአበባ የጽጌ የብርሃን ወቅት በመሆኑ በዚህ ወር የመስቀል በዓል መከበሩ እጅግ ድምቀት እንዲያገኝ አድርጎታል ። እናም ኢትዮጵያውያን በርዕሰ በዓልነት ታላቅ ማዕዘን ላይ ያስቀመጡት ወርኃ መስከረም፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን አቅፏል። ከነዚህም ውስጥ ከእንቁጣጣሽ በዓል ቀጥሎ በሠፊው የሚታወቀው በዓለ መስቀል ነው።
መስቀል ምንም እንኳ በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ዘንድ፣ የራሱ የሆነ ትርጉም ያለው ቢሆንም ከኃይማኖታዊ ክንዋኔው ባሻገር፣ ባህላዊ በሆነ ገፅታ የሚያከብሩት የኅብረተሰብ ክፍሎችም ቀላል የሚባሉ አይደሉም። ለምሣሌ በደቡብ ኢትዮጵያ የሚደረጉት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ስለመስቀል በዓል አከባበር ፣ በጽሑፍና በቃል የተላለፉ መረጃዎች እንደሚነግሩን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል በተአምራዊነቱና በክርስቲያኖች ዘንድ ምልክት የታየበት ሕሙማን የሚድኑበት ከፍተኛ ክብር የተሰጠው በመሆኑ፣ አይሁድ በቅንአት ተነሣሥተው ለ300 ዓመታት ያህል በቆሻሻ መጣያ ቦታ ቀብረውት ቆይቶ ነበር።
ይሁንና በ326 ዓ/ም የቄሳር / ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራኮስ በተባለ አንድ ታሪክ አዋቂና ፈላስፋ ሽማግሌ ጠቋሚነት፣ መስቀሉ የተጣለበትን አካባቢ ተረዳች። ከዚያም
በኋላ ደመራ ደምራ በእሳት አቀጣጥላ ዕጣን ባጨሰች ጊዜ፣ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ከወጣ በኋላ ተመልሶ ያረፈበትን ሥፍራ አስቆፍራ መስቀሉን አውጥታዋለች። ንግሥተ ዕሌኒ በጭሱ ምልክትነት፣ መስቀሉን ለማውጣት ለሰባት ወራት ያህል ማስቆፈሯን ማለትም መስከረም 17 ቀን አስጀምራ በመጋቢት 10 ቀን እንዳስወጣችው ይነግረናል። ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ተከትሎ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል ።
በነገራችን ላይ ስለመስቀል በዓል ስናነሳ፣ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ቢያከብሩትም በልዩ ክብር እና ደማቅ ሁኔታ የሚከበረው ግን በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ መሆኑን መናገር ይቻላል። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ መሞትና በመስቀሉ የማይረሳ ውለታ የሰው ልጅ መዳኑን ቢያምኑም እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶና ሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ትውፊትን ስለማይቀበሉ፣ የመስቀልን በዓል ኃይማኖታዊ በዓል አድርገው አይመለከቱትም።ይሁን እንጅ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው መስቀሉን አስቆፍሮ ለማግኘት ሰባት ወራት ያህል ፈጅቶ “መስቀሉ የተገኘው መጋቢት 10 ቀን ነው፣ ይህ ወር ግን የየዓቢይ ጾም ወቅት በመሆኑ በዓሉ በመስከረም 17 ቀን እንዲሆን ሊቃውንቱ ተስማምተው አቆይተውናል” ።
በኢትዮጵያችን ሌላው የጌታችንን መስቀል ልዩ ሥፍራ እና ክብር የሚሰጠው ጉዳይ ደግሞ በ15 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ የተሰቀለበት ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መቀመጡ ነው። ስለ መስቀሉ መምጣት ታሪክ እንደሚያስረዳን፣ ንጉሡ አፄ ዳዊት ግማደ መስቀሉን አስመጥተው በኢትዮጵያ አድባራት ሁሉ በመዞር፣ ሊያሳርፉበት ያልሞከሩበት ቦታ አልነበረም፤ ነገር ግን መሬቱ እየተንቀጠቀጠ አስቸግሯቸው ሲጨነቁ ፡ በመጨረሻ ግን “አንብር መስቀልዬ በዲበ መስቀል። (መስቀሌን በመስቀለኛ ሥፍራ አስቀምጠው)” የሚል መለኮታዊ ራዕይ ስለደረሳቸው፣ አሁን ግሼን አምባ በሚባለው ሥፍራ ላይ መስከረም 21 ቀን 1446 ዓ/ም እንዳሳረፉት የታሪክ መዛግብት
ያስረዳሉ። የግሸን ደብረ ከርቤ (አምባ ማርያም) ቦታ የተመረጠበት ምክንያት መስቀለኛ መልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ያለው በመሆኑ ከራዕያቸው ጋራ ስለስማማላቸውና ስለተፈቀደላቸው ነው።
የተወደዳችሁ ክርስቲያኖች ዛሬም እኛ ከአባቶቻችን በቅብብሎሽ የተረከብነውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት አስቀጥለን በዓለ መስቀልን አክብረንና አስከብረን አባቶቻችን የወረሱትን የመስቀሉን ጸጋና በረከት አምላካችን እግዚአብሔር ያድለን አሜን ።
“እግዚአብሔር ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ያስብልን፤ ህዝቦቹንም ይጠብቀን፡፡”
ይቆየን ።