ገብር ኄር (መልካም አገልጋይ)

ከደብረ ዘይት ቀጥሎ ያለው ስድስተኛው የዓቢይ ጾም ሳምንት ደግሞ ገብር ኄር ይባላል። መልካም አገልጋይ ቸር ርኅሩኅ ማለት ነው። ይህ ዕለት መልካም አገልጋዮች በትጋታቸው የሚወደሱበት ሰነፍ አገልጋዮች ደግሞ በስንፍናቸው የሚወቀሱበት ዕለት ነው።

ስያሜውን ያገኘው፦
አንደኛ፦በብሉይ ዘመናት የነበሩ መልካም አገልጋዮቹ ነቢያትና እና ካህናት በአጠቃላይ ምእመናነ ብሉይ የአገልግሎት እና የመልካም አገልጋይነት ዋጋቸውን አግኝተው እንደምን እንደ ተመሰገኑ እነሱንና መልካም ስራቸውን የምናስብበት ዕለት ነው።

ሁለተኛው፦የትሩፋተ ሥጋ የትሩፋተ ነፍስ ጀማሪው መድኅን ክርስቶስ በተገዥ ሰውነት ተገልጦ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተመላልሶ በሕጻንነቱ ለእናቱ ለዘመዶቹ ኋላም ለሁሉም ሰው አርአያ በመሆን በሰውነቱ ማገልገሉን የምናስብበት ነው።”

የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” ማቴ.20 ፥ 28 ። አርአያነት ማለት!! የትህትና ሥራውን በገለጸበት በምሴተ ሐሙስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡም ከዚህ የተነሣ ነውና።
ስለዚህ ይኸ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የቸርነት ተልእኮ የምናስብበት ሳምንት ነው።

ሦስተኛ፦ቅዱሳን ሐዋርያት እና ተከታዮቻቸው በጸጋ እግዚአብሔር ከብረው በሠሩት መልካም የወንጌል አገልግሎት የተልእኮ ሥራቸው “ቸር አገልጋዮች ተብለው ታማኝነታቸው ፣ ትሩፋታቸው፣ ክብራቸው የሚነገርበት ሳምንት ነው።

አራተኛ፦አጠቃላይ ምእመናን በተሰጣቸው የተፈጥሮ ጸጋ እና የእምነት ጸጋ፣የትሩፋተ ሥጋ፣የትሩፋተ ነፍስ ጸጋ፦ሥራ ሠርተው የጸጋ መክሊታቸውን አብዝተው አትርፈው ቢገኙ የሚመሰገኑበት ሳምንት ነው።

አምስተኛ፦በተፈጥሮ በተሰጣቸው ጸጋ እና በሃይማኖት በሹመት በተሰጣቸው ጸጋ ምግባር ትሩፋት መሥራት ሲገባቸው በስንፍና፣በፍርሀት ተሸብበው የኖሩ ሰነፍ ሰዎችም የሚወቀሱበት ሳምንት እና ክፍለ ጊዜ ነው።

ስድስተኛ፦አጠቃላይ ከእግዚአብሔር በተፈጥሮ የተሰጡን ነገሮች በሙሉ የሚያስጠይቁ ሀብቶች እንደሆኑ የምንማርበት ጊዜ በመሆኑ ሁሉም የሥነ ፍጥረት እና የሃይማኖት ጸጋዎች ሁሉም ሥጦታዎቻችንን
በትክክል ተቀብለን በሕይወታችን ዘመን ሙሉ ጠብቀን ለሚመጣው ትውልድ ልናስረክባቸው ግድ ነው። ይህንን ባናደርግ ግን መክሊት ቀባሪዎች ተብለን እንደምንወቀስ የምንማርበት ነው።

ስለዚህ መክሊቱን የሰጠን አምላክ ተመልሶ መጥቶ ሲጠይቀን ምላሽ እንዳናጣ መክሊትችንን አውጥተን እንደተሰጠን ጸጋ መጠን አትራፊዎች ልንሆን ይገባል ። “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።”ማቴ.25 ፥ 15

በመጨረሻም የጸጋው ባለቤት ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በመጣ እንደየ መክሊታችን አትርፈን እንድንገኝ ይርዳን አሜን

ይቆየን ፣