የ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መልእክት
“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት” ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2ጢሞ 3÷1
+ + +
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለ2012 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ በሰላም በጤና አሸጋገረን አሸጋገራችሁ ።
ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ሲቆጠር 7512 ዓ/ዓ ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ከወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ከተወለደ ደግሞ 2012 ዓ/ም ይሆናል ።
ማይክሮ – ሰከንዶች – ሰከንዶችን – ሰከንዶች ሰዓታትን – ሰዓታት – ቀናትን – ቀናት-ሳምንታትን – ሳምንታት – ወራትን- ወራት- ዓመታትን እየወለዱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር 64÷12 ላይ ” ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ,, ዓመታትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ (አንድም) የምሕረት አመታትን በቸርነትህ ለሰዎች ታድላለህ ብሎ እንደተናገረ እየተፈራረቁ ዘመናት በዘመናት እየተተኩ ዛሬ ካለንባት ጊዜና ዘመን ደርሰናል ።
ነገር ግን አባቶቻችን ዘመንን የሚቆጥሩት በሕይወት የኖሩበትን ዘመን ነበር እኛ ደግሞ ዛሬ ዘመን በሕይወት የምንኖርበት ሳይሆን በሥጋ የምንኖርበት ብቻ ሁኗል የሰዎች የክፋትም ሆነ የደግነት፣ የመልካም ሥራም ሆነ የክፉ ሥራ ውጤት በዘመን ይገለጣል ለዚህ ነው ሐዋርያው በመጨረሻው ዘመን ያለው እንደ እድል ሆኖ የኛ ዘመን ከመልካም ይልቅ ክፋት የበዛበት ከእውነት ይልቅ ውሸት የሚታመንበት ከፍቅር ይልቅ ጸብ የሚወደድበት ከሰላም ይልቅ ሁከት የሚፈለግበት ከምሕረት ይልቅ መዓት የሚሰማበት ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአት የነገሠበት ከመረዳዳት ይልቅ መገፋፋት የሚቀናበት ከመተሳሰብ ይልቅ መረሳሳት የተለመደበት ከማመስገን ይልቅ መካሰስ የበዛበት ከትእግሥት ይልቅ ቁጣ የፈጠነበት ከትሕትና ይልቅ ትእቢት ከሥራ ይልቅ ስርቆት የሞላበት የመከራው ዘመን ነው ።
ዓለም እንደፈለገ የሚጋልብበት የውድድር ሜዳ አጥር ቅጥሩ የፈረሰበት ዘመን እየሆነ መጥቷል እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ለተፈጠርንለት አላማ ሳይሆን በራሳችን አዙሪት እየተሽከረከርን መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል ጥንቱን ሰው የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነበር እሱም እንደ መላእክት ያለዕረፍታና ያለመታከት ያለድካም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ዓለም ግን መሥመር እየሳተ አቅጣጫ እየቀየረ መንገድ እየለቀቀ ነው ።
ይህንን ነበር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “የሚአስጨንቅ ዘመን እንዲመጣይህንን እወቅ ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ” ብሎ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን በዝርዝ የነገረው ። ቅዱስ ጳውሎስ ወረድ ብሎ ከቁጥር 14 ላይ እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ቃል መሠረት በማድረግ እንደ ደቀ መዝሙሩ እንደ ጢሞቴዎስ ታዛዦች በመሆን አዲሱና የሚመጣው ዓመት እኛ ተለውጠን ሌሎችን የምንለውጥበት እኛ ከብረን የምናከብርበት ሰርተን ዋጋ የምናገኝበት ያለፈውን ድክመታችንን የምናስተካክልበት ባለፈው ያባከነውን ጊዜ ሐዋርያው ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ እንዳለ በቁጭት የምናስብበት ያስቀየምነውን ይቅርታ የምንጠይቅበት የቀማነውን የምንመልስበት ያጣነውን ሕይወታችንን ፈልገን የምናገኝበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የምንመለስበት ንስሐ ገብተን ባጠፋነው ክሰን የምንችል ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት የማንችል ሁሉን ወደሚችል አምላክ እንዲያስችለንና ለሥጋው ለደሙ እንዲያበቃን በጽኑ እምነት በቁርጥ ኅሊና በጠነከረ ልብ በበረታ ጉልበት ለጾም ለጸሎት የምንዘጋጅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ እንዲአደርግልንም ተግቸ እጸልያለሁ ።
እናንተም እንደ ጢሞቴዎስ በተማራችሁበትና በተረዳችሁበት ነገር ጸንታችሁ እንድትኖሩ አደራ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።
መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመወርቅ