የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሚያዚያ ፳፭ እና ፳፮ ፥ ፳፻፲፯ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ የትሮንድሄም ምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፲፯ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የኢጣልያና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በተገኙበት እንዲሁም በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፭ እና እሁድ ሚያዚያ ፳፮ ፥፳፻፲፯ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
በዓሉ ቅዳሜ ከሰዓት በኃላ የተጀመረ ሲሆን በአባቶች ዋዜማ እንዲሁም በአጥቢያው አዋቂ እና ታዳጊ መዘምራን የተለያዩ ያሬዳዊ ዝማሬዎች የቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም የቅዳሜው ጉባዔ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ማሳረጊያና ቡራኬ ተፈጽሟል። ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በአባቶች ካህናት ፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማኅሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። የማኅሌቱ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ የነግህ ኪዳንና የቅዳሴ ስርዓት ተከናውኗል። በመቀጠልም የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ፡ንግሥ በዝማሬና በምስጋና በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ፤ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በብፁዕነታቸው የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉ ላይ የተገኙት ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።
በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ረድኤት እና በረከት አይለያችሁ።