የሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ሚያዚያ ፳ እና ፳፩ ፥ ፳፻፱ ዓ.ም በድምቀት ተከበረ
በቅዱስ ጊዮርጊስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በትሮንዳሔም የሚያዝያ ፳፫፥፳፻፱ ዓ.ም የሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተለያዩ አውሮፓ ሀገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተጋብዘው በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ ከመላው ኖርዌይ እንዲሁም ከትሮንዳሔምና አካባቢው በተገኙ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ምእመናንና ምእመናት ዓርብ ሚያዚያ ፳ እና ቅዳሜ ሚያዚያ ፳፩ ፥፳፻፱ ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።
በዓሉ ዓርብ እለት ምሽት ላይ በጸሎት ተጀምሮ በዲያቆን ብሩክ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ከቀረቡ በኋላ የወንጌል ትምህርት በመልአከ ምህረት አባ ዘሚካኤል ደሬሳ የተሰጠ ሲሆን በመቀጠልም የቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙሮችን እና ወረብ አቅርበዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ማኅሌት ላይ ከሚቀርቡ በዓሉን ከሚያወድሱ ወረቦች መሃከል አንዱን በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ እና በአጥቢያው መዘምራን በጋራ ቀርቧል። በመጨረሻም የዓርቡ ጉባዔ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ማሳረጊያ ትምህርትና በአባ ላዕከ ማርያም ቡራኬ ተፈጽሟል።
ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በመልአከ ስብሐት ተክሌ ሲራክ መሪነት በአባቶች፣ በዲያቆናት፣ በአጥቢያውና በቅዱስ ሚካኤል የሰ/ት/ቤት መዘምራንና በምእመናን ተሳትፎ የቅኔ ማኅሌቱ ስርዓት በደመቀ መልኩ ተከናውኗል። የማኅሌቱ ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ የነግህ ኪዳንና የቅዳሴ ስርዓት ተከናውኗል። በመቀጠልም በአጥቢያው መዘምራን ያሬዳዊ መዝሙር ከቀረበ በኋላ የዕለቱ ስብከተ ወንጌል በአባ ላዕከ ማርያም ተሰጥቷል። ትምህርቱንም ተከትሎ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል ስርዓተ-ንግሥ በዝማሬና በምስጋና በደመቀ ሁኔታ ተከናውኖ፤ በአጥቢያው መዘምራን የወረብ ዝማሬ ከቀረበ በኋላ በአባቶች የማሳረጊያ ጸሎት የክብረ በዓሉ መርሐ ግብር ፍጻሜ ሆኗል። በዓሉ ላይ የተገኙት ምእመናንም ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደየመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።
በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽዖ ላደረጋችሁ ምእመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን።
የበዓሉን የቀጥታ ስርጭት ምስሎች ለማየት የቤተክርስቲያናችንን የፌስቡክ ገጽ ይጎብኙ https://www.facebook.com/StGeorgeEOTCTrondheim/?hc_ref=SEARCH