ዘወረደ
“ወአልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ዘውእቱ ይነብር ውስተ ሰማይ።
ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።” ዮሐንስ 3 ÷ 13
ዘወረደ ፦ ማለት! ከክብር አንድም ከከፍታ አንድም ከንጽሕና አንድም ከጽድቅ የወረደ የተለየ ማለት ነው ፣ለጌታ ሲሆን ከሰማየ ሰማያት ከልዕልና ከመስቀል የወረደ ማለት ነው ።
እግዚአብሔር አዳምን በጥንተ ተፈጥሮ በልጅነት አክብሮ በቦታ አልቆ በገነት አኑሮት ነበር ነገር ግን ሕግ ባለማክበሩ ከክብሩ ተዋርዷል ፣
- ከንጽሕና ፦ አዳም በክብር በልጅነት ከብሮ ከሚኖርባት ገነት በኃጢአት ቆሽሾ መውጣቱን ፣ የሰው ልጅ ሰማያዊ መንግሥትን እንዳይወርስ በምድራዊ በኃላፊው በሚጠፋው በሚቀረው ቁሳዊ ዓለም ተጠምዶ በኃጢአት ተውጦ መኖሩን መናገር ነው ፣
- ከሰማይ፦ በዚህ ሁሉ ምክንያት የተዋረደ አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ የተዋረደውን የአዳምን ሥጋ ለብሶ ሰው መሆኑን አንድም ከልዕልና መውረዱን መናገር ነው ፣
ስለዚህ ወንጌላዊ ከወረደው በቀር የወጣ የለም ሲል ወደ ሲኦል የወረደ አዳም ወደ ገነት ተመልሶ ርስቱን መውረሱን በኃጢአት በበደል የወረደው ወደ ጽድቅ ፣ በውርደት የተሰደደው ወደክብር ፣ በሞት የተቀጣው ወደ ሕይወት ፣ በኀዘን የተዋጠው ወደ ደስታ ፣ በጭንቀት የተያዘው ወደ ሰላም ፣ በፍዳ በመከራ የወደቀው አዳም ወደ ነጻነት ተመለሰ ማለት ነው ።
አንድም ከአደባባይ ወደ መስቀል ፣ ከግዘፍ ወደ ርቀት ከትሕትና ወደ ልዕልና ከከመቃብር ወደ ትንሣኤ ከምድር ወደ ሰማይ የወጣ እርሱ ቅድመ ዓለም የነበረው በማዕከለ ዓለም የተገለጠው ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው መንግሥቱ ዘለዐለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየሰማያት የወረደው ዝቅ ያለው ከድሆች ጋር የተመላለሰው ከኃጢአተኞች ጋር የተቆጠረው ተዋርዶ የነበረውን ሰው ወደላይ ከፍ ያደረገው በትህትና ውስጥ እየተመላለሰ ነው ፣
የክብር ባለቤ ኢየሱስ ክስቶስ በኃጢአት የተዋረድነውን ሁሉ በመሐሪነቱ በንስሐ ይመልሰን ፣ አሜን ።
ይቆየን