አዲስ አመት – ፳፻፲፰ ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
” አሮጌውን ሰው አስወግዱ አዲሱን ሰው ልበሱ ” ኤፌ 4-22
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን አላችሁ? እንኳን ለ2018 ዓ/ም ዘመነ ማርቆስ በሰላም በጤና አደረሳችሁ አደረሰን ።
አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ተተካ ስንል ዓመተ ምሕረቱ አራቱ ወንጌላውያን በየ አራት አመቱ እየተፈራረቁ ዘመናትን ሲመግቡ ይኖራሉ ፣ ስለዚህም ማቴዎስ ሲወጣ ማርቆስ ተተክቶ ዓመቱን ሙሉ ያሳልፋል ማለት ነው ። በዘመነ ማቴዎስ የነበረን ሕይወት ሁሉ ተቀይሮ የቆሸሸው ጸድቶ ያደፈው ታጥቦ የከፋው ቀንቶ የወደቀው ተነስቶ አዲስ ሕይወት እንዲኖረን ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱን ሰው ልበሱ እያለ ይነግረናል ።
ጌታችን መድኃኒታችን እኢየሱስ ክርስቶስም በዮሐንስ ወንጌል 6 ÷ 53 ላይ ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም ።”
- ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ ።
- ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና ።
- ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ ።
በማለት የአዳም ልጅ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ አዲሱን ሰው ክርስቶስን ለብሶ ሥጋውን ደሙን ተቀብሎ አዲስ ሕይወት እንዲኖረው ያስፈልጋል። አብዛኛው ማኅበረሰባችን የወንጌሉን ቃል በተግባር እየተረጎመው አይደለውም እና ከዛሬ ነገ በማለት በቀጠሮ ጊዜውን ያሳልፋል ፣ ቅዱስ ስጋውን እና ክቡር ደሙን ሳይቀበል መልአከ ሞት በድንገት እንደ ሌባ ደርሶ ሳያስበው ነጥቆ ይወስደዋል ስለዚህ እንደ ቃሉ ልንኖር ያስፈልጋል።
በቀጠሮ ዘመናችን ሳያልቅ ፣ የጭንቅ ቀን ሳይመጣ ፣ ልንመለስ ፣ ልንስተካከል ፣ ልንታረቅ ፣ ልንታጠብ ፣ ልንቀደስ ፣ አዲስ ሕይወት ልንይዝ ይገባል ።
እግዚአብሔር ዘመኑን የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የቅድስና ፣ የለውጥ ፣ የንስሐ ፣ የደስታ ፣ የምስጋና ፣ ዘመን ያድርግልን አሜን ።
መልካም አዲስ አመት !