በትሮንዳሔም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ተቋቋመ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰንበት ት/ቤት ከ 17 ዓመታት ጉዞ በኋላ ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አደገ። ሰንበት ትምህርት ቤቱ እ.ኤ.አ በ 1995 «በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትሮንዳሔም ሰንበት ት/ቤት» ተብሎ የተመሰረተ ሲሆን አሁን ቅዱስ እግዚአብሔር ፈቅዶ ታቦተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ በሊቃነ ጳጳሳት ተባርኮ በመጋቢ ምስጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ አማካኝነት ወደ ኖርዌይ በመምጣቱ ወደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሊያድግ ችሏል። አጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን ማቋቋም አስመልክቶ የሁለት ቀን ጉባኤ ታህሳስ ፬ እና ፭ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም ተዘጋጅቶ ታቦተ ሕጉን በደማቅ ስነ ሥርዓት ከተቀበልን በኋላ በሥርዓተ ጸሎት በትሮንዳሔም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተቋቋመ።
በጉባኤውም ላይ አባቶች ካህናት፣ ወንድሞች ዲያቆናትና ምእመናን ከትሮንዳሔምና አካባቢው፣ ከስታቫንጋር፣ ከኦስሎ፣ ከበርገን፣ ከላቫንጋር እና ኦታ የተገኙ ሲሆን በዓሉ በማህሌት፣ በቅዳሴ፣ በስብከትና በዝማሬ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል:: ያሬዳዊ ዝማሬን የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን፣ የላቫንጋርና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የትሮንዳሔም ቅዱስ ሚካኤል መዘምራን ያቀረቡ ሲሆን የሰንበት ትምህርት ቤቱ የ17 ዓመታት ሂደት፣ የአሁን ገጽታና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነት በሚል ርዕስ መጠነኛ ገለጻ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም ታቦተ ሕጉን በሊቃነ ጳጳሳት አስባርከው ላመጡልን አባት እንዲሁም ለቤተክርስቲያናችን እገዛ ላደረጉልን ለአ/ፕሮፌሰር ስቫይን ኤገ ለማስታወሻ ይሆን ዘንድ ስጦታም ተበርክቶላቸዋል::
በአጠቃላይ በከተማችን እንዲሁም በተለያየ አካባቢ የምትኖሩ ምዕመናን እና ምዕመናት ጥሪያችንን አክብራችሁ እዚህ ድረስ በመምጣት፣ በዓሉ ላይ በመገኘት በስራና በተለያዩ መንገዶች ተሳትፎ በማድረግ ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት ላደረጋችሁልን ተሳትፎ ሁሉ በሊቀ ሰማዕቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ምስጋናችንን እናቀርባለን::