ቅድስት
“እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ።” ኤፌሶን 5 ÷ 27
የአብይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት የሚከተሉት ናቸው።
- የቅድስና ትርጉም፡ “ቅድስት” ማለት “የተቀደሰች፣ የተለየች” የከበረች ” ማለት ነው። ይህ ሳምንት በልዩ መንፈሳዊ ትኩረት እና በጸሎት፣ በጾም እና በንስሃ ስለሚታለፍ ቅድስት ተብሎ ይጠራል።
- በዚ ሳምንት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ የጀመረው የ40 ቀን እና ሌሊት ጾም የሚታሰብበት በመሆኑ ቅድስት ይባላል።
- ስያሜው ከኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ከቅዱስ ያሬድ የተገኘ አስተምህሮ ነው፡፡
ከዚህ ሰንበት ዋዜማ ጀምሮ ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስና ይዘመራል፡፡ የቤተክርስቲያን ትምህርት፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሰንበቱን ስለ ቅድስና ልጆቿን ታስተምርበታለች ፡፡ በቅዳሴ ጊዜ የሚሰበከው ምስባክ ፤ የሚነበቡ መልዕክታት ፤የሐዋርያት ሥራ እና ወንጌላቱም ስለ ቅድስት የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ፣ የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት “ቅድስት” ተብሎ የሚጠራው በውስጡ ባለው መንፈሳዊ ትኩረት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ትውስታ እና በቤተክርስቲያን ትምህርት ነው።
ስለዚህ ቅድስት ሲባል የሚጠቁመን እራሳችንን ቁዱስና እና ንጹህ አድርገን በንስሐ ታጥበን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበልን እኔ ቅዱስ ነኘና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ እንዳለ ከሐጢአት ከበደል ከክፋት ከተንኮል ከቂም ከበቀል ከሐሜት ከሐሰት ከምቀኝነት ከዘረኝነት ወጥተን በጎ በጎውን በማሰብ መልካም ሥራ በመሥራት መንፈሳዊ ሰው በመሆን ልንኖር ይገባል ፣አምላካችን መልካሙን ሁሉ እንድናደርግ ይርዳን አሜን ፣
ይቆየን ።