መስቀል – ፳፻፲፰ ዓ.ም.
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ አደረሰን ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብር የምትሰጠው?
” መስቀል ኃይላችን ነው ፣ ኃይላችን መስቀል ነው ፣ የሚያፀናን መስቀል ነው ፣ መስቀል ቤዛችን ነው ፣ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው ፣ አይሁድ ይክዱታል እኛ ግን እናምነዋለን ያመነው እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።” /የዘወትር ጸሎት/
“በብሉይ ኪዳን መስቀል የእርግማን ምልክት ና የወንጀለኞች መቀጫ ነበር::” (ዘዳ 21:23) ክርስቶስ በደሙ ስለቀደሰው ግን ቅዱስ መስቀል ተብሏል።
“በመስቀል ድህነትን አግኝተናል። ” (1ኛ. ጴጥ 2: 24-25) ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን በቀራኒዮ የተሰቀለበት ቤዛችን ነው። መስቀል የነጻነታችን ግርማ: የድህነታችን መገኛ: ጠላትን ድል የምንነሣበት መሳሪያችን ነው። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው በጥንቱ ፋርስ (በዛሬዋ ኢራን) ከክርስቶስ ልደት በፊት
(339 – 33) ዓመት ነው። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለምንድን ነው ለመስቀል ክብርን የምትሰጠው?
- ክርስቶስ መስዋዕት ሆኖ ራሱን የሠዋበት እውነተኛ መንበር በመሆኑ ፤
- የክርስቶስ ደም የፈሰሰበት: እኛ የዳንበት የነጻነት አርማችን በመሆኑ ፤
- የአምላካችን መለኮታዊ ፍቅር የተገለጠበት መሳሪያ በመሆኑ ፤
የመስቀል ዓይነቶች :-
- የመጾር መስቀል:- በቅዳሴ እና በማዕጠንት ጊዜ ሠራዒው ዲያቆን የሚይዘው ነው።
- የእጅ መስቀል:- ካህናት ምእመናንን የሚባርኩበት በእጅ የምትያዝ የመስቀል ዓይነት ናት።
- የአንገት መስቀል:- ምእመናን ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ ከማዕተባቸው ጋር በአንገታቸው የሚያደርጉት ነው።
- እርፈ መስቀል:- በማንኪያ ቅርጽ ተሠርቶ በእጅታው ላይ የመስቀል ምልክት ያለበት ነው። ሠራዒው ዲያቆን በቅዳሴ ጊዜ የአምላካችንን ክቡር ደሙን ለምእመናን የሚያቀብልበት ነው። እንዲሁም ጌታችን በእለተ አርብ የተወጋበት ጦር ምሳሌ ነው።
መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ይሰራል ። መስቀል ከተለያዩ ማዕድናት ሊሰራ ይችላል። መስቀሉ የሚሰራባቸው ማዕድናት የራሳቸውን ባህርያት እንዳላቸው ሁሉ ምሳሌውን ለመግለጽ ብቁ ናቸው ብለው አባቶች ያስቀመጡትን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
- የእንጨት መስቀል:- ጌታችን የተሰቀለው በዕጽ በእንጨት ላይ መሆኑን ለማመልከት ነው።
ለምን ኢየሱስ ክርስቶስ በእንጨት ተሰቀለ? አዳም ዕጽ/ እንጨትን በልቶ ሞትን በማምጣቱ ክርስቶስም በእንጨት ተሰቀሎ ህይወትን ሊሰጠን በእንጨት መስቀል ተሰቀለ። - የብረት መስቀል:- ጌታችን በአምስቱ ቅንዋተ ለመቸንከሩ ምሳሌ ነው።
- የብር መስቀል:- ይሁዳ በሠላሳ ብር አሳልፎ ስለመስጠቱ። በተጨማሪም ከብር ቢሰራ ተስፋን: ዕድልን ያመለክታል። ይኸውም እርሱ ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ ሊሆን በደሙ ዋጋ ከፍሏልና ከእርሱ ተስፋ እንድናደርግ ያመለክተናል።
- የወርቅ መስቀል፦ ከወርቅ ቢሰራ ወርቅ ንጹህ እንደሆነ ንጹሀ ባህርይ እድፈት የሌለው ጽኑ አንተ ነህ ብሎ ለመመስከር ነው።
- የመዳብ መስቀል:- መዳብ ቀለሙ ቀይ ይመስላል: ጌታችን ለእኛ ብሎ ያፈሰሰው ደም ምሳሌ ነው።
ብዙዎች የመስቀል ጠላት ሆነው መስቀልን ጣኦት ነው ይላሉ ጣኦት ማለት ግን የሠይጣን ስም የሚጠራበት ፣የሚመለክበት ነው።መስቀል ደግሞ የመድኃኒዓለም ስም የሚጠራበት ህማሙን የሚድኑበት አርማችን፣ ኃይላችን ነው እንጂ መስቀል አምላክ አይደለም። በመስቀል የተሠቀለው ግን አምላክ ነው። ምሳሌ:- ሰው አልጋ ላይ ሲተኛ አልጋ ላይ ተኛ ይባላል እንጂ እንጨቱ ላይ ተኛ አይባልም: ሰው የቤቱን በር ሲዘጋ እጨቴን ልዝጋ አይልም በሩን ልዝጋ ይላል እንጂ: አልጋ አልጋ ይባላል የተሰራው ከእንጨት ሊሆን ይችላል ነገር ግን እንጨት ተብሎ አይጠራም: በርም በር ይባላል እንጂ እንጨት ተብሎ አይጠራም። እንዲሁም ጌታ የተሰቀለበትን መስቀል መስቀል ይባላል ፤እንጂ እንጨት አይባልም።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ።
መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። (ፊልጵ 3÷18-19)
“ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።” ( ገላ 6:14)
“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ” ተብሎ ተጽፎአልና። (1ኛ ቆሮ 1÷18-19)
ልዑል እግዚአብሔር ከመስቀሉ በረከት ያድለን ።
በትሮንድሃይም ከተማ የምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን የደመራ በዓል እንዲህ ከታች በፎቶ እንደሚታየው በአማረ በደመቀ ሁኔታ አክብረናል እግዚአብሔር ይመስገን ፣፣