ደብረ ዘይት

ደብረ ዘይት:- የዐቢይ ጾም አምስተኛ እሑድ የጌታችን ዳግም መምጣትና የዘመኑ ምልክት የሚነገርበት ቀን በመሆኑና   ጌታችን ስለ ዓለም መጨረሻና ስለ መምጣቱ ምልክት የተናገረው በደብረ ዘይት ተራራ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ደብረ ዘይት እየተባለ ይጠራል። (ማቴ.24÷ 3)

ቅዱስ ያሬድ ዕለቱን ደብረ ዘይት ብሎ መሰየሙ ብቻ ሳይሆን በዕለቱም ያቀረበው ዝማሬ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአእላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬሕይወት”

ትርጉም፡-
“የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማይና የምድር ሠራዊት ሁሉ ይነቃነቃል። ያን ጊዜ በምድር የሚኖሩ ኃጢአተኞች ሁሉ ያለቅሳሉ፡፡ጌታችንም ከአእላፍ መላእክት ጋር በትእዛዙና በቃሉ መሠረት ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል። የእግዚአብሔር መለከትም ይሰማል፡፡ በዚያች ሰዓት እርሱ ያድነን። እርሱ የሕይወት ባለቤት ነውና።” በማለት ቅዱስ ያሬድ የዘመረው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24  ላይ ያለውን ነው።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣው ከአሁን በፊት በመጣበት መንገድ  በትሕትና ሳይሆን በልዕልና በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ሳይሆን በምልዓት በስፋት በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ነው። በከብቶች በረት ሊጣል ሳይሆን በደመና በዙፋን ተገልጦ ይመጣል። ስምዖን አረጋዊ እንደ ታቀፈው  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት ሆኖ ። ከእናቱ ጡትን እየለመነ ሳይሆን፣ ለፍጥረት ሁሉ  ዋጋ ለመስጠት ። ከሄሮድስ ፊት የሚሸሽ ሆኖ  ሳይሆን፣ ሰማይና ምድር ሲያዩት ከፊቱ  የሚሸሹለት  ሆኖ  ይመጣል ። የጌታችን ዳግም ምጽአት ፡-

  1. የጸሎታችን መልስ ነው።
  2. የፍጥረት የምጥ ዕረፍት ነው።
  3. የዘመናት ናፍቆት መልስ ነው።
  4. የተስፋችን ፍጻሜ ነው።
  5. የእምነታችን ክብር ነው።
  6. የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው።
  7. የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው፡፡

1.  የጸሎታችን መልስ ነው:-

ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ሲባሉ ይፈራሉ። ፍርሃታቸው ግን ለንስሐ አያዘጋጃቸውም። የጌታችን መምጣት ግን የጸሎታችን መልስ ነው። የምንፈራውና ይቅርብን የምንለው ሳይሆን በየዕለቱ “መንግሥትህ ትምጣ” እያልን የምንጸልይበት ትልቅ ርዕሳችን ነው። የዚህ ዓለም መንግሥት በግፍ ተጀምሮ በግፍ የሚጠናቀቅ፣ በውሸትና በሐሰተኛ ተስፋ ሰውን የሚያደክም፣ በጭካኔ ሲወዳደር የሚኖር፣ ደም በደም የሆነ መንገድ ነው። በዚህ ክፉ ሥርዓት የተጨነቁ ሁሉ ጽድቅና ሰላም የነገሠባትን የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ (ሮሜ.14÷17) ። የክርስቶስ መንግሥቱ የምትገለጠው ጌታችን ምድራውያን ነገሥታትን አሳልፎ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሚነግሥበት በዳግም ምጽአቱ ነው። ዳግም ምጽአቱ ምድራዊውን ሥርዓት አሳልፎ አንድ መንግሥትን በሁሉ የሚያፀና ነው።

2. የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው:-

ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና” ይላል። (ሮሜ.8÷19)ዳግመኛም “ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና” ይላል ቁ.22) ። በሰው ኃጢአት የተጨነቀው ሰው ብቻ ሳይሆን ፍጥረት በሙሉ ነው። እንስሳቱ አራዊቱ ሁሉ የሰውን ኃጢአት ቅጣት እየተካፈሉ ነው። እነዚህ ሁሉ የሚያርፉት ክርስቶስ ልጆቹን በክብር በሚገልጥበት በምጽአቱ ቀን ነው። ስለዚህ ፍጥረት ሳይወድ በግድ የሰውን ማረፍ ይናፍቃል። የራሱም ዕረፍት ነውና። ዛሬ በብዙ ነገር እናለቅሳለን። ብዙ ጭንቀቶችም ከበውን እንኖራለን። የክርስቶስ መምጣት ግን የፍጥረት ምጥ ዕረፍት ነው።

3.  የዘመናት ናፍቆት እርካታ ነው:-

“ አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና” (ራእ.22÷20)። ዮሐንስ በራእዩ ስለሚመጣው የዘመናት ጣር ካየበኋላ የዚህ ሁሉ ማብቂያው ምንድነው? ብሎ ሲያስብ የጌታ መምጣት እንደሆነ ተረዳ። ስለዚህም ማራናታ አለ። የጌታችን መምጣት የመከራው ድንበር ነው። በመጀመሪያው  ምጽአቱ ሞት እንደ ተገደበ፣ በዳግመኛ ምጽአቱም መከራ ገደብ ያገኛል።

4.  የተስፋችን ፍጻሜ ነው:-

የምንጠባበቃቸው ብዙ ተስፋዎች ቢኖሩም ትልቁ ተስፋችን ክርስቶስ ነው፡። የምንጠብቃቸው ነገሮች ቢሆኑልን እንኳ ሌላ መመኘታችን አይቀርም። ክርስቶስ ከመጣልን ግን ምንም እንዳያምረን ለዘላለም ያረካናል። ሐዋርያው ቀዱስ ጳውሎስ፡- “የተባረከው ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክብር መገለጥ እየጠበቅን ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” (ቲቶ.2÷12 13) ይላል። ሰዎች ተስፋ ካላቸው ራሳቸውን ከሚጎዳ ነገር ይከላከላሉ። እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋቸው የሆነ ይቀደሳሉ በኃጢአት መጫወት ተስፋ መቁረጥ ነው። የክርስቶስ ምጽአት የተስፋችን ፍጻሜ ነው። ለቤተ ክርስቲያን የቀረላት ተስፋ የክርስቶስ መምጣት ነው።

5.  የእምነታችን ክብር ነው:-

ጌታችን ዳግመኛ የሚመጣው በናቀን ዓለም ፊት እምነታችንን ሊያከብር ነው፡ የዘበቱብንና ያስጨነቁን ለዘላለም ያፍራሉ፡፡ዛሬ ቃሉን የረገጡ፣ ያን ቀን ፍርዱን መርገጥ አይችሉም። የእግዚአብሔር ልጆች የሆንም በዚያን ቀን በዘላለም ክብር ተውበን  እረኛችንን ተከትለን  ወደ ዘለዓለም  ደስታ  እንገባለን።

6.  የአዲስ ዓለም ጅማሬ ነው:-

በዮሐንስ ራእይ ላይ እንደ ተጻፈው “አዲስ ሰማይና አዲስ ምድርን አየሁ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና ባሕርም ወደፊት የለም” ይላል (ራእ.21÷1) ። አዲስ ነገር የሚያስፈልገው ፊተኛው ሲያረጅ ነው። ያረጀ ነገር መልኩ የወየበ፣ ጉልበቱ ያለቀ፣ ወደፊት ሊጠቅም የማይችል ነው። አሁን ፍጥረት አርጅቷል። በረዶ እየቀለጠ፣ የምድር ሙቀት እየጨለመ፣ መሬቱ ማዳበሪያ እየፈለገ፣ ሰውም በብዙ መድኃኒት እየኖረ ነው። ይህ የማርጀት ምልክት ነው። ይህን ሁሉ አዲስ የሚያደርገው የክርስቶስ መምጣት ነው። ሰውም ሞት ላይዘው በትንሣኤ፣ የሚመጣው ዓለምም ማርጀት ላያገኘው በአዲስነት ይኖራል።

7.  የዘላለም ሕይወት መክፈቻ ነው:-

ጌታችን ሲመጣ ዘላለማዊት የምትሆን መንግሥተ ሰማያት ትከፈታለች። ዛሬ በክርስቶስ ያመኑ በበጎ ሥራ የፀኑ አማንያን በጊዜያዊ ማረፊያቸው በገነት ይኖራሉ። ገነት ጊዜያዊ የነፍሳት ማረፊያ ናትና። ክርስቶስ ሲመጣ ገነትና ሲኦል ያልፋሉ። መንግሥተ ሰማያትና  ገሃነመ እሳት ይከፈታሉ (ማቴ. 25÷34.41) ።
ዘለዓለማዊው  ርስትም  ይከፈታል። ዘወትር አዲስ የሆነውን ጌታ እያየን በዘላለም ደስታ እንኖራለን።
የጌታችን መምጣት ብዙ ትርፎች ያሉት ወደማይነገርም ክብር የምንገባበት ነው። ዛሬ በዓለም ላይ የምናየው መከራና ሰቆቃ የምጽአቱ ዋዜማ ነው። ይህ ሁሉ ጭንቅ በክርስቶስ መምጣት ይጠናቀቃል።

የእግዚአብሔር ፍቅርና  ሰላም ከሁላችን ጋር ይሁን
አሜን ።

እንኩዋን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

”እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና…..”ሉቃ.2፤11

አስቀድሜ እንኩዋን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ዜና ነው፡፡እርሱ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማስወገድ ተወለደ፡፡መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ነገራት ”….ስሙን ኢየሱስ ትዪዋለሽ እርሱም ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል..” የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቀ. 32 ፡፡

ምናልባት ብዙ ጊዜ በተለምዶ ብቻ ገናን ወይም ልደትን ማክበር እየተስፋፋ የሄደ ጉዳይ ነው፡፡ ፈረንጆቹ በልደቱ ቀን ስጦታን መለዋወጥ ፤ ዛፎችን በደመቀ መብራት ማሸብረቅ፤ መብላት እና መጠጣት የመሳሰሉትን ጉዳዮች በመፈጸም ቀኑን ያሳልፋሉ፡፡ከበዛ ደግሞ ሳንታ ክሎስ ብለው ከሰየሙት የገና አባት ጋር ፎቶ መነሳት ሕጻናትን በውሸት ትርክት እንዲደነዝዙ በማድረግ የልደቱን ነገር የሚሸፍኑበትን የገና አባት የውሸት ትርክት እየነገሩ በማታለል….የልጆችን እውነቱን የማወቅ መብት በጊዜአዊ ብልጭልጭ ስጦታ ቀይረውታል፡፡
እንዲያውም አሁን አሁን ገና ማለት የልጆች ቀን ክፍለ ጊዜ እየመሰለ መጥቷል ፡፡ይህ ማለት ከዋናው ጉዳይ ጋር በእጅጉ የሰማይና የምድር ያህል እየተራራቅንና እየተለያየን ነው ማለት ነው፡፡

በአገራችንም ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት እና የገና ዛፎችን በማስጌጥ ሲዘፈን ሲጨፈር መዋል የተለመደ ነገር ሁኗል፡፡
ብቻ በሁሉም ጎን ማለት ይቻላል ፈር የለቀቀ ጉዳይ ይስተዋላል፡፡ ማለትም ከዋናው ጉዳይ ጋር ያለተገናኙ ነገሮች የበዓሉ ዋና ነገር ሆነው ቀርበዋልና፡፡

ከርስቶስን ከልደቱ ጀምሮ ሊገድለው ሲፈልግ የነበረ ሰይጣን፤ በኋላም ከሞት መነሳቱን በውሸት ዜና ተክቶ አልተነሳም ብለው እንዲናገሩ ሲጥር የነበረው ሰይጣን፤ አሁን ደግሞ ስልቱን ቀይሮ ሰዎች የልደቱን ትክክለኛ አላማ ቁም ነገር እንዳይረዱ በማድረግ በሚችለው ሁሉ እየሰራ ይገኛል፡፡በተወሰነ መልኩ የተሳካለትም ይመስላል፡፡

የልደቱን ምሥጢር ብዙዎች አልገባንም በቤተ ልሔም በግርግም የተወለደውን ሕፃን ከልባችንና ከቤት አስወጥተን ፤ በሰላሙ ፋንታ ሁከት በፍቅሩ ፋንታ ጥላቻውን በሕይወት ፋንታ ሞትን እያስፋፋን ወንድም ወንድሙን ልጅ አባቱን አባት ልጁን ወገን ወገኑን ለሞት አሳልፈን እየሰጠን።  ሰላም እምነት ደግነት የዋሀት ትሕትና ትዕግሥት እነዚህ ሁሉ ከልባችን ርቀው እነሱን ሳንመልስ ደግሞ ልደት ለማክበር ደፋ ቀና ማለት ምን ያህል ያለማስተዋል ይሆን ?
ምእመናን ሆይ ልብ ልንል የሚገባው ዋና ነገር የተወለደው ሕፃን ክርስቶስ በእኛ ልብ ስለመኖሩ እና የተወለደበት፣ የተሰቀለበት፣ የሞተበትና፣ የተነሳበት ትክክለኛ ዓላማ ገብቶናል ወይ የሚለው ቁም ነገር ነው፡፡
ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለመላእክት እስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ከመ ያግብዖ ለአዳም ቀዳሚ ብእሲ እምድር ውስተ ገነት ፣
የመላእክት ሀገራቸው ቤተ ልሔም ሆይ ደስ ይበልሽ የቀደመ ሰው አዳምን ከምድር ወደገነት ከሞት ወደ ሕይወት ይመልሰው ዘንድ በአንች ከአንች ተወልዷልና ፤ ብሎ ቅዱስ ኤፍሬም እንዳመሰገነ እኛም ገብቶንና ተረድተነው ልናከብር ልናመሰግን ይገባል።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከኃጢአት ለማዳን ተወለደ፤በእርሱ የኃጢአታችንን ስርየት እናገኛለን /የሐዋርያት ሥራ.10፤43/፤
መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላል፡፡ ሮሜ 10፤11

እርሱ የሕይወታችንም የክርስትናችንም መሠረት ነው፡፡ ያውም በልደቱ ቀን እርሱን ደስ የማያሰኘውን ጉዳይ እየፈጸምን እርሱን ከቤታችንና ከልባችን አስወጥተን ሰደን ወይም ቸል ብለን ድግሱ ላይ ብቻ የምናተኩር ከሆንን ምኑ ላይ ነው ክርስትናው? ያስብላል፤

ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ አንድያ ልጅህን ወደ ዓለም ልከህ ስለ ዓለም ሁሉ ኃጢአት ቤዛ እንዲሆን ፈቃድህ ስለ ሆነ እናመሰግንሃለን ፡ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሰራነውን መተላለፍና ኃጢአት ይቅር በለን፡፡
ጌታ ሆይ ወደ ልባችን እንድትመልሰን እንማፀናለን ሁለጊዜ አንተን በማመን ጸንተን እንድንኖር እርዳን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን በዓሉን የበረከት የንስሐ የሥርየት በዓል ያድርግል ፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን። ይቆየን።

መልካም በዓል ያድርግልን

ኖላዊ

የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ‹‹ኖላዊ›› ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት ‹‹እረኛ›› ወይም ‹‹ጠባቂ›› ማለት ሲሆን በዚህ ዕለት ቅዱሳን ነቢያት አምላክ ወልደ አምላክ እውነተኛ ጠባቂ ሆኖ ይገለጣል ብለው ትንቢት መናገራቸው እና ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት የተናገሩለት ኖላዊ ዘበአማን እውነተኛ ጠባቂ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ቤተክርስቲያናችን የምታስተምርበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውንና ሕዝበ እስራኤልን ፤ ብሎም ዓለምን ፤ እንደ በጎች በመቁጠር ስለ እውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል። በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ክርስቶስ ድረስ ያለው አሥራ አራት ትውልድ ይታሰባል። ቤተክርስቲያን ፦

“ ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አፅምእ፤
ዘይርዕዮሙ ከመ አባግዕ ለዮሴፍ፤
ዘይነብር ላዕለ ኪሩቤል አስተርአየ።
በቅድመ ኤፍሬም ወብንያም ወምናሴ፤
አንሥእ ኀይለከ ፥ ወነዐ አድኅነነ።

እረኛ የሌለው የበግ መንጋ ተኵላ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛው የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ (መዝ 79፡1) በማለት ይማፀኑ እንደ ነበር ታስተምራለች።

ቸር ጠባቂ: የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል›› ዮሐ፣ 10፥11 በማለት እውነተኛ አእረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ሰጥቷል። ስለራሱም ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፥ አብም እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ ነፍሴንም ስለ በጎች አኖራለሁ።›› ዮሐ 10፡15 በማለት አስተምሯል፡፡

በልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝ የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል መዝ (22፡1) ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ የጾም ወቅት አቤቱ ብርሀንህንና ጽድቅህን ላክ፣ ቸሩ እረኛችን ሆይ ተቅበዝብዘናልና እባክህ አስበን፣ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተበትነናልና ሰብስበን ጠፍተናልና ፈልገን አንተ እውነተኛ ሰላምህን ስጠን እያልን ሁሉን ወደ ሚችል ወደ እውነተኛው እረኛችን ወደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንስሐ ልንመለስ ይገባል።

ከተኩላዎች ተጠበቁ: ለክርስቲያኖች ሁሉ የታመነ ጠባቂ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹በጎቼን ጠብቅ›› ብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ በኩል አደራ የተሰጣቸው ካህናተ ቤተክርስቲያን የመንጋው ጠባቂ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሐሰተኛና ምንደኛ በበዛበት ዘመን እውነተኞቹን እረኞች ከተኩላዎቹ መለየት ያስፈልጋል፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ እንዲያፈራ መልካም እረኛም ለበጎቹ መልካምን ያደርጋል፡፡ ስለበጎቹም ይገደዋል ራሱን አሳልፎ ይሰጣል። (ማቴ 7፡15)፡ ተኩላ ግን በጎችን ሊጠብቅ ሳይሆን ሊነጥቅ እንደሚመጣ ሐሰተኞች እረኞችም ምዕመናንን ሊጠብቋቸው ሳይሆን ሊነጥቋቸው እየታገሉ ነው ፡፡ ነገር ግን መጨረሻቸው ጥፋት ስለሆነ ልናውቅባቸው ይገባል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ በገና ጾም ነቢያትም ሐዋርያትም ጾመው በረከት አግኝተውበታል፡፡ እኛ ምእመናንም እንደ እነርሱ በረከትን እናገኝ ዘንድ ይህንን ጾም መጾም እንደሚገባን የቤተክርስቲያን አባቶች ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ በዚህም መሠረት የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት አምላክ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ሐዋርያት በረከት እንዲያሳትፈን፤ መንግሥቱንም እንዲያወርሰን ሁላችንም በዚህ በጾመ ነቢያት ወቅት በጾም በጸሎት ተወስነን እግዚአብሔርን ልንማጸነው ይገባል ከቅዱሳን ነቢያት በረከት ያድለን አሜን፣

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ብርሃን

የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ‹‹ብርሃን›› ይባላል፡፡ ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ሰለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበካል፤ ይዘመራልም፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ነቢያት የነበሩበትን ያን ዘመን ጨለማ ብለው በመግለጥ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፣ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ቀን/ሳምንት/ ነው። በዚህ ሳምንት ከዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ዘመን ( 14 ትውልድ) ይታሰብበታል፡፡

ነቢያት የአምላክን ማዳን ከአስተማሩባቸውና፣ ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ልበ አምላክ ክቡር ዳዊትም ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን ወደ ዓለም እንዲመጣ “ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ” (መዝ 42፡3) በማለት ይጸልይ ነበር፡፡ ይህም ማለት ብርሃን፣ ጽድቅ፣ እውነት የሆነውን ልጅህን (ወልድን) ላክልን፤ እርሱ መርቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት ያስገባን ዘንድ ማለት ነው (ኢሳ 49)፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ‹‹ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ እውነተኛ ብርሃን ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት አስረግጦ ይነግረናል፣ (ዮሐ 1፡1-11)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ 8:12) ብሎ ስለ እርሱ እውነተኛ ብርሃንነትና አምላክነት በሚገባ አስተምሯል፡፡

በዚህ ዕለት ‹‹ከብርሃን የተገኘ ብርሃን›› እንዲሁም ‹‹የማይነገር ብርሃን›› የተባለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን መሆኑ አስረግጦልናል፡፡ ‹‹ብርሃን ወደ ዓለም መጣ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ እንዳስተማረን። ቅዱስ ኤፍሬምም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ‹‹በዚህ አለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለሰው ፍቅር ወደ አለም የመጣህ፤ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኽዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ጻዕረኝነት ነጻ አድርገኃታልና። የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኽን፤ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን የሕይወታችን ብርሃን የሆነውን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፡፡

እውነተኛ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ረድኤቱን ይላክልን ፣ አሜን ፣

ዘመነ ስብከት

ከታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 26 ቀን ያለው ዘመን ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ ዘመነ ስብከት የተባለበት ምክንያትም ነቢያት የጌታን በሥጋ መምጣት አምልተውና አስፍተው በትንቢትና በትምህርት መስበካቸውን ቤተክርስቲያን እያሰበች ሰውን ለማዳን ወደ ምድር የመጣውን አምላክ የምትሰብክበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡

ስብከት: የዘመነ ስብከት የመጀመሪያው ሰንበት (እሑድ) ‹‹ስብከት›› ይባላል፡፡ በዚህ ቀንም በኦሪተ ሙሴ፣ በነቢያትም አስቀድሞ ስለ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ትንቢት ተነግሮ፣ ምሳሌ ተመስሎ፣ ሱባዔ ተቆጥሮ እንደ ነበር ይነገራል፤ ይሰበካልም፡፡

እምኦሪተ ሙሴ እስከ ነቢያት ሰበኩ ምጽአቶ ንህነ ነአምን ስብከቶ ፣ ከኦሪተ ሙሴ አንስቶ እስከ ነቢያት የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት ሰበኩ አስተማሩ እኛም ሙሴና ነቢያት የሰበኩት ስብከት አምነን እንቀበላለን ፣እንዳለ (ቅዱስ ያሬድ )

ቅዱሳን ነቢያቱ አስቀድመው መምጣቱን ሰብከው ስለነበር ያንን ለማሰብ ይህ ዕለት ‹‹ስብከት›› ይባላል፣ ስብከት ማለት ሰውንና እግዚአብሔርን የሚያገናኝ ትምህርት ማለት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከአብርሃም እስከ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከው ስብከት ይታሰባል፡፡

የነቢያት ስብከት: በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደ ጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል (ዮሐ 1፡44)፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ፈኑ እዴከ እም አርያም » እጅህን ከአርያም ላክ አድነኝም› (መዝ 143፡7) በማለት ስለክርስቶስ ማዳን በትንቢት መነጽር ተመልክቶ የዘመረው የመዝሙር ክፍል እንዲሁ ይሰበካል፡፡ ከዐበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ! ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› (ኢሳ 64፡1) ብሎ ስለክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ፣ ከድንግል ማርያምም መወለድ የተናገረውን ትንቢት ቤተክርስቲያን ትሰብካለች፡፡

የቤተክርስቲያናችን ስብከት: ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” (2ኛ ቆሮ 4፡5) እንዳለው ቤተክርስቲያን በተለይ በዘመነ ስብከት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የሰጠውንና የፈጸመውን የማዳን ተስፋ ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ “ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን” እንዳለ ቤተክርስቲያናችን ፣ በጊዜውም አለጊዜውም፣ በችግርም በደስታም ስለ ኃጢአታችን የሞተውንና አምላክ ወልደ አምላክ ክርስቶስን ትሰብካለች፤

አምላካችን እግዚአብሔር ከአባቶቻችን በረከየተ ያድለን፣ አሜን።

ኅዳር 7 የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ በዓል በትሮንድሃይም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ።

ኅዳር 7 ቀን በቅዱስ ጊዮርጊስ ሀገር በልዳ በስሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተክርስቲያን የታነፀበት ዕለት ነው። ይህ ታላቅ በዓል በትሮንድሃይም ምሥራቀ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በማኅሌት፣ በቅዳሴ እና ፣ በዝማሬ በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።

«ጥብዒኬ እም ወኢትናፍቂ  ንፈጽም ገድለነ ወስምዓነ»
‟እናቴ ሆይ! ገድላችን እንፈጽም ዘንድ ጨክኝ በርቺ አትጠራጠሪ  አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ ያድነናል”
(ቅዱስ ያሬድ)

እንኳን ለታላቁ መልአክ ለቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን !!

በዛሬው ዕለት የቅዱስ ገብርኤልና የቅዱስ ቂርቆስ የቅድስት ኢየሉጣ አመታዊ ክብረ በዓል ነው።
በዚህ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት እየሉጣንና ልጇን ቅዱስ ቂርቆስን ከሥጋ መከራ እንደታደጋቸው ከፈላ የብረት ጋን እንዳወጣቸው  ታሪክ ይናገራል።

የ፳፻፲፪ ዓ.ም. ዘመን መለወጫ መልእክት

“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት” ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። 2ጢሞ 3÷1

+ + +

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን ።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ እንኳን ለ2012 ዓ/ም አዲስ ዓመት አደረሰን አደረሳችሁ ። እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ በሰላም በጤና አሸጋገረን አሸጋገራችሁ ።

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ዘመን ሲቆጠር 7512 ዓ/ዓ ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ከወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖ ከተወለደ ደግሞ 2012 ዓ/ም ይሆናል ።

ማይክሮ – ሰከንዶች – ሰከንዶችን – ሰከንዶች ሰዓታትን – ሰዓታት – ቀናትን – ቀናት-ሳምንታትን – ሳምንታት – ወራትን- ወራት- ዓመታትን እየወለዱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙር 64÷12 ላይ ” ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ ,, ዓመታትን በቸርነትህ ታቀዳጃለህ (አንድም) የምሕረት አመታትን በቸርነትህ ለሰዎች ታድላለህ ብሎ እንደተናገረ እየተፈራረቁ ዘመናት በዘመናት እየተተኩ ዛሬ ካለንባት ጊዜና ዘመን ደርሰናል ።

ነገር ግን አባቶቻችን ዘመንን የሚቆጥሩት በሕይወት የኖሩበትን ዘመን ነበር እኛ ደግሞ ዛሬ ዘመን በሕይወት የምንኖርበት ሳይሆን በሥጋ የምንኖርበት ብቻ ሁኗል የሰዎች የክፋትም ሆነ የደግነት፣ የመልካም ሥራም ሆነ የክፉ ሥራ ውጤት በዘመን ይገለጣል ለዚህ ነው ሐዋርያው በመጨረሻው ዘመን ያለው እንደ እድል ሆኖ የኛ ዘመን ከመልካም ይልቅ ክፋት የበዛበት ከእውነት ይልቅ ውሸት የሚታመንበት ከፍቅር ይልቅ ጸብ የሚወደድበት ከሰላም ይልቅ ሁከት የሚፈለግበት ከምሕረት ይልቅ መዓት የሚሰማበት ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአት የነገሠበት ከመረዳዳት ይልቅ መገፋፋት የሚቀናበት ከመተሳሰብ ይልቅ መረሳሳት የተለመደበት ከማመስገን ይልቅ መካሰስ የበዛበት ከትእግሥት ይልቅ ቁጣ የፈጠነበት ከትሕትና ይልቅ ትእቢት ከሥራ ይልቅ ስርቆት የሞላበት የመከራው ዘመን ነው ።

ዓለም እንደፈለገ የሚጋልብበት የውድድር ሜዳ አጥር ቅጥሩ የፈረሰበት ዘመን እየሆነ መጥቷል እኛ አሁን እየኖርን ያለነው ለተፈጠርንለት አላማ ሳይሆን በራሳችን አዙሪት እየተሽከረከርን መሆኑ ደግሞ እጅጉን ያሳዝናል ጥንቱን ሰው የተፈጠረው ለአንድ አላማ ነበር እሱም እንደ መላእክት ያለዕረፍታና ያለመታከት ያለድካም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልን ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ዓለም ግን መሥመር እየሳተ አቅጣጫ እየቀየረ መንገድ እየለቀቀ ነው ።

ይህንን ነበር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ “የሚአስጨንቅ ዘመን እንዲመጣይህንን እወቅ ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ” ብሎ ስለ አሁኑና ስለሚመጣው ዘመን በዝርዝ የነገረው ።  ቅዱስ ጳውሎስ ወረድ ብሎ ከቁጥር 14 ላይ እንዲህ በማለት ያስጠነቀቀበትን አረፍተ ነገር እናገኛለን ። “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና ” 2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥14

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ቃል መሠረት በማድረግ እንደ ደቀ መዝሙሩ እንደ ጢሞቴዎስ ታዛዦች በመሆን አዲሱና የሚመጣው ዓመት እኛ ተለውጠን ሌሎችን የምንለውጥበት እኛ ከብረን የምናከብርበት ሰርተን ዋጋ የምናገኝበት ያለፈውን ድክመታችንን የምናስተካክልበት ባለፈው ያባከነውን ጊዜ ሐዋርያው ያለፈው ዘመን ይብቃችሁ እንዳለ በቁጭት የምናስብበት ያስቀየምነውን ይቅርታ የምንጠይቅበት የቀማነውን የምንመልስበት ያጣነውን ሕይወታችንን ፈልገን የምናገኝበት ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የምንመለስበት ንስሐ ገብተን ባጠፋነው ክሰን የምንችል ሥጋውን ደሙን የምንቀበልበት የማንችል ሁሉን ወደሚችል አምላክ እንዲያስችለንና ለሥጋው ለደሙ እንዲያበቃን በጽኑ እምነት በቁርጥ ኅሊና በጠነከረ ልብ በበረታ ጉልበት ለጾም ለጸሎት የምንዘጋጅበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ እንዲአደርግልንም ተግቸ እጸልያለሁ ።

እናንተም እንደ ጢሞቴዎስ በተማራችሁበትና በተረዳችሁበት ነገር ጸንታችሁ እንድትኖሩ አደራ በማለት መልእክቴን አስተላልፋለሁ ።

መልአከ ፀሐይ አባ ቀለመወርቅ

የ፳፻፲ የጌታችን ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በቤተክርስቲያናችን በደማቁ ተከበረ

ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን

ሞተ ወኬዶ ለሞት

ለእለ ውስተ መቃብር

ወሃበ ሕይወተ ዘለዓለመ ዕረፍተ።

የ፳፻፲ ዓ.ም የጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እና ትንሣኤ በዓላት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ በድምቀት ተከበረ። በዓላቱ ከስዊድን ተጋብዘው በመጡት አባታችን መልአከ ህይወት ፍስሐ አባ ገብረማርያም ቢምረው እና በርካታ ቁጥር ባለው የትሮንዳሄምና አካባቢው ምእመን ሱታፌ በተለያዩ አገልግሎቶች ተከብሯል።

ዕለተ ዓርብ መጋቢት ፳፰፥፳፻፲ ዓ.ም በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጌታችንን ስቅለት በሚያወሱ ምንባባት፣ ሕማሙን በሚዘክሩ ጸሎቶች እንዲሁም በስግደት ያለፈ ሲሆን፤ በመጨረሻም ዕለቱን የተመለከተ ትምህርት ተሰጥቶ በቡራኬ የዕለቱ መርሃ ግብር ተፈጽሟል።

ቅዳሜ ምሽት ከ20:00 ሰዓት ጀምሮ የጌታችንን ትንሣኤ የሚያወድስ ሥርዓት ከምንባባት ጋር ከተከናወነ በኋላ በሥርዓተ ቅዳሴና ቡራኬ መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል። በዓሉን ለመካፈል የተገኘውም ህዝበ ክርስቲያን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ጸበል ጸዲቅ ቀምሰው ወደየቤታቸው በሰላም ተመልሰዋል።

 

የበዓሉን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ።

የ፳፻፲ ዓ.ም. የዘመን መለወጫና የመስቀል ደመራ በዓላት በደመቀ ሁኔታ ተከበሩ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የትሮንዳሔም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የ፳፻፲ ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓልን በማስመልከት እሁድ ጷጉሜን ፭፥፳፻፱ ዓ.ም ከዴንማርክ ተጋብዘው በመጡት አባ ዘሚካኤል የቅዳሴ አገልግሎትና የወንጌል ትምህርት የተሰጠ ሲሆን በዕለቱ ከትሮንዳሄምና አካባቢው የተገኙ ምዕመናንም በክብረ በዓሉ ላይ ታድመዋል። በተጨማሪም ቀኑን የተመለከቱ መዝሙሮችም በኅብረት ተዘምረዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ማክሰኞ መስከረም ፲፮፥፳፻፲ ዓ.ም በትሮንዳሔምና አካባቢው ከተገኙ ምዕመናን እንዲሁም ከቅዱስ ሚካኤል የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በመጡ ምዕመናንና አገልጋዮች በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

በዓሉ ማክሰኞ ዕለት ከሰዓት በኋላ 17:00 ሰዓት ላይ በጋራ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በመጡ አገልጋዮች ወረብና ቀኑን የሚያወሱ ንባቦች ቀርበዋል። በመቀጠልም የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መዘምራን በዓሉን የተመለከተ መዝሙራትን ያቀረቡ ሲሆን ስለመስቀል በዓል የሚያስረዳ ስነ ጽሁፍም ቀርቧል። ቀጥሎም ደመራው በወረብና በመዝሙር ምስጋና በመታጀብ ተለኩሷል። መዘምራንና መላው ምእመንም በጋራ በመዘመር በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል። በመጨረሻም ምእመናኑ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ዝክር ቀምሰው ወደ የመጡበት በሰላም ተሸኝተዋል።

በዚሁ አጋጣሚ በተለያዩ መንገዶች ለዝግጅቱ መሳካት ብሎም ለበዓሉ ድምቀት መንፈሳዊ አስትዋጽኦ ላበረከታችሁ ምዕመናን ሁሉ በሊቀ ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስም ልባዊ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን።

የበዓላቱን አከባበር በፎቶ ይመልከቱ